ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳና ድርሰታቸው! /አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው/

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳና ድርሰታቸው! /አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው/

ፕሮፌሰር (ሊቀ ጠበብት) ጌታቸው ኃይሌ ፕሮፌሰር (ሊቀ ጠበብት) ፍቅሬ ቶሎሳ በጻፉት የተረት መጽሐፍ ላይ
የሰጡትን አስተያየት አነበብኩት፡፡ ጥሩ አስተያየት ነው የሰጡት፡፡ ከአራት አምስት ዓመታት በፊት ነው የፋና
ሬዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ጋዜጠኞች (ዘጋቢዎች) አንድ ዝግጅት በብሔራዊ ቴአትር (ተውኔት) ቤት ለፕሮፌሰር (ሊቀ
ጠበብት) ቆይ ቆይ በዚህ አጋጣሚ አንድ መልእክት ባስተላልፍስ? ከጽፉፎቸ እንደተረዳቹህት እኔ ዶክተር የሚለውን
ቃል ሊቀ ማእምራን (የአዋቂዎች አውራ፣ አለቃ) ፕሮፌሰር የሚለውን ደግም ሊቀ ጠበብት (የጠቢባን አውራ፣ አለቃ)
ብየ ተርጉሜ ነው የምጠቀመው፡፡ ምክንያቱም ማወቅ ይቀድማል መጠበብ ይከተላልና፡፡ ሳይታወቅ መጠበብ አይቻልምና፡፡

አንዳንዶች ግን ምን ሲያደርጉ አየኋቸው “በዓለማዊው ትምህርት የመጨረሻው የዕውቀት ደረጃ ፕሮፌሰር ነው፤
በመንፈሳዊው ደግሞ ሊቀ ሊቃውንት ነው ስለዚህ…” በሚል ሔዱና ፕሮፌሰር ለሚለው ቃል ሊቀ ሊቃውንት የሚል
ትርጉም እየሰጡ ለመጠቀም ሲሞክሩ አየሁ፡፡ በፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ብዙ የሚለያያቸው፣ የማያመሳስላቸው፣
የሚያቃርናቸው፣ የሚያራርቃቸው ነገሮች አሉና እባካቹህ አቻ ትርጉም በዚህ መልኩ አይሰጥምና ታረሙ ለማለት ነው፡፡
እናም እነዚያ የፋና ዘጋቢዎች ለሊቀጠበብት ፍቅሬ ቶሎሳ በብሔራዊ ተውኔት ቤት አንድ ዝግጅት እንዳዘጋጁ በሬዲዮ
(በነጋሪተ ወግ) አስታውቀው ስለነበር ዝግጅቱ ላይ ተገኘሁ፡፡ በጣም ጥቂት ሰው ነበር የተገኘው፡፡ ዝግጅቱ
ተጀመረና ሊ.ጠ. ፍቅሬ ቶሎሳና ገጣሚ ታገል ሰይፉ ግጥሞችን አቀረቡና ወደዋናው ዝግጅት ተገባ፡፡

ዋናው ጉዳይ የነበረው ሊጠ ፍቅሬ አምና “የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ!” በሚል ርእስ ስላሳተሙት በወቅቱ ግን ገና
ስላልታተመው መጽሐፍ ይዘት ማስተዋወቅ ነበርና ሊጠው በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት መኖሩን
መታዘባቸውን፣ ሕዝቡም በሚያስደንቅ የመንፈስ ከፍታ ላይ ያለ መሆኑን፣ የኪነ ጥበብ (በትክክለኛው አጠራር ሥነ
ኪን) ዘርፉም አድጎ ማግኘታቸውን ከተናገሩ በኋላ ወደ መጽሐፋቸው ይዘት በማምራት ኦሮሞና አማራ ከሦስት ሽህ
ዓመታት በፊት ከጎጃም የወጡ የአንድ አባት ልጆች መሆናቸውን ተረኩ፡፡ ሊጠ ፍቅሬ በዚህ አላበቁም በንግግራቸው
አፍ እላፊ ውስጥም ገቡና “አማራ ኢትዮጵያን ገዝቶ አያውቅም! እስኪ ጥቀሱልኝ? የትኛው ንጉሥ ነው አማራ?”
እስከማለት ደረሱ፡፡

