“የተራሮች ወግ 1” – ከአደዋ ተጓዦች /በያሬድ ሹመቴ/

“የተራሮች ወግ 1” – ከአደዋ ተጓዦች /በያሬድ ሹመቴ/

“ጤና ይስጥልኝ ወንድሜ። ይህ አካባቢ ስሙ ማን ይባላል?

“መነኩሲቶ ይባሓልን” ቁመተ ሎጋው ገበሬ መልስ ሰጠ። ቀጠለና ተረኛ ጠያቂ እሱ ሆነ።
“ምን ታደርጉ ነው ጉዑዞ? የት ትሔዱ?”
“ዓድዋ”
“ምን አሎ ዓድዋ? ምን ትሰሩ?”
“ኢትዮጵያ ጣሊያንን ጦር ወግታ ያሸነፈችበትን በዓል ለማክበር ነው። የካቲት 23”
“ለካቲት! እህ በአያቶቻችን? የጅጋን ኢቴጵያ ጥሩ ኖው እንተዋወቅሲ? እነ ስመይ ወልደ ጆርጊስ ነው። ያንተውን ስም ማነው?”
“እኔ ያሬድ እባለለሁ”
“እህ ያሬድ! ለሱስ?”
“ሽመልስ” ብዬ የአምናውን ተጓዥና የዘንድሮውን የፊልም ቀረጭና አስተባባሪ አስተዋወቅኩት።

“ሺ.ማ.ል.ስ.” እየነጣጠለ ስሙን ጠራና ቀጠለ።
“ሺ-ማልስ ማለት የወሰደውን ገንዘብ መልሰህ ስጦ ማለት ነው?” እየሳቀ ጠየቀን። እኛም ሳቅን።

“አሁን ይሔ ብጀርባ ያሎ ተራራ ሺ-ፈጅ ይባላል። ቀደም ግዜ እንደ ላሊበላ ውቅሮ ቤተክርስቲያን ነበር ይባላል። አሁንስ ህጽው (የተዘጋ) በኋላ ድማ ብቃልሲ (በጦርነት) ሺ ሰው የሞቶበት ስለዝኮነሲ።” ስለ ተራራው በአፈታሪክ የሚነገረውን ተረክ ውብ አድርጎ በተሻለ አማርኛ ከትግርኛ ጥቂት ቃላት ጋር እየቀላቀለ ይነግረን ጀመር።

“አንዲት ንግስቲ ነበረች ብዚ። ንሳትን ልጅ ዎልዳ ክርስትና ታስነሳ ነገረች- ልቄሶች። ሲጦብቋት አትመጣም። ሲጦብቋት አትመጣም። ሲጦብቋት። ቅዳሴ ገብተው ጠርሸው፥ ደገ ሰላም ጎብተው ምግቢ በልተው ሳለ መጣች። እነሱስ በልተው ጠግበው ነበር ግን ‘ቅዳሴ ግቡ ልጄን ክርስትና አንሱ’ ብላ አዘዘች”

“ቄሶቹ ለሷ ፈርተው ለእግዚአብሔር ደፍረው ከነ ሆዳቸው ቅዳሴ ገቡ። ከዚያ ቧህላ እግዛብሔር ተቆጥቶ ልድፍረታቾ እሳንም ቄሶቹንም የተራራውን በር ዘጋባቸው። ታቦቱም በውሽጢ ቀረ ቄሶቹም እሷም ተቀሰፉ።” ሲል የተራራዋን አፈታሪክ አጫወተን።

ከወልዴ ጋር ሌሎችንም አፈታሪኮችን እያወጋን ቆይተን ተሰነባብተነው መንገዳችንን ቀጠልን።

የቀደመው ህዝባችን ፈሪሐ እግዚአብሔርን በተራሮቹ አምሳያ እያደረገ በማይናወጥ ቋሚ ቅርጽ፥ የቃል ቅርስ ለትውልድ የሚያቆየው በአስተሳሰቡ የመጠቀ ስለነበር ነው ብዬ አምናለሁ።

“እሷን ፈርተው እግዚአብሔርን ደፍረው” ከመባል ያውጣን።
የተባረከ ቀን ይሁንላችሁ።

LEAVE A REPLY