ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት መሄድ /ይገረም አለሙ/

ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት መሄድ /ይገረም አለሙ/

የመንገዳችን ርዝመት የድላችን ህልምነት ነበር የመነጋገሪያ ርእሰ ጉዳያችን፣ብዙ አይደለንም አጋጣሚ ያገናኘን ሁለት ሰዎች እንጂ፤ተቀራርቦ ለማውራት ብዙ ትውውቅ አላስፈለገንም፣በሁለታችንም ውስጥ ያለው የቁጭትና የብሽቀት ስሜት ከመቅጽበት ተናቦ ለመተዋወቂያ የሚሆን መንደርደሪያ ጨዋታም ሳያስፈልገን ነው ዘው ብለን በወያኔ ሀያ አምሰት አመታት ለመገዛት ስላበቃን ምንነትና እንዴትነት ማውጋት የጀመርነው፡፡ እኝህ ድንገቴ ያገናኘን ወዳጄ ችግሩ የዛሬ ሳይሆን ስር የሰደደ ትውልድ የተሻገረ መሆኑን ገልጸው  እንቆቅልሻችንን  በምሳሌ ሲያስረዱኝ በአይነ ልቦና ሁለት ቦታ ሄድኩኝ፡፡ አንዱ ጌትነት እንየው እኛው ነን የሚለውን ግጥሙን በመድረክ  ሲያነብ፤ ሁለተኛው  ኢሳትና ቭዢን ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት አንድ መድረክ ላይ አቶ ዳኛቸው ተሾመ ሲናገሩ ታዩኝ፡፡

የጌትነትን ልተወውና   ብዙም  ሰው ከቁብ ካልቆጠረው የአቶ ዳኛቸው ንግግር  በልቤ ውስጥ ታትማ የቀረች አንድ አንቀጽ ልጥቀስ፡፡ “  ችግሩ እኛ ራሳችን በራሳችን መሞላታችን ከራሳችን በላይ የሆነ እሞትለታለሁ ለዚህ ብዬ እኔ ልዋረድና የቆምኩለት ሀሳብ ይቀጥል የምንለው አንዳችም ነገር ስለሌለን ነው  ዛሬ የምንገኝበት ውርድት ውስጥ ያለነው ፡፡” አዎ ድፍረቱ ኖሮ በፖለቲካው መቆመሩ፣ በታሪክ ማደናገሩ መነገዱ ቆሞ በትክክል ራስን ማየትና እንደ አቶ ዳኛቸው በድፍረትና በሀቅ መናገር ቢቻል የችግራችን ችግሮቹ እኛው ራሳችን ነን፡፡ ወደ ፊት ጋት የማንራመድ  አስርም ይሁን መቶ አመት የኋልዮሽ እያየን አካኪ ዘረፍ ለማለት ወደር በራሳችን ምህዋር ሰንሽከረከር ሶስት ትውልድ የሞላን ለጎዞአችን እንቅፋቶቹ እኛው ነን፣ ወዳጄ አገዛዝ የሚፈራረቅብንና የዴሞክራሲ ባይተዋሮች የሆንበትን ምክንያት ከመጽኃፍ ቅዱስ እያጣቀሱ ሊነግሩኝ ሲጀምሩ የሀይማኖት ሰባኪ አይደለሁም አሉኝ፣ችግር የለውም አልኩዋቸው፤ ለእኔ የኢትዮጵያውያን ነገር በመጽኃፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው እስራኤሎች ከግብጽ ወደ ተስፋዋ ምድር ካደረጉት ጉዞ ጋር  ይመሳሰልብኛል በማለት ወጋቸውን ቀጠሉ፡፡ እግዚአብሄር አምላክ የመረጣቸውን እስራኤላውያንን  በግብጽ መኖራቸው አብቅቶ ወደ ከነአን እንዲገቡ ነገራቸው፤ ሙሴንም መሪ አድርጎ ሰጣቸው፣ ቀይ ባህርንም ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ እስራኤላውያኑ ግን የኖሩባትን ግብጽ ያውቃሉና ስለሚሄዱበት ሀገር ግን የሚያውቁት ነገር አልነበረምና የማያውቁት ሀገር ሆኖባቸው ፤በፈጣሪ ላይ ያለቸው እምነትም የጸና አልነበረምና  እግራቸው ወደ ፊት ቢራመድም ልባቸው  ወደ ኋላ ወደሚያውቋት በግዞት ወደ ነበሩባት ሀገር  ግብጽ ነበር፡፡

