የአትላንታ ቅድስት ማርያም የቤተክርስቲያን ችግር መነሻና መድረሻ /የቀድሞ የአስተዳደር ቦርድ አባል/

የአትላንታ ቅድስት ማርያም የቤተክርስቲያን ችግር መነሻና መድረሻ /የቀድሞ የአስተዳደር ቦርድ አባል/

የሰዐሊተ ምህረት ቅድስት  ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን፣የቦርድ አባላት እና የአባቶች መከፋፈል የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም መከፋፈል በዓለማዊ ሕግ እንዲወሰን ፍርድ ቤት በመቅረቡ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እጅጉን አሳዝኗል። ሃዘኑ እጥፍ ድርብ ያረገው ዛሬ  በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ወጣቶችን በጅምላ ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ በመጨፍጨፍ፣ በማሰርና በመግደል ላይ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው። የቦርዱ ሊቀመንበር አቶ አባተ ዘውዴ እና ጓደኞቹ እነ አቶ አየለ ገብሩ በሊቀ ጳጳሳት እና በሽማግሌዎች ፤ በሞቱ ከአባቱ ጋር እና ከራሱ ጋር ባስተረቀን አምላክ ስምእንዲሁም በአግአዚ ጦር አልሞ ተኳሾች የልጆቻቸው ግንባር እየተመታ የተገደሉባቸው ስለሚያለቅሱት እናቶች ስትሉ ፣ ስለ ቅድስቲቷ አገራችን የኢትዮጵያ አምላክ ብላችሁ  እባካችሁ ለሰላም እጃችሁን ዘርጉ ሲባሉ ልባቸው እንደ ፈርዖን ደንድኖ እንቢ ሲሉ ማየት ልብን የሚያሳምም ክስተት ነው። ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥምና አሁንም በግራም ሆነ በቀኝ የተሰለፉት ምእመናን እና አባቶች በእግዚአብሔር ቸርነት ችግሩን በሰላም ይፈታሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ምእመናን በሳምንት ከአርባ እስከ ስልሳ ሰዓት እግራቸው እየነደደ ቆመው ሰርተው እንዲሁም በጸሃይ እና በብርድ እየተቃጠሉ ታክሲ እየነዱ ካገኙት ገንዘብ ለእግዚአብሔር ቤት ያቀረቡትን መባ ለፈረንጅ ጠበቃ ሲሳይ ማድረግ የማንም ሰው ህሊና ስለማይፈቅድ በሽምግልና እንደሚያልቅ ሙሉ ተስፋ አለኝ።አንደ ቤተክርስቲያን አባልነቴ እንደዚሁም ከዚህ በፊት እንደ አስተዳደር ቦርድ አባልነቴ የቤተክርስቲያናችን ችግር መነሻ ብዬ የተገነዘብኩትን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
የዚች ቤተክርስቲያን አባል ከሆኑኩ ከ18 ዓመት በላይ  አስቆጥሬአለሁ። ያኔ የነበርነው በትንሿ ቤተክርስቲያን ሲሆን አሁን የማውቃቸው ምእመናን በሙሉ ያወኳቸው እዛ ነበር። አሁን በተነሳው ውዝግብም የቦርድ አመራር የነበሩት ያኔም የቦርድ አመራር ነበሩ። ያንጊዜም  ተፈጥሮ ለነበረው ያለመግባባት የተወሰደው መፍትሔ አሳዛኝ ነበሩ። የቦርድ አባላት የነበሩ ጥለው ሄደዋል፤መዘምራን ተባረዋል። አሁንስ የተፈጠረው አለመግባባት እንዴት ተጀመረ?
