በአማራነት ስለመደራጀት፤ አንዳንድ “አማሮች” ምን ነካቸው? /ተክለሚካኤል አበበ/

በአማራነት ስለመደራጀት፤ አንዳንድ “አማሮች” ምን ነካቸው? /ተክለሚካኤል አበበ/

ያለፉት ጥቂት ወራት፤

1- በዚህ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ፤ ለአመታት የኢትዮጵያውነት ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች/ቡድኖች፤ ደርሰው ”አክራሪ አማራ” መሆን ጀምረዋል፡፡ ይሄ ነገር ደግሞ ከዚህ “ከወልቃት የማነው” ወይም “ወልቃይቴ ማነው” ጋር ተያይዞ ከተነሳው ጽኑ ተቃውሞ በኋላ ብሷል፡፡ ጎበዝ፤ በአማራነት መደራጀት ጸረ-ኢትዮጵያዊ ሀሳብ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ፤ ሕወሀትን ጨምሮ ሌሎችን በዘረኝነት የሚከሱ ሰዎች፤ የለም በአማራነት እንደራጃለን ማለታቸው ግብዝነት ነው፡፡ ከዚህ ከወልቃይት ጋር በተያያዘ የተነሳውም ነገር፤ ባንድ በኩል ህወሀትን ከማጣቃት አንጻር ጥሩ ቢያስተባብርም፤ ይሄ “ወልቃይት የኛ ነው፤ ነገር ግን ትግሬዎች ወሰዱብን” የሚለው አስተሳሰብም ኢትዮጵያዊ አይደለም፡፡ ወልቃይት የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው፡፡ ከኢህአዴግ በፊት ያደግነው እንደዚያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነች፡፡ ይሄ ወልቃት የጎንደር ነው፤ ወልቃይት ያማራ ነው፤ ለአማራ ይመለስ፤ አማራው እንደአማራ ይደራጅ የሚለው አስተሳሰብ፤ ቀስ በቀስ የኢህአዴግ የፖለቲካ ቅኝት፤ ውስጣችን እየገባ እንደመጣ ያመለክታል፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን፤ አደገኛም ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የደም አማሮች፤ የማንነት ግን ኢትዮጵያዊያን፤ ይሄንን አማራው እንደአማራ ይደራጅ የሚል ሀሳብ በክፉ እንዋጋዋለን፡፡

ብሄርን መሰረት ያደረገ አከላለል ጣጣ፤

2- እንደኔ እንደኔ፤ ይሄ ብሄርን መሰረት ያደረገ አከላለል ጨርሶ መጥፋት አለበት፡፡ ወልቃይት የጎንደር መሆኑን ያጸደቅን እለት፤ አዲስ አበባንም የዚህ ብሄር ነው የሚለውን አስተሳሰብ ልናጸድቅ ነው፡፡ የወልቃይትን ጉዳይ በምንሰፍርበት ቁና፤ የፊንፊኔን (የአዲስ አበባንም) እንሰፍራለን፡፡ አዲስ አበባ፤ ከጠበበ የሚኖሩባት፤ ከሰፋም የኢትዮጵያዊያን ናት፡፡ ወልቃይትም እንደዚያው፡፡ በታሪክ ጎንደሮች አስተዳድረዋት ነበር፡፡ ነግር ግን ታሪክ ተቀየረ፡፡ ኢህአዴግ መጣና፤ አከላለሉን፤ የህዝቡን አሰፋፈርና ስብጥር ቀየረው፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ጉዳይ ይፈታ ከተባለ፤ አንዱን አሸናፊ፤ ሌላውን ተሸናፊ በሚያደርግ መልኩ መሆን የለበትም፡፡ ሀረሪ ክልል ከሆነ፤ ወልቃይት ራሱን የቻለ ክልል የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ፡፡ እንደውም እንደወልቃት፤ ራያ፤ ያሉትን አካባቢዎች፤ በግድ ጨፍልቆ ትግሬ ወይም አማራ ከማድረግ፤ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ አሁን ሸዋን ጨፍልቆ/ከፋፍሎ አማራና ኦሮሞ፤ ደቡብ ማድረግ አግባብ ነው? ሸዋ ራሱን የቻለ ክልል የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ትግራይ ራሱ ክልል ተጭኖበት እንጂ፤ ክልል መሆኑ ቀርቶ፤ ወደሌላው የኢትዮያያ አካል ተበተን ቢባል የሚመርጥ መስለኛል፡፡ ትግራይ ብቻውን ምኑን ከምን ያደርገዋል? ስለዚህ ይሄ ብሄርን፤ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነገር እንደገና እንዲከለስ ነው መጠየቅ እንጂ፤ ወልቃይት የኛ ነው፤ ራያም የኛ ነው፤ ኢህአዴጋዊና ጸረ- ኢትዮጵያዊ አካሄድ ነው፡፡