ለምን ከግብጽ አወጣችሁን ብለውም  ፈጣሪን አማረሩት ሙሴንም በእጅጉ አስቸገሩት፡፡ ይህን ያየ ፈጣሪም እነዚህ ትእዛዜን አልተቀበሉም ከንአን  ቢደርሱም ቃሌን አይጠብቁም አለና ቃሉ በእነርሱ ሳይሆን በልጆቻቸው እንዲፈጸም ወስኖ እነርሱ እስራኤል እንዳይገቡ መንገዱን አረዘመባቸው፡፡  ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት ሲጓዙ የ11 ቀኑ መንገድ አርባ አመት ፈጀባቸው፡፡  እስራኤል የደረሱትም ከግብጽ የተነሱት ሳይሆኑ ልጆቻቸው ሆኑ፡ አሉና ከእኛ ነገር ጋር እያዘመዱ አወጉኝ፡፡ ከርሳቸው ተለይቼ ቤቴ እንደደርስሁ መጽኃፍ ቅዱስ  ገለጥሁ እንዲህ የሚል ቃልም አነበብሁ፤ “..  ሙሴንም በግብጽ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን፣ከግብጽ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው፣ በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናል ተወን፣ ለግብጻውያን እንገዛ ብለን በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን አሉት፡፡ (ዘጸአት 14/11-12) “ለምርኮ ይሆናሉ ያላችኋቸው ህጻናቶቻቸሁ ዛሬ መልካሙን ከክፉ መለት የማይችሉ ልጆቻሁ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፣ምድሪቱንም ለእነርሱ እሰጣለሁ፣ይወርሱአታልም፣ እናንተ ግን በኤርትራ ባህር መንገድ ወደ ምድር በዳ ሂዱ፡፡ ( ዘዳግም 1/39-40) ሰውየው ያዩበት ያነጻጸሩበት መንገድ አስገረመኝ፡፡

እውነት ነው የኢትዮጵያውያን ነገር እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንዶቹ  ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት  ነው የምንጓዘው/የምንታገለው  ሲሉ ይሰማሉ፤አንዳንዶቹ ደግሞ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ነው የምንፈልገው ይላሉ፡ (ማን ሰርቶ እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ ባይታወቅም) ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተጣሉትን ትተን ሌሎቹ ብናይ ምንም ይበሉ ምን ቢያንስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመፈልግ ይመሳሰላሉ፡፡  ነገር ግን ከእነዚህ አብዛኞቹ የሚናገሩት የሚጽፉትም ሆነ የሚሰሩት ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚያስጉዝ አይደለም፡፡  በአፈ ታሪክ ሲነገር  የሰሙትን ወይንም   በኢትዮጵያ በሚቀኑ  ሰዎች ተጽፎ ያነበቡትን የአባት አያታቻውን ዘመን ወደ ኋላ እያሰቡ መሻታቸው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ሙግትን ነው ምርጫቸውም ስራቸውም ያደረጉት፡፡ ወደ ኋላ ማየቱ ከትናንት ተምሮ ወደ ፊት ለመረማጃ መንገድ መቀየሻ ቢሆን ክፋት አልነበረውም ክፋቱ ለዛሬም በማይበጅ ለነገም ምንም ፋይዳ በሌለው ሁኔታ  ልዩነት ለመስበክ፣ለበቀል ለማነሳሳት በጥቅሉ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርኣት አንዳትሸጋገር እንቅፋት  ለመፍጠር እየዋለ መሆኑ ነው፡፡