እኔም መቸም የማይቻል ነገር የለም እንደምንም ችየ ቆየሁና ጥያቄና አስተያየት የመስጠት ዕድል ለታዳሚ ሲሰጥ
ተቀበልኩና ሊጠ ፍቅሬ “አለ!” ያሉት እድገት ከአገዛዙ ጋር የተቆራኙ ግለሰቦችና የፓርቲ ድርጅቶች እንጅ በፍጹም
የሕዝብ ወይም የሀገር አለመሆኑን፣ ሕዝብ ግን ከመቸውም ጊዜ በባሰ በጉስቁልና እየኖረ መሆኑን፣ “ሕዝቡ ከፍተኛ
የመንፈስ ከፍታ ላይ አለ!” ያሉትም ፍጹም ሐሰት እንደሆነ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ በትውልዱ ላይ
በተሠራበት ዕኩይ ተግባር ትውልዱ የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲያጣ መደረጉን፣ ማንነቱን ጠልቶና አሽቀንጥሮ ጥሎ
በባዕዳን ማንነት እንዲዋጥ መደረጉን በመጥቀስ በከፍተኛ የመንፈስ ዝቅጠት ላይ ያለ እንጅ ከፋታ ላይ ያለ
አለመሆኑን፣ ኪነ ጥበብም እንደ የቅጅ መብት ጥሰት በመሳሰሉ በአገዛዙ በተፈጸመባት ሸፍጥና ደባ ምክንያት
በሀገራችን ከነበረችበት የዕግገት ደረጃ አሽቆልቁላ በአቅሟም በጥራቷም መዝቀጧን ከተናገርኩ በኋላ “ላሳትመው
ነው!” ስለሚሉት መጽሐፋቸውም “ብሔረሰቦች በፍቅር በወንድማማችነት መንፈስ እንዲኖሩ ለማድረግ ያለዎትን ቅን
ፍላጎት ባደንቅም ተረትና ፈጠራ ታሪክ መሆን አይችልምና የተናገሩት ነገር ሁሉ ከነባራዊውና ተጨባጭ እውነትና
መረጃዎች ጋር የማይስማማና የሚጣረስ በመሆኑ፣ የሚደግፈውን አንድም ዓይነት መረጃ ያላቀረቡና የሌለዎት በመሆኑ
ይህ ተግባርዎ ከአንድ ተማርኩ ከሚል ሰው በፍጹም የማይጠበቅና ነውረኛ ሥራ ነው!” በማለት ተናገርኩ፡፡ ከዚህ
ቀደም በተለያዩ ጽሑፎቸ እንደገለጽኩት ኦሮሞ እንደ ማኅበረሰብ አሁን የምሥራቅና ደቡብ የኢትዮጵያ ድንበር ከሆነው
አልፎ የገባው የግራኝ አሕመድ ወረራና ድል የፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከ16ኛው መቶ ክ/ዘ በኋላ ነው፡፡
እርግጥ ነው ከታሪከ ነገሥት እንደምንረዳው ከ16ኛው መቶ ከ/ዘ በፊት ከ11ኛው መቶ ክ/ዘ ጀምሮ እንደነ አዛዥ
ጫላ፣ እነ ላሎ፣ እነ አጋፋሪ ቱሉ ያሉ የኦሮሞ ተወላጆች ስሞች ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡

ይሄ ማለት ግን ኦሮሞ በዚያ ዘመን አሁን ኢትዮጵያ ተብላ በምትታወቀው ምድር ነበረ ማለት አይደለም፡፡ እነ አዛዥ ጫላ፣እነ ላሎ፣ እነ
አጋፋሪ ቱሉ በዚያ ዘመን እዚህ ሊገኙ የቻሉት ኦሮሞ ከነበረበት ሞቃዲሾ አቅራቢያ እየተነሣ ለከብት ዝርፊያና
ለጦርነት ይመጣ ስለነበር በእንደዚህ ዓይነቶቹ አጋጣሚዎች ተማርከው የሚቀሩት ግለሰቦች በታማኝነታቸውና
በጉብዝናቸውም ሞገስ አግኝተው በዐፄ ምኒልክ ሁለተኛ ዘመን እንደታየው ለአዛዥነት እንዲበቁ ስለተደረጉ ነው፡፡
ታሪክን ለመናገር ያህል ይሄንን እንናገራለን እንጅ አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በረጅም ታሪኩ በማኅበራዊና
ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) መስተጋብሮች ተዋልዶ፣ ተዋሕዶ፣ ተቀላቅሎ አንድ ቅይጥ ደም የያዘ ስለሆነ
ይሄንንም እውነት እያንዳንዱ ዘሩን ወደኋላ አርዝሞ መቁጠር የቻለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በእናቱም በአባቱም በኩል
ሲቆጥር የሚደርስበት ሀቅ በመሆኑ የዘር ፖለቲካን ማቀንቀኑ ሲበዛ ከንቱነትና እውነታ ላይ አለመመሥረት፣
አመክንዮአዊ አለመሆን ከመሆኑም በላይ በሠለጠነው ዓለም ኋላቀርነቱና ጎጅነቱ ታውቆ የተጣለውን፣ የተከለከለውን
ውዳቂ አስተሳሰብ በማንሣት እንዳልበሰልን እንዳልሠለጠንን በራስ ላይ መመስከር ነውና እንተወው! በሚለው መስማማቱ
ይሻለናል እንጅ የሌለና ያልነበረን ነገር መዘባረቁ ፈጽሞ መፍትሔ አይሆንም፡፡