አማራውን ጎል ለማስገባት፤ እኛን ለማስመታት

3- እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ ያለፉት ጥቂት ወራት እንደሚሳዩን ከሆነ፤ አንዳንድ ሰዎች፤ ወይም ለአማራው እንታገላለን የሚሉት ወገኖች፤ በአማራው ስም ነገር እያበላሹ ነው፡፡ አማራን ጎል ለማስገባት ትግል የጀመሩ ይመስላል፡፡ አማራ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ታግሎ ታግሎ፤ በመጨረሻ፤ አማራ ሊሆን ይታገል እያሉን ነው፡፡ ከ25 አመታት በኋላ፤ አማራውን እንደአማራ የማውጣት ትግል ላይ፤ የኢህአዴግ ዓላማ ግቡን እየመታ ነው፡፡ ይሄ አንዳንዶች አማራውን እንደአማራ አደራጅተን እንታገላለን የሚሉ ሰዎች ዓላማ የተሳካ እለት፤ ያኔ ነው ኢትዮጵያ እውነተኛ ችግር ውስጥ የምትገባው፡፡ ያኔ፤ አማራው፤ እንደአማራ መደራጀቱ እውን የሆነ እለት፤ የኢህአዴግ ፖለቲካ ስሪት ላይ የማጽደቅ ማህተም የማስፈር ያህል ነው፡፡ አማራ እንዲህ ያለው የእብደት ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡
4- አማራው እንደአማራ ከተደራጀ፤ ሌሎች በብሄራቸው የተደራጁትን እንደከፋፋይና አግላይ ሊቆጥር አይችልም፡፡ በብሄር መደራጀት የሚፈልጉ በብሄር መደራጀት ክልላቸውንም በብሄር ማካካል መብታቸው ነው፡፡ እኔ በግሌ ግን በብሄር መደራጅትን አልደግፍም፡፡ እንደ ብሄር መደራጀት በባህርዩ አግላይ ነው፡፡ ገላጋይ አይደለም፡፡ ሌሎችን ያገላል፡፡ ኢትዮጵያን የፈጠረ፤ የአማራ ከሌሎቻ ጋር መጋባት፤ መናገድ፤ መዋለድ፤ እንጂ እንደአማራ መደራጀት አይደለም፡፡ አማራ አግላይነት አያምርበትም፡፡ ሌሎች በብሄር ሲደራጁ ያምርባቸዋል ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን፤ ሌሎች ብሄሮች፤ በብሄር መደራጀትን በተለያየ ምክንያት ሊመርጡት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፤ አማራው በኢትዮጵያዊነት ስም ጨፍልቆናል ብለው ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ በተወሰነ መልኩም ትክክል ነው፡፡ ብዙ አማሮች ባይዋጥላቸውም፤ የአማራው የባህል የበላይነት እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው፤ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ 25 ዓመታት በኋላም እንኳን፤ በኦሮሞ ተቃውሞ ወቅት ከሚገደሉ ወጣት ተማሪዎች ውስጥ፤ ከግማሽ የማያንሱት ስሞቻቸው የአማራ የሆነው፡፡ “ግርማ፤ ሲሳይ፤ በቀለ፤ ተገኝ፤ ቻላቸው“ ብሎ ኦሮሞ፡፡ የአማራው ባህል ምን ያህል ጠልቆ እንደገባ ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ፤ ሌሎች ብሄሮች፤ ይሄንን ለዘመናት የዘለቀ፤ የአማራውን በባህል የመጨፍለቅ ሀይል ለመቋቋም፤ በብሄር መደራጀት ያዋጣናል ቢሉ ያስኬዳል፡፡ ሌሎች በብሄር ቢደራጁ በብሄራችን ተጨቆንን ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ አማራው ምን ሆንኩ ብሎ ነው በብሄር የሚደራጀው፡፡ አማራ በብሄር መደራጀት አያምርበትም፡፡ ያልሆነውን መሆን ነው፡፡