የሚናገሩ የሚጽፉትም ሆነ ታሪክ ብለው የሚጠቅሱት እውነት እንዳልሆነ በመረጃና ማስረጃ ሲነገራቸው ደግሞ በእርዳ ተራዳ ጩኸት ባልትገራ ብእርና አንደበት አገር ይቃጠል ይላሉ፡፡  ይህም እንደ በጎ ነገር ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ርምጃችንም ሆነ እያታችን ሰራችንም ሆነ ሀሳባችን ወደ ፊት ላይ ማተኮር ባለመቻሉ እነሆ ለእስራኤላውያን  የ11 ቀኑ ጉዞ 40 አመት እንደፈጀባቸው እኛም የዴሞክራሲ ጉዞ ከጀመርን ሶስት ትውልድ ደርሷል፡፡ ምን አልባት ጉዞውን ሀ ብሎ የጀመረው ትውልድ የፈጣሪን መንገድ ምሪት አልቀበል ያለ፣ ለቃሉም መገዛት ያልቻለ ሆኖ  እናንተ ቀርቶ የልጅ ልጆቻችሁ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን አያዩም ፣ቃሌ ግን ይፈጸማል ከሶስተኛው ትውልድ በኋላ ተብለን  ይሆን! ከአብዛኛው ፖለቲከኛ ነኝ ባይ የምናይ የምንሰማው በቃልም በግብርም ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መድረሻ  ዘዴውን መሄጃ መንገዱን ለጉዞ የሚያስፈልገውን ከማሰብ ከመዘጋጀትና  ወደዛው ከማምራት ይልቅ ትናንትም ሆነ ዛሬ የኋልዮሽ እይታን ነው፡፡

ወደ ፊት ማየቱ ቀርቶ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማለምና ለዛ የሚቻለውን ማድረግ ቀርቶ  የአያቶቻችንን ዘመን እያነሱ መዋቀስ መካሰስ ለማንና ለምን እንደሚበጅ የሚያውቁት ፈጻሚዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ አድራጎት ውጪ ባለው ሰው እምነት ግን  በእገሌ የሥልጣን ዘመን ይህ ሆኗል በዛኛው እንዲህ ተደርጓል እያሉ  ሆኖ እንኳን ቢሆን አድራጊዎቹ በሌሉበት ዛሬ መወነጃጀል ወደ ፊት ለመጓዝ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እኛ ባንሆን ልጆቻችን ይደርሱባት ዘንድ ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚደረገውን ጉዞ እንደ እስራኤላውያን  የግብጽ ከንአን ጉዞ  ያስረዝመዋል እንጂ፡፡ እስራኤሎች ፈጣሪያቸውን ያማረሩት መሪያቸውን ሙሴንም ያስቸገሩትና  ልጆቻችሁ እንጂ እናንተ እየሩሳሌም አትገቡም ለመባል የበቁት ከማናውቃት እየሩሳሌም የምናውቃት በግዞት የምንኖርባት ግብጽ ትሻለናች ብለው ወደ ፊት እየሄዱ ወደ ኋላ በማየታቸው ነው፡፡

ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን መሆኑ ነው፡፡ የእኛ ግን ከዚህ ግራ ነው፡፡ወደ ኋላ የምናየው መነታሪኪያና መወነጃጀያ ያደረግነው የምንጠላ የምናወግዘውን ነው፡፡ የጠሉትና ለምን ሆነ ብለው በቁጭት የሚናገሩለት ነገር ዛሬ እንዳይደገም ለማድረግ መስራት እንጂ  ያንኑ እያነሱ ውሀ መውቀጥ የማናውቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትሉት ይቅርብን የምናውቀው የለመድነው  የወያኔ ግዞት ይሻለናል ከማለት በምን ይለያል? ወደ ፊት ለመሄድ የሚደርግን እንቅስቃሴ  ማወክ ያለው እንዲቀጥል መፈለግ የማይሆንበት ምን ማሳመኛ ማቅረብ ይቻላል? ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለማሻጋር በየዘመናቱ የተነሱ ሙሴዎችም  የከፋ ተግዳሮት የገጠማቸው  ከሚታገሉት ኃይል በላይ ወደ ዴሞክራሲ እየተጓዝን ነው ከሚሉ  ወገኖች ነው፡፡ ለትግሉ ራሳቸውን ሰጥተው፣ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት ቆርጠው፣ እንደ ሙሴ በብትርም ባይሆን በሰላማዊ መንገድ ወይንም በጠመንጃ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ቆርጠው የተነሱ ወገኖችን ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሁሉም ዴሞክራሲ የናፈቀወና አገዛዝ ያስመረረው  በሚችለው በመደገፍ ከዛም ያለፈው ከጎናቸው በመሰለፍ ጉዞውን ማፋጠን በተገባ ነበር፡፡ የእኛ የትናት ታሪክም ሆነ የዛሬ ተግባር ግን ይህን አያሳይም፡፡ ተለያይቶ በትናንት መነታረክ እንጂ ተደጋግፎ  ስንዝር ወደ ፊት የመራመድ ነገር የለም፡፡

