ጄኔራሉና ያልከፈልነው ዕዳ! /ምስክር/

ጄኔራሉና ያልከፈልነው ዕዳ! /ምስክር/

በዚህ የመጽሔት ስራ ውስጥ ትልቁን ሚና ከሚጫወት ወዳጄ የተደወለልኝን ስልክ ከአነሳሁ በኋላ ሌላ በዚሁ ስራ ላይ የበኩሉን ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ወዳጃችን ተቀላቀለን ። ትልቁ እንግዳ የመጡት መጨረሻ ላይ ነው ።

ስናስባቸው ከርመን ነበር ። ስላለፈው ደግም ሆነ ክፉ ቀን ፣ ስለዛሬው ጥረታችንና ሰለወደፊት ተሰፋችን የሚሉትን ከአንደበታቸው ለማዳመጥ ጓግተናል ። ትሁትና ቅን ሰላምታ ተለዋውጠን ወደጉዳያችን ገባን ።

ብርጋዴር ጄኔራል አሸናፊ ገብረጻዲቅ ይባላሉ ። ዛሬ አሜሪካ ውስጥ በስደት ሲኖሩ አስራ ሁለት ዓመታትን አስቆጥረዋል ። በክፉ ቀን ኢትዮጵያን ከታደጓት የቀድሞው አየር ኃይል አባላት መሃከል አንዱና ግንባር ቀደሙም ናቸው ። በእኛ ዘመን ሃገሪቷ በይፋ ከመሰከረችላቸው ጥቂት ጀግኖች መሃከል በሕይወት ሰንብተዋል ። የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ተሸላሚው ጄኔራል ስለነገም ብሩህ አመለካከት አላቸው ። ወደፊት ለማየትም ወስነዋል ።

ጥያቄያችንን አሃዱ ብለን የጀመርነው አሁን በመቋቋም ላይ ስለአለው የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ሕብረት ነበር ። ምን ሃሳብ አለዎት አልናቸው ። መልሳቸው ወደፊት ለማየት ዝግጁ ከሆነ ሰው የሚጠበቅ ነበር ። እንዲህ አሉን ። “ይህ ትልቅ ዓላማ ነው ። ጅምሩን ወድጄዋለሁ ። እሰከአሁን በተሰራው ላይ አንድ እርከን የሚጨምር ነውና መበረታታ አለበት” … ፤ አሉና በሳል አመለካከታቸውን ጫን በማድረግ አከሉበት ።

በጄኔራሉ አነጋገር ትልቅ ዓላማ ስኬታማ የሚሆነው በጎ (positive) አመለካከት ቅድሚያ ሲሰጠው ብቻ ነው ። ይህንን ከጅምሩ አይተዋል ። ጎጂ ሃሳቦች ትርፍ አያስገኙም ባይ ናቸው ። እናም ይህ ማሕበር ጠቃሚና ገንቢ ሰራዎችን እንዲሰራ ይጠብቃሉ። በእሳቸው አመለካከት ብዙ ስራዎች

ከፊታችን ተደቅነዋል ። በዓለም ዙሪያ የተበተነው ፣ ዛሬ ዲያስፖራ ተብሎ ስም ከወጣለት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን መካከል የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ቁጥር ጥቂት አይደለም ። ይህንን ኃይል ማሰባሰብ ፣ ታሪኩን ፣ ሙያውንና ልምዱንም ዘግቦ ለትወልድ ማሰተላለፍ በራሱ ትልቅ ስራ ነው ይላሉ ።

ጄኔራል አሸናፊ መሰረታቸው ሲዳሞ ነው ። ክበረመንግስት ከተማ ውስጥ በ1937 ተወልደው እዚያው አድገው ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአጠናቀቁ በኋላ ነው በ1954 ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ሰርቬይንግ (ቅየሳ) ለማጥናት አዲስ አበባ የመጡት ። አየር ኃይልም የመለመላቸው እዚያው ተገባረ ዕድ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያሉ በ1957 ዓም ላይ ነበር ።

ምልመላው የሚጠይቀውን መመዘኛ ሁሉ አሟልተው በዚያው ዓመተ ምህርት የበረራ ኮርሳቸውን ደብረ ዘይት ሐረር ሜዳ ወዲያው ቀጠሉ። ዩኒት P-16 ፣ ሃያ አንድ የበረራ ተማሪዎችን ሳፋየር አውሮፕላን ላይ አሰልጥኖ ከአስመረቃቸው ሰድስት ዕጩ መኮንኖች መሃከል ጄኔራል አሸናፊ አንዱ ነበሩ ። ከዚያ በኋላ T-28 ዲ ታክቲካል ተዋጊ አውሮፕላን ላይ ስልጠናቸውን ቀጥለዋል ። OCS – 6 ገብተው በም/መቶ አለቃነት ማዕረግ ከተመረቁ በኋላ በበረራ አስተማሪነት ከ1961 እስከ 1963 ድሬደዋ ተመድበው አገልግለዋል ። ከዚያም ወደ አስመራ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ደብረ ዘይት ተዛውረው F- 5 ላይ ተመድበው ከሰሩ በኋላ በ1967 F- 5E ላይ ለመሰልጠን ወደ አሜሪካ ተልከዋል ።