አማራው ሲያጠቃም ሲጠቃም የኖረው በኢትዮጵያዊነት ነው

5- አማራው ሲደራጅና ሲያደራጅ የኖረው በኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ሲጠቃ የኖረውም በኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ አጥቂዎቹ ብሄሩን መዘው ሊያጠቁት ይችላሉ፡፡ ጥቃቱ ግን፤ ከአማራነቱ ይልቅ በኢትዮጵያዊነቱ የመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራ ስም ከተጠቁ ኢትዮጵያዊኖች ውስጥ፤ በርግጥም ምንያህሉ አማሮች ናቸው፤ ምን ያህሉስ የሌላ ብሄር ተወላጆች የሚለውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንደው አንድ ላይ ተጨፍልቀው አማራ ተባሉ እንጂ፤ የተጠቁት ሌሎች ብሄሮችም ናቸው፡፡ ኦባንግ እንደነገረኝ ከሆነ፤ የዛሬን አያድርገውና፤ ለጋምቤላዎች፤ ከጋምቤላ ምስራቅ የሚመጣው ሁሉ፤ ኦሮሞውንም ጨምሮ፤ አማራ ነው፡፡ ደገኛ፡፡ ስለዚህ፤ በጉራፈርዳ ወይም በመተከል፤ የብሄር ጥቃቱን ሁሉ አማራ ላይ ብቻ የተፈጸመ አስመስሎ በማቅረብ፤ ይሄ ባለፉት ጥቂት ወራት/አመታት የተጀመረው፤ የአማራ ምንትሴ፤ የአማራ ቅብርጥሴ የሚል አማራውን እናድን አካሄድ፤ በተሳሳተ ፍልስፍና ላይ የቆመ፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊ አቋም ነው፡፡ ያለበለዚያ፤ በተዘዋዋሪ መንገድ፤ የኢህአዴግን አካሄድና አሰላለፍ መደገፍ፤ ማጽደቅ ይሆናል፡፡ አማራ እንደአማራ ይደራጅ የሚለው አካሄድ ኢትዮጵያ ገደል ትግባ አይነት አዋጅ ይመስለኛል፡፡
6- የሚገርመው ነገር፤ ሌሎች የብሄር ፖለቲከኞች፤ ይሄንን የአማራነት አደረጃጀትን የሚያቀነቅኑትን ሀይሎች እንደተራማጅ ሀይሎች አይተው የተቀበሏቸው ይመስላል፡፡ ለነዚህ ሰዎች፤/ቡድኖች፤ ለብሄር አደረጃጀት ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቶ የነበረው፤ የአማራ እንደአማራ አልደራጅም፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይነት ነበር፡፡ አማራው፤ ራሱን እንደኢትዮጵያዊ ነበር የሚያደራጀው፡፡ አሁን ግን አማራ እንደአማራ ይደራጅ የሚለው አካሄድ ያንን ለመቀየር የሚታትር ይመስላል፡፡ ለምሳሌ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች፤ አማራው የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ትቶ ወደአማራ ብሄርተኝነት መዞሩ፤ በተዘዋዋሪ መንገድ የነሱን ብሄርተኝነት መቀበልና ማጠናከር አድርገው አይተውት፤ አጨብጭበው የተቀበሉት ይመስላል፡፡ አማራ እንደአማራ ከተደራጀ፤ ሌሎችም ወደብሄራቸው የመከተታቸውን ትክክለኛነት ያጠናክርላቸዋል፡፡ ለኔ ግን፤ የአማራው በአማራነት መደራጀት፤ ኢትዮጵያን ከማፍረስ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ፤ አማራው የሚያምረው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነቱን ሲገፋበት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጥላ ስር ሌሎችም ብሄሮች አሉበትና፡፡ አማራው ወደብሄር ጉያ ከገባ ግን፤ ያኔ ኢትዮጵያ ወዮልሽ፡፡
እኔ አማራ ብሆን፤ ያሳደገኝና ቀድሼ ያገለገልኩት ኦሮሞ ምን ይሉኛል