ከሆያ ሆየው ጨዋታ ወጣ ብሎ ከወገንተኝነት ተላቆ ከስሜት በነጻ ሁኔታ ማየት ከተቻለ ወደ ፊት ከማየትና ከመስራት ይልቅ  ከትናንት ጀምሮ ወደ ኋላ ማየት ላይ ብቻ የማተኮሩና በዚሁ የመነታረኩ  አብይ ምክንያት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ሆና ማየትን ካለመፈለግ ነው፡፡  እስቲ አስቡት ኢትዮጵያ ለዛ ብትበቃ በተቀዋሚ ስም በተለያየ አይነትና መንገድ የተሰለፈው ምን ይሆናል? ሰዎቹን አጢኑአቸውና  ሁኔታቸውን ገምግሙና በየራሳችሁ ፍርድ ስጡ፡፡

እኔ ግን ፈቃዳቸው ይሁንና አቶ አሰፋ ጫቦ ትንሽ ገለጥለጥ የሚል ርእስ በሰጡት ጽሁፋቸው ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ  ያሉትን አንድ አንቀጽ በዋቢነት ልጥቀስና ልሰናበት፡፡ “ “ያጋራ ቤታችንን”  ጨርሼ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አዋጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል  Facebook  ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ባልተነበበ ጹሁፍና አስተያየት ላይ ነበር። ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማንውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን ? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ሰውረን ነው? አውቀን የካንደነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን?  ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ በተለየ አንዳንድ ዲያስፖራው ኗዋሪዎች መተደዳደሪያም ወደመሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ ሆነን፤አገር አውቆን ፣ፀሐይ ሞቆን፤ አንቱ የተባልንበትን ልታፈርስብንም ነው  የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል። ” በተቀዋሚነት ስም ያገኙትን/የሚያገኙትን ክብርም ይሁን ብር ይዞ ለመዝለቅ ወያኔ በሥልጣን መቆየት አለበት፡፡ለዚህ ደግሞ አንድ ከጳጳሱ ቄሱ እንዲሉ ሆኖ ዋንኛ የወያኔ ተቀዋሚ መስሎ የቃላት አረር መተኮስ፣ከተግባሩ ቦታ አለመድረስ፤ሁለት ከምር ወያኔን ለመጣል የሚታገሉትን መሀከላቸው ገብቶ መናጥ፣ከጎን ሆኖ ማደናቀፍ፣ከኋላ ሆኖ መጎተት፡፡

ሶስት ህዝቡ በአንድ እምነት ተስማምቶ፣በአንድ ሀገር ልጅነት ተማምኖ  ትኩረቱን እየገደለው እያሰረና እያሰቃየው ባለው ወያኔ ላይ እንዳያደርግ የሀሰት ታሪክ እየፈጠሩ የጥላቻ መርዝ መርጨት፡፡ በዚህ ስራቸውም የራሳቸውን ጥቅም የወያኔንም እድሜ ያስጠብቃሉ፡፡ ፈጣሪ የወሰነው ቀን ሲደርስ ከብዙ መንከራተት በኋ እስራኤላውያን ሂዱ ወደአላቸው ሀገር ደርሰዋል፤እነሆ ዛሬ አይበገሬ ኃያል ሀገር ለመሆን በቅተዋል፡፡  ኢትዮጵያንም አይረሳትምና የወሰነላት ቀን ሲደርስ ለዴሞክራሲ መብቃቷ አይቀሬ ነው፡፡ ጉዞውንም ታሪክ ይመዘግበዋልና ያኔ ሁሉም አንደ ስራው ክብረትን ወይንም ውርደትን ያገኛል፡፡ እና ባንደርስ ልጆች የልጅ ልጆቻን ይኮራሉ ወይ ያፍራሉ፡፡ ልጁ የልጅ ልጁ የሚያፍርበት ወላጅ ላለመሆን ዛሬ ከራስ በላይ እናስብ ገንዘብ እቃ የምንገዛበት እንጂ እኛ የምንገዛበት አይሁን፤ «..ስለዚህ እላችኋላሁ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይንም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡» (የሉቃስ ወንጌል ም.2 ቁ.!2)

LEAVE A REPLY