አቶ ይልማ ደሬሳ ስለ ኦሮሞ ጥልቅ መረዳት አላቸው ካሏቸው አባገዳዎች ያገኘሁት መረጃ ብለው “የኢትዮጵያ ታሪክ
በ16 መቶ ክ/ዘ” ከሚለው መጽሐፋቸው፣ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ
ቴዎድሮስ”፣ አባ ባሕርይ ስለ ኦሮሞ ታሪክ በጻፉት፣ ዐፄ ልብነ ድንግል በግራኝ ሲሸነፉ ለፖርቹጋሎች ባቀረቡት
የእርዳታ ጥሪ መሠረት አብሮ መጥቶ የነበረው ቤርሙዴዝ ስለ ኢትዮጵያ በጻፈው ማስታወሻ፤ እነኝህ ጸሐፍት ከፊሎቹ
ኦሮሞ ከማዳጋስካር ተነሥቶ በታንዛኒያ ኬንያን አቋርጦ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ አካል ከነበረው የዛሬው ሱማሌ
ሞቃዲሾ አጠገብ እንደሰፈረ ሲናገሩ ከፊሎቹ ደግሞ “አይ አይደለም ከሌላ ስፍራ መጥቶ ሳይሆን ያ ስፍራ ጥንትም
ጀምሮ የነበረበት ስፍራው ነው” ይላሉ፡፡ ተ/ጻድቅ መኩሪያ በመጽሐፋቸው ላይ “ኦሮሞ የገባው ከ16ኛው መቶ ክ/ዘ
በኋላ ከሆነ ከዚያ በቀደመው ዘመን እነ አዛዥ ጫላና የመሳሰሉት እንዴት እዚህ ሊገኙ ቻሉ?” ሲሉ ይጠይቁና ኦሮሞ
ከ16ኛው መቶ ክ/ዘ በፊት የገባ እንደሆነ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የተጠቀሱት ግለሰቦች እዚህ ሊገኙ የቻሉበት
ምክንያት ግን ከላይ የገለጽኩት ነው፡፡

ዛሬ ኦሮሞ ሰፍሮ ባለበት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ግራኝ ያፈረሳቸው የጥንታዊ አብያተክርስቲያናት ፍርስራሾች
የሚገኙትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ መረጃ የለም፡፡ የጥፋት ኃይሎች ሌላ የራሳቸውን ፈጠራ
የሚያወሩት ይሄንን እውነት ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን እውነታው ለጥፋት ተልእኳቸው እንቅፋት ስለሆነባቸው ነው
ሊቀበሉት የማይፈልጉትና ለማስተባበል ጥረት የሚያደርጉት፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና አስተያየቴን ከሰጠሁ በኋላ የፋና ነጋሪተወግ ዘጋቢዎችና ሊጠ ፍቅሬ ቶሎሳ ንዴት
ብስጭታቸውን መቋቋም አልቻሉም ነበር፡፡ እኔን የተለየ ፖለቲካዊ ዓላማ ይዠ ለመበጥበጥ የተገኘው አድርገው
ተናገሩ፡፡ ብቻ ከዚያ በኋላ ዝግጅቱ ሲበዛ ቀልቡ ተገፈፈ፡፡ ብዙ ሳይቀጥል አዘጋጆቹ ጋዜጠኞች ሊጠ ፍቅሬን
በነጋሪተወግ ፋና እንደሚያቀርቧቸው ተናግረው ዝግጂቱን ቋጩት፡፡