7- እኔ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ አማራ አይደለሁም፡፡ እናቴ የወሎ ቆንጆ ነች፡፡ ነበረች፡፡ አባቴ የሸዋ ጀግና፡፡ በኮንጎና በኤርትራ የተዋጋ፡፡ ከኮንጎ መልስ፤ ነጌሌ ቦረና ገቡና፤ ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ ወለዱኝ፡፡ ነጌሌ ቦረና የወሰዳቸው አማራነት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በኔም በቤተሰቦቼም ላይ ብሄራቸውን/ትውልዳቸውን/ደማቸውን መሰረት ያደረገ ጥቃት ቢደርስብን/ቢደርስባቸው፤ ያንን የሚመክትላቸው/የሚመክትልን ኢትዮጵያዊነት እንጂ፤ አማራነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም፤ ኢትዮጵያዊ እንጂ፤ አማራ ነጌሌ ቦረና ምን ይሰራል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፤ ብሄሬ በኢትዮጵያዊነት እሳት ቀልጦዋል፡፡ የአርሲን ገብስ እየበላሁ፤ የቦረናን ስጋ እየቆረጥኩ፤ የሲዳማን ቡና እየጠጣሁ ያደግኩት፤ ከነጌሌ ወዮ መድሀኔዓለም፤ ከነጌሌ ቀርሳ ኢላላ እግዚአብሄር እተጓዝኩ ያገለገልኳቸው ኦሮሞዎች፤ ምን ይሉኛል፡፡ እኔ ልጅ ተክሌ፤ እን ኢጆሌ ነጌሌ፤ ብድግ ብዬ አማራ ነኝ ብል፤ ኢጆሌ በዬቻ ምን ይለኛል፤ ገልገሎና ገባባስ ምን ይሉኛል፡፡ አባቴስ ምን ይላል፡፡ ይሄ አማራ አማራ የሚል የሰሞኑ ዘፈን፤ እኛን በሌሎች ክልልች የምንኖረውን ኢትዮጵያዊያን ለማስመታት የተጫረ ጸብ ይመስለኛል፡፡ አልተቀበልኩትም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡
ተክለሚካኤል አበበ፡፡ ቶሮንቶ፤ ትህሳስ፤ 2009/2016

(ተክለሚካኤል አበበ ሣሕለማሪያም፤ በቶሮንቶ ካናዳ የሚገኝ የህግ ባለሙያ ነው፡፡ አልፎ አልፎ፤ ቢዝነስ ሲቀዘቅዝ፤ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ይጽፋል፡፡ ስለሚሰጣቸው የህግ አገለግሎቶች ለማወቅ ይሄንን ይጎብኙ፡፡ www.tekle.info ትራምፕ የሚገፋችሁ ደግሞ ወደኛ ኑ፡፡)