ከዚያ በኋላ ነው ኢትዮጲያን ከጠላት ለመታደግ ግንባር ላይ የተሰለፉት ። ሶማሊያ ለረዥም ዘመናት ስትዘጋጅበት የቆየችውን ጦርነት ቀድመው ከተጋፈጡት መሃከል ጄኔራል አሸናፊ አንዱ ናቸው ። አሁንም ድረስ እንደሚያስታውሱት ኢትዮጲያ ለዚህ ጦርነት ዝግጁ አልነበረችም ። በተለይም በምድር ጦሩ በኩል ዝግጅቱ አልነበረም ። አየር ኃይላችን በመሳሪያ ኃይል አነስተኛ ይሁን እንጂ ያሉትን አውሮፕላኖች በሚገባ ሊጠቀሙ የሚችሉ ጥቂት ምርጥ በራሪዎች ነበሩት ። ጄኔራል አሸናፊን ጨምሮ ።

ጄኔራል አሸናፊ ቀድም ሲል የአየር ለአየር ውጊያ በግሩም ሁኔታ የተለማመዱ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባር ላይ ያዋሉት የሶማልያ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ላይ ነበር ። በዚህ አሃዱ ባሉበት የጦር ሜዳ ውሎአቸውም ግዳይ ጥለዋል ። አድብቶ ከኋላ ሲከተላቸው የነበረውን የሶማልያ ሚግ አውሮፕላንን ፈጣንና ድንገተኛ የአቅጣጫ ለውጥ አድርገው በታጠቁት ሚሳይል ደረቱን ለሁለት በመግመስ አየር ላይ ብትንትኑን አውጥተውታል።

በዚያን ዘመን ለረዣዥም ሰዓታት ፣ ሌትና ቀን ሰማይ ላይ ነጭ ላብ ፈሷል ። ሕይወትም ተገብሯል ። ለግዳጅ ሸኝተን መልሰን ያልተቀበልናቸው ጀግኖች ዛሬም ባለውለታዎቻችን ናቸው ። ይሄ ሁሉ ለነጻነትና ለሉአላዊነት የተከፈለ ክቡር መስዋዕትነት ነበር ። ከዚያ ሁሉ መዓት ተርፈው ገና ብዙ ሊያገለግሉን ፈቃደኛ የነበሩ ወደር የማይገኝላቸው የአገሪቷ ሃብቶች መንግስት ስለተለወጠ ብቻ እንደ ተራ ወንጀለኛ አለም በቃኝ መውረዳቸው ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ነው ። እንዲህ አይነቱ ክፉ ዕጣ ከደረሰባቸው የአየር ጀግኖች መሃከል ጄኔራል አሸናፊ ገ/ፃድቅ አንዱ ናቸው ። ህውሃት ደብረ ዘይትን የተቆጣጠረ ዕለት ሻቢያዎች ነበሩ ጀነራል አሸናፊ መኖሪያ ቤት ድረስ በመምጣት በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው ። ቆይተውም ለህውሃቶች አስረከቧቸው ።  ህውሃት ከተረከባቸው በኋላ ታድያ ድፍን አስር ዓመት እስር ቤት ውስጥ ማቀዋል ። ገና ባልቀዘቀዘ የተዋጊነት ስሜት ፣ ባልተኮላሸ ወኔ ላይ የነበሩ ጀግና የአየር ሰው ለእስር ተዳረጉ ። አስር ዓመት ሙሉ ከአንዱ እስር ቤት ወደሌላው እያዟዟሩ አንገላተዋቸዋል ። ይሄ ከዕድሜዬ ላይ በግፍ የተነጠቀ ዘመን ነው ይላሉ ጀነራሉ ። ሆን ተብሎ አስር ዓመት ታሽጎ እንዲዝግ የተበየነበት ዕውቀትና ልምድ ብዙ ወጪ የወጣበት የሃገር ሃብት ነበር።

