የተከበሩ፣ የእርቅና የሰላም ሰው ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም /ፍቅር ወርቁ/

የተከበሩ፣ የእርቅና የሰላም ሰው ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም /ፍቅር ወርቁ/

እንኳን ለጌታችንና ለመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት/የገና በዓል በሰላምና በጤና አደርስዎ! እንዲሁም ወንድማዊ የአክብሮት ሰላምታዬ ባሉበት ይድረስዎ!

በየሳምንቱ ጠለቅና ሰፋ ያለ የትንታኔ ጽሑፍዎ/Commentary ይደርሰኛል። እንዲሁም በውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ጊዜያት፣ በበርካታ ወቅታዊ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚጽፏቸውን ጽሑፍዎችዎንም በሚገባ እከታተላለሁ። ለሀገረዎ ያለዎትን እንደ እቶን እሳት የሚንቀለቀል ቅናትዎን፣ (መጽሐፍ፣ “ቅንዓተ ቤትከ በልአኒ፤ የቤትህ ቅናት በላኝ።”) እንዲል። የኢትዮጵያን አምላክ የሚማፀን “ተስፋንና ፍጻሜን” የተሞላ ራእይዎን እና ትጋትዎትን፣ መጽሐፋችን/አይሁዳዊው ንጉሥ፣ ጠቢቡ ሰለሞን፣ (“ትጋት ለሰው የከበረ ሀብት ነው።”) እንዳለ። በእጅጉ አደንቃለሁ፣ አከብራለሁም።

የተወደዱ ፕ/ር የምዕራባውያኑን የChristmas እና የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል በማድረግ ለሀገርዎና ለወገንዎ ያለዎትን ሕልም፣ ራእይ፣ ምኝዎትዎንና የመልካም ምኞት መግለጫዎን ካነበብኩ በኋላ ይህችን አጠር ያለች ጦማር ላደረሰዎ ወደድሁ።

ምዕራባውያኑ “የገና/የልደት በዓል -It is the holiday of Gifts and Forgiveness/የፍቅር ስጦታ መለዋወጫና የይቅርታ በዓል፤” እንደሆነ የሚያስረግጥ የቆየ ተወዳጅ ብሂል አላቸው። እንደ ሃይማኖት ሊቃውንት አስተምህሮም የገና በዓል – በሀጢአትና በአለመታዘዝ ጠንቅ ከፈጣሪ፣ ከተፈጥሮ፣ ከራሱ፣ ከሌላው ወንድሙ/ወገኑ የተጣላው፣ የተለያየው የሰው ልጅ ከፈጣሪው፣ ከተፈጥሮ፣ ከመላእክት፣ ከወገኑ ጋር ዕርቀ-ሰላም አውርዶና በአንድነት ሆኖ በፍጹም ደስታ እያሸበሸበ፤

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ ሃሌ ሉያ!” በማለት ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት/አብሮነት የዘመሩበት፣ ያዜሙበት፣ ልዩ የሆነ ሰማያዊ ቅኔን የተቀኙበት – ታላቅ የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታ በዓል ነው። ገና ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ – ከኢየሩሳሌም ቤተልሔም እስከ ሩቅ ምሥራቅ፣ ጃፓንና ቻይና፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ድረስ በታላቅ ሃይማኖታዊ ደማቅ ሥነ ሥርዓትና በብዙ ተናፋቂ ባህላዊ ዝግጅቶች የሚከበር በዓል ነው።

ገና የሰላም፣ የዕርቅ በዓል ነው … የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱትም ምዕራባውያን 50 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ከሞቱበትና ዓለማችንን ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከዳረጋት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በገና በዓል ሰሞን ተግባራዊ የሚሆን አንድ “የሰላም ስምምነት ሕግ” አውጥተው ነበር። ይሄውም በጠላትነትና በጦርነት ውስጥ ያሉ የባላንጣ ሀገራት ወታደሮች – የገና በዓል ዕለትና ሰሞን ስለ ሰላም ሲሉ ነጭ ርግብ ይለቃሉ፣ ስጦታ ይለዋወጣሉ፣ ጠላትነታቸውን ለጊዜውም ቢሆን ረስተው በገና በዓል ሰሞን ሰላምታ ይለዋወጣሉ። በዚህ ጦርነት፣ ጠላትነት በገነነበት የጥላቻ አየር ውስጥ ሽው የሚል የዕርቀ-ሰላም ያለህ የሰላም ናፍቆትን “the Christmas Truce” ሲሉ ይጠሩታል።

የተከበሩ ፕ/ር አለማሪያም ነገሬን አስረዘምኩት መሰለኝ። ጦማሬን ለዛሬ በዚህ ላጠናቅቅ። ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም በተበሰረበት የጌታችንና የመድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መታሰቢያ ለዓለም፣ ለሰው ልጆች ሁሉ፣ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን በመመኘት ልሰናበት።

ሰላም! ሻሎም!

LEAVE A REPLY