ተመስገን ደሳለኝ ያለበት ታወቀ፤ ቤተሰቦቹ ሲያዩት እግሩ ያነክስ ነበር!!!

ተመስገን ደሳለኝ ያለበት ታወቀ፤ ቤተሰቦቹ ሲያዩት እግሩ ያነክስ ነበር!!!

/Ethiopia Nege/፦ በተከሰሰበት የፈጠራ ክስ የሶስት አመት ፍርድ ጨርሶ በአመክሮ የሚፈታበት ጊዜ ተከልክሎ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከ10 ቀናት ፍለጋ በኋላ ያለበት ቦታ መታወቁን ቤተሰቦቹ አስታወቁ፡፡

ላለፉት 10 ቀናት አዲስ አበባ የሚገኘውና በመጥፎነቱ የሚታወቀው ማእከላዊ እስር ቤትን ጨመሮ፤ በሸዋሮቢት፡ በቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች ውስጥ ሲፈለግ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ለረጅም ጊዜ የነበረበት ዝዋይ እስር ቤት ውስጥ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
የተመስገንን መጥፋት ተከትሎ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገጹ በየእለቱ የሚያደርጉትን ፍለጋና ውጤት ሲያሳውቅ የሰነበተ ሲሆን በዛሬው እለት ተመስገንን ለመፈለግ በየአቅጣጫው ተበታትነው ሲፈልጉ ከነበሩት ቤተሰቦቹ መካከል ወንድሙ አላምረው ደሳለኝ በዝዋይ እስር ቤት ለአምስት ደቂቃ ብቻ እንዳገኘው ለመረዳት ተችሏል።

ተመስገን በተገኘበት ሰአት እግሩ ያነክስ እንደነበርና የጨጓራ ህመሙ እያሰቃየው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በምን አይነት ሁኔታ እስከዛሬ ድረስ ለአስር ቀናት  ከቤተሰቦቹ ጋር እንዳይገናኝ የተከለከለበት አግባብ ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ሆኗል።

የተመስገንን መጥፋት ተከትሎ በርካታ መላምቶች ሲሰጡ እንደሰነበቱ የሚታወቅ ሲሆን አገዛዙ በእስረኛው ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ወደ እስር የተጣሉ ደ/ር መራራን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን አያያዝ ሁኔታ ተከትሎ ከአለም መንግስታት እና ታላላቅ አለማቀፍ ተቋማት እየደረሰበት ያለው ከፍተኛ ጫና ያስደነገጠው አገዛዙ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈታ የሚጠበቀውን ጋዜጠኛ ተመስገንን ለይቶ በማውጣት አቅጣጭ ለማስቀየር እየተጠቀመበት ነው በማለት አንዳንድ ተንታኞች ይስማማሉ።

/Ethiopia Nege December 16, 2016/

LEAVE A REPLY