4 COMMENTS

  1. ወድም ተክሌ እኔም የአንተን ሃሳብ በደብ ነው የምጋራው።የወልቃይት እና የጸለምት የማንነት ጥያቄ ድሮውንም ወያኔ ትግራይ በርሃ እያለ ትግራይን የመገንጠል አባዜ ስለነበረው ትልቅ የዘር ማጥፈት አድርጎል አሁንም በክልል ካስቀመጣቸው በሃላ ወንዶቹን በመግደል በማሳደድ ሴቶቹን የትግራይ ውንዶች በማስደፈር አካባቤውን የትግራይ ሰወች እያመጣ በማስፋር ከስደተኞች ካፕ ከሱዳን ከኬንያ ገንዘብ በመስጠት አማራወችን በማሳደድ የራሱን ትግረኛ ተናጋሪ የሆኑትን በማስፈር የአካባቤውን ሰው ለማኝ እና ስደተኛ በማድረግ ታሬክ ሊረሳው የማይችል ኢሰባዊድርጊቶች ተፈጽመዋል።

  2. This is your personal ideology.The need that the Amhara to come into one strong and unified bond is no try to weaken Ethiopia or it is not to split or disintegrate the country.We are not TPLF’S and OLF’s agenda followers.The organization that will be established by the Amhara people is to rescue and to defend the attacks and genocide on the Amhara people.There is not hidden secret or narrowish agendas.
    Some people try to degrade and criticize this huge movement without knowing the reality.It is better to watch what it happened on the Amhara people for the last 42 years by TPLF,OLF,EPLF,and their supporters..We will not wait another 50 or 100 years until we disappear from our country.There is no back bit or doubt on the Amhara people about our only flag (green,yellow,and red).No deal about our nationality and citizenship to be an Ethiopian.
    Hopefully when everyone will know the truth,everybody will be the supporter of this huge movement and it is a must to organise ourselves.It is not to be beneficiary in political aspects,rather it is beyond that and it is a question of survival as a human being.

  3. ግራ የገባህ ይመስላል እርስ ብርሰ የሚጋጭ ሀሳብ ነ ው የጻፍከው ለምሳሌ አማራ በአማራነት መደራጀት የለበትም አልከ ዝቅ ብለህ ደግሞ አንደ ኦሮሞ አይነቱ መደራጀቱ ጥሩ ነው እያልከን ነው ።
    for your information አማራ በአማራነት ተደራጅቶ ኢትዮጽያን እናፈራርሰ አላለም ካልክሰ እንደዚያ አይነት አላማ ያለው እነማን እንደሆኑ ልብህ ያውቀዋል። አማራ በኢትዮጽያ አንድነት የሚያምን ሁሉንም ብሔር በእኩልነት የሚያከብር ኩሩ ኢትዮጽያዊ ነው ታሪክ ይመሰክር እንደናተ አይነቱ በጥላቻ ተነሰቶ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የምትሞክሩት።

  4. ጤና ይስጥልኝ አቶ ሞላ ። በጭራሽ መገነጣጠልን አልደገፈም። ቢሉም ምክንያት አላቸው ኑው ለኔ የጉባኝ። የምናደርጋቸው ነገሮች ዋጋ ያስከፍሉናል ያኔ ዞሮ (ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል )እንዳይሆን ነው። የራስ ገዝ መስተዳደር ጉዳይ መጤዎች ቡሚበዙበት ሀገራት ነው የሰራው ። የብሄር ጉዳይ የኛ ብቻ ችግር አይደለም ። ሌሎች በአኗኗራቸው ወይም በሐገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ አያስገቡም ። ኢትዮጽያዊ ጉራጌ። ኢትዮጽያዊ ኦሮሞ። ሌላም ሌላም ።ለምን መሆን አቃተን ። እነ ጀርመን እነ የመን ጥንት አለመርባቱን አይተው የተውትን ብሎም የኛው ኤሪትራ ። ታዲያ ኢትዮጽያዊነትን የመሰለ የሚያኮራ አንድነት የት አለ። አቶ ከተክለሚካኤል በጣም እስማማለሁ ።

LEAVE A REPLY