ሊጠ ፍቅሬም አወጣዋለሁ ያሉትን የተረትና የልብ ወለድ ፈጠራ መጽሐፍ ከተናገሩ ከዓመታት በኋላ አሁን ከወራት
በፊት ማለት ነው አሳትመው ለገበያ አበቁት፡፡ እስኪ የጠቀሱት መረጃ ካለ ብየ አያለሁ “የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ”
እንዲሉ ሰውየው የመሪ ራስ በላይ መጻሕፍትን ምንጭ አድርገው በማጣቀሻነት ጠቅሰዋል፡፡ እጅግ በጣም ተገረምኩ!
መሪ ራስ ሲሉ እራሳቸውን የሚጠሩ አቶ በላይ የተባሉ ሰውየ እውነቴን ነው የምላቹህ እኔ ጤነኛ እንኳን
አይመስሉኝም፡፡ ሰው የሚቃዠውን “እውነተኛ ታሪክ ነው!” በማለት ድርቅ ብሎ ካወራ እንዴት ጤነኛ ሊሆን ይችላል?
አሁን ማን ይሙትና የአቶ በላይ መጻሕፍት ማንን ማታለል ወይም ማሳመን ይችላልና ነው ይሄንን ያህል ዋጋ
ተሰጥቷቸው በሪፈረንስነት (በዋቢነት) የተጠቀሰው?

ከእኒህ ሰውዬ (አቶ በላይ) መጻሕፍት ሁለቱን ለማንበብ ሞክሬ ነበር በፍጹም በፍጹም መጨረስ አልቻልኩም!
እያቋረጥኩ ተውኳቸው፡፡ ዋጋ ሰጥቸ ለመጨረስ በመሞከሬ እራሴን እንደቂል እንድቆጥር አደረገኝ፡፡ በእርግጥ
መጽሐፎቹ ምን ያህል ብላሽ እንደሆኑ ለመታዘብም ጨርሸ ማንበብ ይኖርብኛል፡፡

እስኪ አቶ በላይ እውነታኛ ታሪክ ነው እያሉ ከጻፉት ተረታቸው አንዱን ልጥቀስላቹህ፦
ከሽዎች ዓመታት በፊት ነው አሉ “ሰንደቅዓልማ የተባለ ዓለምን የገዛ ኃያል የኢትዮጵያ ንጉሥ ነበረ…” ይሉና
አቶ በላይ “ለየሀገሩ መለያ ሰንደቅ ዓላማ የፈጠረላቸው እሱ ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማ መያዝ የተጀመረው ከዚያ በኋላ ነው” ሲሉ ረጅም ተረታቸውን ይጨርሳሉ፡፡ አቶ በላይ ሰንደቅ ዓላማ
የሚለው ቃል ከጥንት ጀምሮ የነበረ ጥንታዊ ቃል መስሏቸዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መንገድ ከጀመረች
ወዲህ የነበሩ ሰዎች ለሰንደቁና ለመስቀያው ሥያሜ ፈልገው ሁለት አመርኛ ቃላትን ፈልገው በማጣመር የፈጠሩት ቃል
መሆኑን አላወቁም፡፡ ቤተክርስቲያን ትእምርተ ኪዳን ነው የምትለው፡፡ ለመንግሥት አገልግሎት ሲሆን የተለየ ሥያሜ
መስጠት ግድ ብሎ ስለነበረ ነው ቃላት ተፈልገው ሰንደቅ ዓላማ የተባለው፡፡ አቶ በላይ ግን ሥያሜው ጥንታዊ
መሰላቸውና ይሄንን ቃል ወስደው “ሰንደቅዓልማ የሚባል ንጉሥ ስለፈጠረው ነው ሰንደቅ ዓላማ የሚባለው” ብለው ቁጭ
አሉ፡፡ የቅሌታቸው ቅሌት ደግሞ ሕፃንን እንኳን ሊያታልል የማይችለውን ተረታቸውን እውነተኛ ታሪክ ነው ብለው
እርፍ!

የእኒህ ሰውየ መጻሕፍት እንዲህ በመሳሰሉ ሐሰትነታቸው በቀላሉ ሊታወቅ በሚችል ተረቶች የተሞላ ነው፡፡ ተረታቸውን
እውነተኛ ለማስመሰል ብዙ ቦታዎች ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚተርካቸውን እውነተኛ ተረኮችና የነገሥታት ስሞች
ይቀላቅሉበታል፡፡ የዓለም ታሪክ እንደሚለው ሰንደቅ ዓላማን መጠቀም የተጀመረው ከ16ኛው መቶ ክ/ዘ በኋላ ነው፡፡
በእውነት ነው የምላቹህ ሰውየው ፍጹም ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰው አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳለ ተረት
ነው ያደረጉት፡፡ እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ራሱ እንዳይታመን ወይም አመኔታ እንዲያጣ ነው ያደረጉት፡፡ ከዚህ
የከፋ የጠላት ሥራ አለ ብትሉኝ ፈጽሞ ላምን አልችልም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ወይ ደግሞ “የጻፍናቸው መጻሕፍት
ታሪካዊ ልብወለዶች ናቸው!” ቢሉ አንድ ነገር ነበር፡፡ ይሄም ቢሆን ግን የሚበረታታ አይደለም ወይም መሆን
የለበትም፡፡ ምክንያቱም ታሪካዊ ልብወለድ ፈጠራውን ከእውነቱ ጋር እየቀላቀለ እውነቱንም ተረት ልብ ወለዱን
እውነት ስለሚያስመስለውና የመረጃ መምታታትን ስለሚፈጥር፡፡ በግሌ የታሪካዊ ልብወለድ ድርሰቶች ተቃዋሚ የሆንኩት
በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይሄ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ምን በጎ ጎን ኖሮት በምሁራኑ (Scholars) ዘንድ እንዴት
ተቀባይነት አግኝቶ በሥነጽሑፍ (Literature) ውስጥ እንዴት ቦታ ሊሰጠው እንደቻለ ራሱ በጣም ነው
የሚገርመኝ፡፡