ጊዜው ብጹዕ አቡነ ያዕቆብ የኤጲስ ቆፖስ ሹመት ያገኙበት ነበር። በወቅቱ አቡነ ያዕቆብ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ነበሩ።እነ አቶ አባተ ያቀዱትን ድብቅ አላማ ወደ ግብዓት ለማድረስ ይችሉ ዘንድ አቡነ ያዕቆብ የጵጵስናውን ማዕረግ በተቀበሉ ማግስት የአስተዳዳሪነቱን ስራ እንዲያስረክቡ ውትወታ ጀመሩ። ብጹዕነታቸውም ጥያቄውን ተቀበሉት። ለአቶ አባተና ጓደኞቹ እንዲሁም ከውጭ ሆነው ከአቶ አባተ ጋር በመተባበር ቤተክርስቲያኗን ከሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አውጥቶ በመጀመሪያ ወደ ገለልተኛ ቀጥሎም ወደ ሀገር ቤቱ በወያኔ የሚዘወረው ሲኖዶስ ለማስገባት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረ።በመቀጠልም በህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ከፈቱ።ያንኑ ሰሞን ከአንድ ቦርድ አባል ኢሜይል ተላከልኝ እና ሳየው ጽሁፉ ከወያኔ ደጋፊ ከሆነ ድረ ገጽ ላይ የተገኘ ሲሆን መልእክቱ በስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ ውስጥ የሚገኙት ሊቀ ጳጳሳት ሁሉ ጎንደሬ መሆናቸውን ገልጾ ይህንን ሲኖዶስ መዋጋት እንዳለብን አስረግጦ የሚናገር ነበር።
አቡነ ያዕቆብን ከቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪነት ከማስወገዳቸው በፊት ለአላማቸው የሚረዳ ቄስ ማፈላለግ ጀመሩ። ይህ መደበኛውን የአስተዳደር ቦርድ ያልተከተለ እንዲሁም የቦርድ አባላት ያልተሳተፉበት ካህን ፍለጋ ሂደት በአቶ አባተና በአቶ ቴዎድሮስ ነበረ የተከናወነው። ሆኖም ቤተክርስቲያናችን በአገልጋይነት የምታስመጣቸው ካህናት የሚከተሉትን መስፈርቶች ሟሟሏት አለባቸው።
     1፦በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና ስርዓት መሰረት ስልጣነ ክህነቱን ያገኘ።
     2፦ ስለ መልካም ስነ ምግባሩ የተመሰከረለት ፤በቂ የቤተክርስቲያን ትምህርት እና ችሎታ እንዳለው የተረጋገጠ።
     2፦ቤተክርስቲያናችን የምትቀበለውን ሲኖዶስ የሚቀበልና የሚያከብር።                                               
የችግሩ ዋና መንስኤ
ከላይ እንደተገለጸው ካህን የማፈላለጉ ጉዳይ ሂደት አልቆ መጋቤ ብሉይ አባ ኃ/ሚካኤል የሚባሉ ካህን መመረጣቸውን በዚያን ጊዜ የአስተዳደር ቦርድ አባላት ለነበርነው ተነገረን። የቤተክርስቲያን ትምህርት ችሎታቸው ተገልጾልን ምርጫው እንድናጸድቅ ተጠየቅን። በወቅቱ መተማመን ስለነበረ፤ የቦርዱ ሊቀመንበር ተንኮል ያስባል ብለን ስሳሳሰብን አፀደቅነው። ሆኖም አቶ አባተ እና  ጓደኞቹ አባ ኃ/ሚካኤል ሲያስመጡ የሚከተሉትን ጉዳዮች ለማስፈጸም ተስማምተው መሆኑን ቆይተን ተረዳን። እኝህ አባት የውጭውን ሲኖዶስ እና በውስጡ ያሉትን አባቶች በአባትነት ስለማይቀበሉ አቡነ ያዕቆብን በተለይ መምህር ልዑለ ቃልን  ለማባረር በሚደረገው ጥረት አንዲያግዙ እና በስደት የሚገኘውን ቅዱስ ሲኖዶስ በተሃድሶነት በመፈረጅ ቤተክርስቲያናችን ከሲኖዶስ እንድታፈነግጥ ነው።
 ሁላችንም እንደምንገነዘነበው በስራችን ገበታ ላይ አንድ አዲስ ሰራተኛ  በአንድ ኩባንያ ውስጥ ሲቀጠር  የሚከተሉትን መስረርቶች ሲያሟላ ነው። በመጀመሪያ የኩባንያውን ህገ ደንብ ተቀብሎ እና አስተዳደሩን ሲያከብር ቀጥሎም ከማንኛውም ወንጀል ነጻ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው።በአንጻሩ አባ ኃ/ሚካኤል ህገ ደንባችን አይቀበሉም እንዲሁም በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተዋረድ ሊቀ ጳጳስ የበላይ መሆኑም አያምኑም። በተደጋጋሚ የቦርድ ስብሰባ ላይ ተጠሪነቴ ለቦርድ ሊቀመንበር ሲሉ ሰምተናቸዋል። በተጨማሪም ወደ እኛ ከመምጣታቸው በፊት ያገለግሉበት ከነበረው ዱባይ ቤተክርስቲያን በስነ ምግባር ጉድለት ማለትም በዝሙት ቅሌት ተከሰው እንደነበር ይነገራል። ማስረጃ አለን የሚሉት አባላት ለኔ በግል አሳይተውኛል። አንድ የቦርድ ሊቀ መንበር እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበትን ካህን አስመጥቶ በፍጥነት አስተዳዳሪ እንዲሾሙ ማድረግ ፤ ለቤተክርስቲያን አስቦ ነው ወይስ ሌላ ድብቅ አጀንዳ?
