የታጋይ ጎቤ መልኬ ሞት፤ የነፃነታችን ኩራት!

የታጋይ ጎቤ መልኬ ሞት፤ የነፃነታችን ኩራት!

   ለመብትና ለነጻነት የሚደረግ ትግል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል የተማርነው፤ የታሪክ ማህደሮችን በማገላበጥ አይደለም። ክቡር ህይወትን፤ ለሕዝብ እና ለአገር ነፃነት አሳልፎ መሥጠት ከቅድመ አያቶቻችን፤ ጀምሮ፤ በኩራት እየወረስን ዘመኑን ዋጀን እንጂ። ለዘለዓለም በባርነት ከመገዛት፤ ለአገርና ለወገን ነጻነት፤ ህወታቸውን ሰጥተው፤ በኩራት እኛም ነፃነታችንን ጠብቀን በመኖር ለቀጣዩ ትውልድ እንድናሥተላልፍ፤ የውጭ ወራሪን፤ የውሥጥ ባፍንዳን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ፤ አሁን ላይ አድርሰውናል።
ጎቤ መልኬም የነዚያ ጅግኖች አባቶቻችን፤ ታሪክ ወራሽ እና ለቀጣዩ ትውልድ ምሳሌ ይሆን ዘንድ፤ ጀግነንትን በሆዱ ያለወጠ፤ ለኃብቱ ቀርቶ ለንፍሱ ያልሳሳ፤ የኢትዮጵያ ኩራት የጎንደር ጀግና ነው።

ዛሬ፤ አርበኛ ጎቤ መልኬን በወያኔ ነብሰ በላዎች፤ በመነጠቃችን፤ አንጥፈን ሙሾ አንደረድርም፤ ታሪካችንንም በነበር አንደመድምም። አስተምሮን ያለፈው፤ ትናንት፤ እነ አበራ ጎባው፤ እነ ወጣት ሞላ አጃው፤ እነ ደጀኔ እና የመሳሰሉት ጀግኖች የጎንደር አርበኞች ሲቀጠፉ፤ በሃዘን ልቡን በመሥበር፤ ተሥፋ ቆርጦ፤ እጅ ለጠላት መሥጠትን ሳይሆን፤ በጀግንነት እና በቆራጥነት፤ ለነፃነት የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ፤ የበለጠ ሺ የጎንደር ጀግኖች፤ እንዲከተሉት፤ ለሁላችን ኩራት የሆነውን መሥዋዕትነት ከፍሎ የጀግና ክብሩን አወጀ እንጂ።

አሥገራሚው እና አሥደናቂው የታሪካችን ገጽታ ደግሞ፤ አገራችን አንድነቷን፤ እኛም ነፃነታችን ጠብቀን በኩራት እንዳንኖር፤ ዘመናዊ መሳሪያውን በመተማመን፤ በትቢት ተወጥሮ፤ ለሆዳቸው ያደሩ ሆዳም አገር በቀል ባንዳዎችን መልምሎ፤ በባርነት ሊገዛን የመጣውን የጣሊያን ጦር፤ ጀግነት እንጂ የመሳሪያ ጥራት፤ ለድል አያበቃም ብለው፤ የነፃነት ተጋድሏቸው ታሪክ፤ በድል ተጠናቆ ለዘለዓለም በትውልድ እንዲዘከር ያደረጉት፤ በዚሁ ወርኃ የካቲ መሆኑ ነው።

ዛሬም ከነዚያ የባንዳ የልጅ ልጆችና፤ በገንዘብ ከተገዙ ምንደኞች ጋር፤ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ሲታገል መሰዋዕት የሆነው ታጋይ ጎቤ መልኬ፤ የካቲትን እንደ ቅደመ አያቶቹ እና አባቶቹ በደሙ ዋጅቷት አልፏል። ታጋይ ጎቤ የሰው ልጅን መብትን ለማስከበር ወደ ትግል ሲገባ ይህን ነብስን ያህል ክቡር ዋጋ እንደሚያስከፍለው አውቆና አምኖ ነበር፤ የወያኔን ጦር እና በገንዘብ የተገዙ ባንዳዎች ለመፋለም በርሃ የወረደው።
ወያኔ ታጋይ ጎቤን በማጥፋት ትግሉን ያደፈነ ሊመስለው ይችላል። ይህን ተሥፋ ሰንቆ፤ አርበኞቻችን በመጨፍጨፍ፤ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የጀመረው፤ ዛሬ፤ በአርበኛ ጎቤ መልኬ ላይ ብቻ አደለም። ወያኔ፤ በሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን በእሥር ቤት እያማቀ ባለበት ሰዓት፤ የከተማው ትግል፤ ጭራሽ፤ መልኩን ቀይሮ እልህ አሥጨራሽ ትግሉ ቀጥሏል። በመቶ የሚቆጠሩትን፤ እየገደለ ቢቀጥልም፤ ከነ ታጋይ