ባጠቃላይ ማለት የምፈልገው ውሸት በቃ ውሸት ነው፡፡ ሰዎች ይመስላቸዋል እንጅ ከሐሰት ምንም የሚገኝ ፍሬ
አይኖርም፡፡ ሐሰት እውነትን ከተደበቀችበት ለማውጣት ከሆነ ይጠቅማል፡፡ እውነትን ለመቅበር ወይም የእውነትን ቦታ
ለመተካት ከሆነ ግን እንዴት ሆኖ ነው ሊጠቅም የሚችለው? ከጠቀመም ሊጠቅም የሚችለው አጥፊዎችን ብቻ ነው፡፡
የፈለገ ቢሆን ምን ብትበረታ የሐሰትን ጉልበት ዘመን ይሽረዋል፡፡ የእውነት ጉልበት ግን በዘመን አይሻርም፡፡
በጊዜውም አለጊዜውም የጸና ነው፡፡ እውነት በአየሩም በነፋሱም በአፈሩም በምኑም ተደብቃ ከአጥቂዋ መሸሸግ
ትችላለች፡፡ ሐሰት ግን ከቶ ምንም መደበቂያ የላትም፡፡ ለዚያው ቅጽበት ብትነግሥ ነው እንጅ ዕድሜ የላትም፡፡
እነ አቶ በላይና እንደ ሊጠ ፍቅሬ ያሉ ቢጤዎቻቸው ይሄንን ሊያውቁ ይገባል ነው መልእክቴ፡፡
ያለፈና ያልተዘገበ የሀገር ታሪክ በሦስት መንገዶች ሊታወቅ ሊደረስበት ይችላል፦

1. ያ ታሪክ ጥሎት ባለፈው አሻራና ማስረጃዎች፡፡
2. በቅድስና፡፡ ለምሳሌ በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሱባኤ ገብተው ከፍጥረተ
ዓለም እስከ ኅልቀተ ዓለም ያለው ምሥጢር ተገልጾላቸው መጻሕፍቱን ሁሉ በአንድምታ ትርጓሜ አብራርተው ለመተርጎም
እንደቻሉትና መልስ ላልነበራቸው ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ እንደተገኘላቸው ሁሉ ማለት ነው፡፡
3ኛ. በጥንቆላ፡፡ አጋንንትና ሰይጣናት ያለፈውን ያውቃሉና፡፡ ነገር ግን ከጠንቋይ (ከአስመሳዩ ከአታላዩ ሳይሆን
ከትክክለኛ የአጋንንት ሰይጣናት ባሪያና አገልጋይ ጠንቋይ) በአጋንንትና በሰይጣናት እገዛ የሚገኝ መረጃ ብዙ
አስተማማኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አጋንንትና ሰይጣናት እራሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ሆን ብለው መረጃን
ያዛባሉና፡፡ ሆን ብለው ያልነበረውን እንደነበረ የነበረውን እንዳልነበረ ያደርጋሉና፡፡

እናም በእነዚህ መንገዶች ያለፈንና የቆየን እውነተኛ መረጃን ማግኘት ቢቻልም 3ኛው መንገድ ግን በጠቀስኩት ችግር
ምክንያት ስለሚበረዝ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ሁኔታው ተመቸን ተብሎ አስተማማኝ የጽሑፍና የቁስ
ማስረጃና ታሪክ ያለበትን ዘመን ሁሉ እየበረዙ ታሪክን ማበላሸት መበረዝ መከለስ ፍጹም ፍጹም ይቅር የማይባል
በደል፣ የሀገር ክህደትና ኃጢአት ነውና እባካቹህ የቁም ቅዠት ውስጥ ያላቹህ ወገኖች ሆይ! ታረሙልን???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY