የምንታገለው ማንን ነው? /የጎንደር ህብረት/

የምንታገለው ማንን ነው? /የጎንደር ህብረት/

ያ! የጥንቱ የጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ የሚታዎቀው፤ አገሩን ወራሪ፤ ክብሩን ደፋሪ ፈታኝ ነገር ሲያጋጥመው፤ በአንድነት ተባብሮ፤ በፍቅር ተሳስሮ፤ የአገርን ጠላት ተከላክሎ፤ ነፃነቱን ጠብቆ፤ የማንነቱ መኩሪያ የሆነችውን አገራችን ለቀጣይ ትውልድ በማስተላለፍ ነበር። ትውልድ እና አገር በየዘመናቱ ፈታኝ ነገሮች እንደሚያጋጥሙት ሁሉ፤ ዛሬም አገራችንን የወያኔው ከፋፋይ ቡድን፤ በጎሳ ፖለቲካ ሠንጎ ይዞ ሕዝባችንን፤ እርስ በእርሱ እያጫረሰ ባለበት አሳፋሪና አሳዛኝ ወቅት ላይ ነን።

በመሆኑም፤ ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ለሕዝባችን ነፃነት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ አመጣለሁ ብሎ በእውነት፤ የሚታግል ኃይል ሁሉ፤ የትግል ትኩረቱ ማድረግ ያለበት፤ የአንድነት እና የዲሞክራሲ ወቅታዊ ጠላታችን በሆነው፤ ወያኔ ላይ ብቻ ነው ብለን እናምናለን። በዘመናችን፤ በማወቅም ይሁን፤ ባለማወቅ፤ አላስፈላጊና ጎጂ የሆነ አካሄድ ማራመድ፤ የተለመደ ሆኗል። ይኸውም፤ አብዛኛው በተቀዋሚ ሥም፤ ተደራጀሁ የሚል ስብሥብ፤ ሁሉ እየታገል ያለው፤ እታገለዋለሁ የሚለውን ተቋም ወይም ግለሰብ ሳይሆን፤ ለቆመለት ዓላማ የጀርባ አጥንት ሊሆን የሚገባውን አካል ነው።

በእኛ ዕምነት፤ በተቃዋሚ ስም ተሰባስበው፤ በአፍራሽ ተግባር ተሰማርተው፤ የእውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅቶችን እና ስብስቦችን፤ ቀን ከሌት፤ ጠላታችን ነው ብለው በቃላት ካስቀመጡት ወያኔ በላይ፤ የጥቃት ተግባር፤ እየፈጸሙ ያሉ በሙሉ፤ ሚሥጢራዊ የሆነ አፍራሽ ተልዕኮ ያነገቡ፤ አሳሳች ፖለቲከኞች ወይም በወያኔ ተቆራጭ የተመደበላቸው ስብስቦች ብቻ ናቸው።

ዛሬ ወያኔ በገበሬው፣ በነጋዴ፣ በተማሪው፣ በአስተማሪውና በሠርቶ አደሩ፤ በጠቅላላም በኢትዮጵያ ሕዝብ ተተፍቶና፤ ተወጥሮ በተያዘበት ወቅት የተቃዋሚውን ጎራ የሚቦረቡርና፤ የራሱን ድርጅት ጥቅም አንቆ በመያዝ፤ ችግራችንን በጋራ አንዳናሳጥር የሚጥር ስብስብ፤ ጤናማ ዓላማ ያለው ነው፤ ብሎ ማሳብ እጅግ አሥቸጋሪ ነው። ማንም ተቃዋሚ ስለራሱ ዓላማ ማስረዳትና በተግባር ከሌሎች ልቆ መገኘትና የሕዝባችን ሰቆቃ ማስወገድ እንጂ፤ ተቃዋሚን መቃወም ጥቅሙም ይሁን ድሉ፤ የሕዝባችን ጠላት ለሆነው ወያኔ እንዲያዘነብል፣ ወይም የሕዝባችን የሰቆቃ ኑሮ እንዲራዘም ድጋፍ ማድረግ ብቻ ነው። ይህ ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው የሚያደርጉት መጠላለፍ፤ የወያኔን እድሜ ያራዝማል ፤ የሕዝባችንም ሰቆቃ ያባብሰዋል እንጅ ለቆምንለት ነፃነት እና ዲሞክርሲ ግብ፤ ምንም ጠቀሜታ የለውም። ይህንም ክፍተት ተጥቅሞ፤ ወያኔ መሀል ገብቶ እሳቱን እያቀጣጠለ እንደሆነ መገመት ይቻላል “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ነውና።

ከዚህ በላይ ላስቀመጥናቸው፤ ቁምነግሮቻችን መነሻዎች የሆንኑን፤ ጉዳዮች ለአብነት እንጥቀስ። ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ፤ በጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ላይ እና በድርጅቱ አባላት ላይ እየተደረገ ያለው ተጨባጭነት የሌለው የስም ማጥፋት ዘመቻና የጥፋት ተንኮል፤ እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ፤ በጣም የወረድ፤ ከኢትዮጵያዊነት ጨዋነት በታች የዘቀጠ ተግባር ሲፈጸም ተመልክተናል። ይህ አይነት አካሄድ እየጠቀመ ያለው፤ አገራችን እያፈረሰ ያለውን ወያኔን እንጅ፤ የተቃዋሚውን ጎራ አይደለም። ወያኔን እየታገልኩ ነው ከሚል አንድ ስብስብም ሆነ ግለሰብ እንዲህ አይነት ውኃ የማይቋጥር ውዥንብር መንዛት፤ የራስን ትንሽነት በግለፅ የሚያጋልጥ ቢሆን እንጂ፤ ለእውነተኛ ታጋይ ድርጅቶችም ይሁን ግለሰቦች፤ ብሎም ለጨዋ ኢትዮጵያውያን፤ ቅንጣት ያክል ጉዳት እንደማያመጣ በድፍረት ልንገልጽ እንወዳለን።