መልኬ በፊት የተጀመረው የትጥቅ ትግል የበለጠ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዛሬው የታጋይ ጎቤ መልኬ፤ መሥዋዕትነ፤ በጀግንነት ሊታገሉ ዱር በርሃ ከገቡት በመለስ፤ በዚህች ወርሃ የካቲት ሌላ ጀግኖችን የሚወልዱ ሺ ሴቶች፤ ሺ መልኬዎችን ፀንሰው እንደሚያድሩ ፈጽሞ አንጠራጠርም!!

ወያኔ፤ ግን የራሱ የእውር ጉዞ ባይታየውም፤ ከደርግ ውድቀት እንኳ ትንሽ መማር ያልቻለ፤ ሁለት እግር ያለው አውሬ ነው። ደርግ ሕዝባችን በጭካኔ በጨፈጨፈ መጠን፤ የበለጠ ሕዝባችን ልቡ እንዲሸፍት፤ እና አጋጣሚውን ሁሉ ተጠቅሞ ሥራዓቱን የሚያንኮታኩትበትን ጊዚ እንዲጠብቅ አዘጋጀው እንጂ። ለዚያም ነው ወያኔ ሲመጣ፤ የይሻል ይሆናልን ተሥፋ ሰንቆ፤ በሩን ከፍቶ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እንዲገባ ያደረገው። ይህን ግን ልብ አላሉም!! እኛ ግን፤ “የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው” አንልም። ከእግዚአብሔር በታች፤ የነ አቡነ ጵጥሮስን መሥዋዕትነት እየዘከርን፤ ታሪካቸውን በተግባር ለመድገም የበለጠ እንጠነክራለን እንጂ።

ይህ ከወያኔ ጋር የምናደርገው ትግል፤ አገርን እንደ አገር ሕዝብን በማንነቱ እና በነፃነት፤ የማሥቀጠል ጉዳይ በመሆኑ፤ ወያኔ፤ ሺ ሆዳም ባንዳዎችን፤ በዙሪያው ኮልኩሎ፤ በጭካኔ፤ ቢዘምትብንም፤ ባንዳ ለሆዱ እንጅ፤ ለክብሩ ቆራጥ አለመሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን። ትግላችን ግን የሚሊዮኖች ነው። የወያኔንም ጭካኔ፤ የምንሰብረው፤ እጥፍ ድርብ ምላሹን በመሥጠት ነው።

በመሆኑም፤ ዛሬ ወያኔ፤ በጎንደር አርበኞች ላይ፤ እየወሰደ ያለው፤ አረመኒያዊ ግድያ፤ ነገ ደግሞ፤ ጊዜውን ጠብቆ፤ በመላ ኢትዮጵያ በያላችሁበት በራችሁ ድርሥ እስኪመጣ በመላ አገራችን ያላችሁ አርበኞች፤ በዝምታ ተራችሁን አትጠብቁ!! በየአላችሁበት የነፃነት ተጋድሏችሁን አቀናጁ እና የወያኔን ፍፃሜ አሳጥሩ እንላለን።

ጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት በታጋይ ጎቤ መልኬ ሞት፤ ከፍተኛ ሐዝንና ቁጭት የተሰማው መሆኑን ይገልጻል። ይሁን እንጂ፤ በቀጣዩ ትግላችን፤ የጎቤን ደም እጥፍ ድርብ ለማሥከፈልም ይሁን ለነፃንታችን የከፈለውን የህይውት ዋጋ ከግብ ለማድረስ፤ ትግሉን እየቀጠሉ ካሉት የትግል ጓዶቹ ጎን በመቆም፤ የድርሻችን እንደምናበረክት ለመግለጽ እንወዳለን። ለነጻነት የቆረጠ ሕዝብ፤ ነጻነቱን እስኪ ጎናጽፈ ድረስ፤ ታጋይ ሲሰዋ ሌላ ታጋይ እየተካ ለግብ እንደበቃ የህብረተሰብ ሳይንስ ያስረዳናል። በደቡብ አፍሪካ፤ በቪትናም የተመለከትነው የቆራጥ ህብረተስብ ተጋድሎ የሚያስተምረን ይህንን ነው።

ለጎቤ ቤተሰቦች እና ለታጋይ ጓዶቹ መጽናናቱን እንመኛለን

ታጋይ እንጅ ትግል አይሞትም!!!!!!!

ጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት
3/1/2017

LEAVE A REPLY