ከላይ ከዘረዘርኳቸው መረጃዎች ተነስቼ ለአንባብያን ማስጨበጥ የምፈልገው እውነታ፤ የዚች ቤተክርስቲያን ችግር የጀመረው አባ ኃ/ሚሳኤል የቤተክርስቲያናችን አስተዳዳሪ ከሆኑ በኃላ ነው። ግን በጥፋተኝነት የምፈርጀው አባ ኃ/ሚካኤልን ሳይሆን የቦርዱ ሊቀመንበር አቶ አባተን ነው። አባ ኃ/ሚካኤል ይዘው የመጡት የሚያምኑበትን ዓላማ ነው። ሄደውም የተቀላቀሉት የሚያምኑበትን ዓላማ የሚያራምድ  የቤተክርስቲያን  ነው።
ቤተክርስቲያናችን አሁን ለደረሰችበት ሁካታ እና ብጥብጥ ሃላፊነቱን የሚወስዱት አቶ አባተ እና ጓደኞቹ ናቸው። ምክንያቱም የኚህን ካህን አቋም እያወቁ ከቤተክርስቲያኒቱ ሰላም ይልቅ የግል ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም እኚህን አባት በማስመጣታቸው ነው። አባ ኃ/ሚካኤል የዜማ ትምህርት የተማሩ እና ነገር አሳክተው መናገር የሚችሉ ጮሌ መነኩሴ  ናቸው።አብዛኛው የቤተክርስቲያናት አባላት ህገ ደንቡ በሚያዘው መሰረት በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ ተቀብሎ የሚኖር ህዝብ ነው። ታዲያ ህጋዊውን ሲኖዶስ የማይቀበል ካህን አምጥቶ የክርስቶስን መንጋ ማበጣበጥ ብሎም መከፋፈል ክርስቲያናዊነት ነው? አቶ አባተን እና ጓደኞቹን እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው!
አባ ኃ/ሚካኤል በአስተዳዳሪነታቸው ዘመን  አውደ ምህረት ላይ የሚያቀርቡት መልእክታት አሽሙርን እና ዘለፋን  እንዲሁም ከፋፋይና አወዛጋቢ በመሆኑ  ምእመናንን ከፋፍሏል ።  ስለዚህም ምእምናን፣ መዘምራን እና የቦርድ አባላት ተከፋፈሉ። ክፍፍሉ ከቤተክርስቲያን አልፎ በማኃበራዊ ህይወት ውስጥ ለቤተክርስቲያናችን እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የጽዋ ማኀበራት እና ቤተሰብ ጋር ደርሶ በመከፋፈላቸው ዛሬ ቤተክርስቲያናችን ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት እነ አቶ አባተ ወስደዋቷል። በመጨረሻም አባ ኃ/ሚካኤል ከአቡነ ያዕቆብ ጋር በእምነት የተለያየን አብረን መስራት አልችልም ብለው በመሰናበት የሃገር ቤቱን ሲኖዶስ ተቀላቅለዋል።
የተከበራችሁ አንባብያን በአሁኑ ሰዓት እዚህ የሌሉትን አባ ኃ/ሚካኤል ማንሳት ፈልጌ ሳይሆን አቶ አባተ እና ጓደኞቹ እሳቸውን ተጠቅመው ቤተክርስቲያኗን እንደበጠበጡ የምስክርነት ቃሌን ለመስጠት ነው።
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችን እና ሀገራችንን ከጥፋት ይጥብቅልን

LEAVE A REPLY