ከዚህ በፊት ደጋግመን እንዳስረዳነው፤ ጎንደር ህብረት የተቋቋመው፤ በሶሥት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው።

1. ወያኔ የለም መሬት ጥቅሙን ለማሟላት፤ የጎንደርን መሬት ወደ ትግራይ ከልሎ፤ የአካባቢ ኗሪ ወገኖቻችንን ያለ ርህራሄ በግፍ በመጨፍጨፍ ለ40 ዓመት በመቀጠሉ፤

2. ተቃዋሚዎችን እንደልማዷ ልታስተናግድ ትችላለች በሚል፤ ለማታለያ እና ለሥልጣን ማራዘሚያ አግቦ ይሆን ዘንድ፤ የጎንደር/ ኢትዮጵያን ለም መሬት ለሱዳን ቆርሶ የመሥጠቱን እና የአገር ክህደቱን፤ በእርግጠኝነት በማየታችን፤

3. እኒህ በተራ ቁ. 1 እና 2 የተንኮል ጥንሥሶችን ለማሳካት ደግሞ፤ ወያኔ ሲፈጠር ጀምሮ፤ ጠላቴ አማራ፤ ነው የሚለውን የዘር ማጥፋት፤ ቅዥት፤ ይሳካለት ዘንድ፤ በሰላም እና በአብሮነት ታሪክ ሰርቶ ዘመናት የተሻገረውን የጎንደር ሕዝብ፤ አሁንም ለመሬቱ እና ለክብሩ በጋራ ተባብሮ እንዳይታገለው፤ እርስ በእርስ በዘር ከፋፍሎ ለማጫረስ፤ የዘር እሳት ሲለኩስ በማየታችን፤ ነው።

እኒህ ከላይ የጠቀስናቸው ሦስት መሰረታዊ ችግሮች፤ አካባቢያዊ ብቻ አይደሉም። በጥቅሉ ሲታዩ አገር አቀፍ፤ ኢትዮጵያዊ ክብርን እና የነፃነት ማንነታችንን የሚፈታተኑ፤ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተባብረን ልንታገላቸው የሚገቡ ችግሮቻችን ናቸው። በክልሉ መደራጀታችንም፤ ይበልጥ ለብሔራዊ ትግሉ፤ ቀደሚ መረጃ እና እግዛ ይረዳል በሚል ህሳቤ ነው።

ታዲያ የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ዓላማው ይህ መሆኑን እየደጋገምን እያስረዳን ባለንበት ወቅት፤ ተጨባጭነት የሌለው አሉባልታ ወሬ በመዝራት፤ ራስን በጠነሰሱት ተንኮል ለጊዜው ያረካ ካልሆነ በቀር፤ በማንኛውም መሥፈረት ተቀባይነት የለውም። አንድ ነገር ግን ለማረጋገጥ የምንወደው፤ ጎንደር ሕብረት የኢትዮጵያ አንድነት፤ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ፤ የሕዝባችን ፍላጎትና ምኞት፤ ተከትሎ የተመሠረተ በመሆኑ በብዙኃን መገናኛ የሚሰራጭ ተራ የጥላቻ ዘመቻ ሊፈርስ ወይም መሰረቱ ሊነቃነቅ ፈፅሞ አይችልም። ትግላችን ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ታሪካዊነታችንም፤ እንደ ፋሲል ግንብ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ለዘለዓለም ህያው ሆኖ ይኖራል።

በመሆኑም፤ የወያኔን አምባ ገነን መንግሥት እየታገልን ነው የምትሉ ሁሉ ትግሉን ዳር ማድረስ የምንችለው፤ ጥቃቅን ልዩነታችንን አቻችለን በህብረት፤ ለአገራችን አንድነት፤ ለዲሞክራሲያዊ ነፃነታችን ስንታገል እንጅ፤ ተመሳሣይ የዴሞክራሲ ጥያቄ አንስተው የሚታገሉትን ድርጅቶችን፤ ሰርጅቶ ለመጣል መጣር አይደለም። መጠላለፍ ደግሞ፤ መጀመሪያ እሚጥለው፤ ጠላፊውን ነው። መነጋገርና መደጋገፍ የጎንደር ህብረት የትግል ዓለማ መሆኑን እንድትረዱ ያስፈልጋል።

ስለሆነም ከዚህ በፊት እንዳሳወቅነው ሁሉ ወያኔን ለመጣልና፤ ኢትዮጵያን በዴሞክራሲያዊ አንድነት አስተሳስርን ወደፊት ለመቀጠል የምንችለው፤ ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች ተባብረው ሲታገሉ ብቻ ነው ብለን እናምናለን። ስለዚህ የተቃዋሚ ኃይሎች ሕብረት ይዋል ይደር የሚባል ጥያቂ ባለመሆኑ፤ ዛሬም እንደተለመደው፤ ለህብረት ትግል ጥሪያችን እናቀርባለን!!

ድል ለሰፊው ሕዝብ!
ጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት

LEAVE A REPLY