እንግድነት ንጉሥነት /ያሬድ ሹመቴ/

እንግድነት ንጉሥነት /ያሬድ ሹመቴ/

አቶ ወርቅ አገኘሁ ገ/ማሪያም ይባላሉ። የተወለዱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በተወለዱበት ቤት ውስጥ ነው- አንጎለላ እንቁላል ኮሶ። በደጃዝማች ከበደ ተሰማ አምካኝነት- የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የትውልድ ቤት ለስማቸው መታሰቢያ የሚሆን ክሊኒክ እንዲሰራበት እነ ጋሽ ወርቅዬ ቤቱን ለቀው ቅያሪ ቤት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ወቅቱም ገና ደርግ ስልጣን የያዘበት ግዜ ነበር።

በታሪክ እንደሚታወቀው ደርግ በርካታ የንጉሱን መኳንንት እና ሚንስትሮች በእስር እንዲሁም በሞት ግድያ ሲያሰናብት ሙሉ ክብራቸውን ሳያጡ፥ ከቤተ መንግስቱም ሳይርቁ፥ እንዲተርፉ ያድረጋቸው ደጃዝማች ከበደ ተሰማን ነበር ይባላል። በዚህም ምክንያት ደጃዝማቹ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የድብቅ አባት ናቸው እየተባለ ወሬ ይናፈስ ነበር።

ታዲያ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በደርግ መንግስት ዘመን ካደረጓቸው በርካታ አስተዋጽዖዎች መካከል የአዲስ አበባው የታዕካ ነገስት ባዕታ ለማሪያም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ድርጅትን እና አዳሪ ትምህርት ቤት ማቋቋም አንዱ ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር አንጎለላ ውስጥ ለስማቸው መታሰቢያ የሚሆን ለአካባቢውም ነዋሪ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ክሊኒክ መትከል ነበር።

ይህ ክሊኒክ እስከ አሁኑ መንግስት መጀመሪያ ድረስ ጥሩ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በአሁን ሰዓት አገልግሎት መስጠት ማቋረጡን እና የክሊኒኩ ክፍሎችም እየተሰነጣጠቁ ከፍተኛ አደጋ እየደረሱባቸው መሆኑን አቶ ወርቃገኘው ይናገራሉ።

“በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስም የተሰየመውን ክሊኒክ ለምን ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንደተሳናቸው ግራ ይገባኛል። ቀደም ሲል፥ ለምን ተዘጋ ብለን ትንጠይቃቸው የሚሰጡን መልስ ‘ከ25 ሺህ ነዋሪ በታይ ባለበት ቦታ ክሊኒክ አያስፈልግም’ የሚል ነበር። አሁን ደሞ ይህነን ቦታ ትተው ተአንጎለላ ትምህርት ቤቱ (ከ3ኪ.ሜ የማይርቅ ቦታ) አካባቢ ሌላ ክሊኒክ ለመስራት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። አሁን እስኪ ልብ በሉ፥ ይኼ ታሪካዊ ክሊኒክ ተዚህ እያለ እንደው ስማቸው እንዳይነሳ ታልፈለጉ በቀር እዚያ ቦታ ምን አስኬዳቸው” ሲሉ ትዝብታቸውን ይናገራሉ።

የጉዞ ዓድዋ 4 ተጓዦችን ይዘን በአንጎለላ የነበረውን ጉብኝት ጨርሰን። ለዓድዋው ስመ ጥር ጀግና ፊታውራሪ ገበየው አፅም የክብር ሰላምታ ሰጥተን እና ደማቅ አቀባበል ቋጭተን ወደ ማረፊያችን ያመራነው እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም በአቶ ወርቅ አገኘሁ ቤት ውስጥ ነው።

አቶ ወርቃገኘው ንጉስ የመጣ ያህል የቆዳ ለምዳቸውን ለብሰው ሸብ ረብ ሲሉ። ካህን የመጣ ያህል አደግድገው መብሉንም መጠጡንም ሲያስተናግዱ ላየ፥ በታሪካችን ሁሌም በኩራት የሚነገረው የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችን ጫፉ ይኼኛው ሳይሆን አይቀርም ሊል ግድ ነው።

መኝታውን ትቶ መሬት የሚተኛ፥ ወርጄ እግር ካላጠብኩ የሚል፥ እናንተ ጠግባቹ ታትበሉ ወንበርም አልይዝ እህልም ታፌ አይገባ የሚል፥ ወተት እንደ ጠላ ‘ድገሙ ደጋግሙ’ ብሎ የሚያስጨንቅ፥ የታረደው በግ ተበልቶ ሳያልቅ ከቤቴ አትወጡም የሚል፥ በየደቂቃው ‘እንደው ታልዘጋጅ መጣችሁብኝ’ ብሎ ባደረገው የማይረካ የትህትና ጥግ ሰው ዛሬም ድረስ በሀገራችን አለ።

ጋሽ ወርቅዬ ቤት በሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀናችንን ጨምረን ለሁለት ቀናት በድሎትና በምቾት የመፃህፍት ናባባችንን ተያይዘነው ስናሳልፍ፥ ከመቶ ሀያ አንድ አመት በፊት የነበሩ ምርጥ ኢትዮጵያውያንን በመንፈስ ተገናኘናቸው።

ጉዞው ቀጥሏል። ሌላም ሌላም ደጋግ ሰዎች ጋር እንግድነት ንጉስነት ነውና ኢትዮጵያዊነታችንን እየወደድነው እየናፈቅናው እያከበርነው ቀጥለናል።

አቶ ወርቅዬን መርቄያለሁ። ሀሳባችሁ ይሳካ! ቤታችሁ አይጉደል! አመት አመት አይለየን! ጤናችሁን ይጠብቅልን! የዳግማዊ አጤ ምኒልክን መታሰቢያ ክሊኒክ በቦታው መልሶ ይትከልልን!!

አሜን!!
#ጉዞ_ዓድዋ
#ይከበር_ይዘከር_ለዘላለም!!!

LEAVE A REPLY