‎ተመስገን ደሳለኝ በጠና ታሞ ሆስፒታል መግባቱ ተገለጸ!

‎ተመስገን ደሳለኝ በጠና ታሞ ሆስፒታል መግባቱ ተገለጸ!

ከ9 ቀናት ፍለጋ በኋላ ለ 3 ደቂቃ ብቻ በወንድሙ ተጎብኝቶ በድጋሚ ደብዛው ጠፍቶ የነበረው እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጽኑ ታሞ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ታወቀ፡፡

ተመስገን በዝዋይ እስር ቤት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በልዩ ልዩ ህመሞች ይሰቃይ እንደነበር አለም አቀፍ ተቋማት ሲያሳስቡ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ ወደ ዝዋይ ባቱ ሆስፒታል በአስቸኳይ በቃሬዛ ተጭኖ የተወሰደበት የህመም ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡

በሆስፒታሉ አካባቢ የተገኙ ምንጮች ለተመስገን ደሳለኝ ቤተሰቦች እንዳስረዱት ፖሊሶች ጋዜጠኛ ተመስገንን በሆስፒታሉ ዙሪያ ሰው እንዳያየው ይከላከሉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በቤተሰቦቹ እና በታላላቅ አለም አቀፍ ተቋማት ቅርብ ክትትል የሚደረግለት ጋዜጠኛ ተመስገን ከዘጠኝ ቀናት ፍለጋ በኋላ በዝዋይ እስር ቤት ለሶስት ደቂቃ ብቻ በወንድሙ የታየ ቢሆንም በድጋሚ ቤተስብ ጋር እንዳይገናኝ ተደርጎ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን የተመስገን ወንድም አላምረው ደሳለኝ በዛቺው አጭር ጉብኝቱ ወቅት ወንድሙ ጋዜጠኛ ተመስገን መራመድ እስኪያቅተው ያነክስ እንደነበር መናገሩ ይታወሳል፡፡

የተመስገንን ሁኔታ በፌስ ቡክ ገጹ በመግለጽ የሚታወቀው የተመስገን ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ የዛሬን ቀን በተመለከተ የዝዋይ እስር ቤት አስተዳዳሪዎችና የዛሬ ተረኛ የሽፍት መሪ ሻለቃ ንጉሴ እንዲሁም እስከዛሬ በተመስገን ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው ነገር ሁሉ መንግስት ሃላፊነቱን ይወስዳል ሲል ገልጿል፡፡

LEAVE A REPLY