ኢሕዲግ አዲስ አበባ እሰከገባበት ቀን ድረስ ጠቅላይ መመሪያ ውስጥ የስራ ገበታቸው ላይ የነበሩት ጄኔራል አሸናፊ የዘመቻ አዛዥነት ግዳጃቸውን እየተወጡ ነበር ። እንዲያው ስለ አጠቃላይ ሁኔታው ምን ይሰማዎታል ? አልንና ጠየቅናቸው ። መቼም የመንግስት ስልጣንን በጠመንጃ የጨበጠ ኃይል መረጋጋት እስኪፈጠር ድረስ የተሸነፈውን ሰራዊት ለሶስት ወር ያህል አግልሎ ቢያቆይ የአባት ነው ብለው ለጥያቄያችን መልስ በመስጠት ጀመሩ። በማስከተልም አስር ዓመት አስሮ ማንገላታት ግን ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን ሃገሪቱንም መጉዳት ነው ይላሉ ። ለምን እንዲህ ማድረግ እንደተፈለገ  እሰከ አሁን ድረስ መልስ ያላገኙለት ጥያቄ እንደ ሆነ አለ ።

እስኪ አስቡት ኢትዮጲያ ለዓመታት ሰማይ ላይ በመዋል ከጠላት የታደጓትን ጀግኖች ሐውልት ልታቆምላቸው ሲገባ ጭራሽ አስራ አንገላታቻቸው ፣ ሞት ፈረደችባችው  ቢባል እንዴት ይታመናል ?  እንደኔ ሃገሬ ያልከፈለችው ዕዳ አለባት ።

ጄኔራል አሸናፊ በቅንነት ከልብ ያገለገሉበትን መስሪያ ቤት የራሳቸውን ያህል ይወዱታል ። ኢትዮጲያ ልጆቼ የምትላቸውን ሁሉ ከአሉበት አሰባስባ የምታሰለጥንበት ፣ አብሮ መኖርንና መከባበርን በተግባር የምታስተምርበትን የያኔውን አየር ኃይል በእጅጉ ያስታውሳሉ ። የድርጅቱን ጥንካሬም ከዛሬው ጋር ሲለኩት በእጅጉ ይቆጫሉ ። እሳቸው የሚያውቁት አየር ኃይል አባላቱን በቅብብሎች ነበር የሚያሰለጥነው ። ዕውቀትና ልምድ ከአባት ወደ ልጅ እነደሚተላለፍ አይነት ። ለዚህም ነበር ከጊዜው ቴክኒዎሎጂ ጋር የሚሄዱ ብቁ ሰዎችን ማፍራት የተቻለው ። ይሄ ዛሬ አለ ብለው አያምኑም ።

ወደፊት እንዴት መኖር አለበን ? ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ የሰጡን መልስ ለብዙዎቻችን ፣ መጽሐፉን ከድነን ማስቀመጥ ለከጀለን ሰዎች ትልቅ ትምህርት ሊሆን ይችላል ። መግቢያችን ላይ እነደጠቀስንላችሁ ሁሉ ጄኔራሉ የሚያዩት ሩቅና ወደፊት ነው ። መጀመሪያ እንደ እምነታችሁ ኑሩ አሉ ። እኔ ክርስቲያን ነኝና እንደክርስቲያን መኖር አለብኝም አሉ ። ይህም ደግና መልካም የሆነውን ብቻ መስራት ማለት ነው ። ከዚያ ተስፋ አለመቁረጥ ነው አሉን ። ብዙ ታለንት (ተሰጥዖ) አለ ፤ ባክኖ እንዳይቀር መታገል አለብን ። ይህንን ታለንት ጥቅም ላይ ለማዋል መዝግበን ለልጆቻችን ማስተላለፍ አለብን ባይ ናቸው ። እኛም ብንሆን አርቀን ማሰብ አለብን ። ዕድሉ ሲፈጠር ሃገራችን ገብተን ብዙ ለመስራት እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ነው ያሉት ጄኔራሉ።

ጄኔራል አሸናፊ ምንም እንኳን አሁን ለጊዜው ተለይተዋቸው ባሕር ማዶ ቢኖሩም ባለትዳር ፣ የአንድ ልጅ አባትና የሁለት የልጅ ልጆች አያት ናቸው ። ያላቸውን ጥቂት የዕረፍት ጊዜ ሰውተው ታሪካቸውንና ሃሳባቸውን ስላካፈሉን መስጋናችን እጅግ የላቀ ነው ። ይህ ጽሑፍ ከሰፊው ታሪካቸው ላይ በማንኪያ የተጨለፈ መሆኑን ግን አትዘንጉ። ባለታሪኩ ልከውልን ዘግይቶ እጃችን የገባው መረጃ የሚናገረው ይህንን ነው። ወደፊት በሰፊው እንመለስበታለን።

LEAVE A REPLY