ጋን ቢሆን ምንቸቱ -የማን ነው ጥፋቱ? /ይገረም አለሙ/

ጋን ቢሆን ምንቸቱ -የማን ነው ጥፋቱ? /ይገረም አለሙ/

አምባሳደር ተስፋዬ አብዲ ከኢሳት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በኔት ወርክ ችግር  ምክንያት ዘግይቼ ነው ያዳመጥኩት፡፡ አምባሳደር ተብለው ይጠሩ አንጂ ያልዋሉበት ቦታ ያልሰሩት  የሥራ መስክ የለም፡፡ ከጀት አብራሪነት እስከ ደህንነት ሰርተዋል፣ከመከላከያ እስከ ውጪ ጉዳይ ብዙ ቦታዎችን አዳርሰዋል፡፡ በአብዮቱ አፍላ ወቅት ሶሻሊዝምን እናራምዳለን ያሉ፣ በርዕዮተ ዓለም ያልተለያዩ ርሳቸው “ሥልጣነኝነት” የሚል መጠሪያ ባወጡለትና ሌሎቻችን የሥልጣን ጥም በምንለው ሲገዳደሉ በቅርብ ነበሩ፡፡ ጠንቁ እስከ ዛሬም ያለቀቀን ነጭና ቀይ ሽብር በማንና እንዴት አንደተወጠነና እንደተፈጸመ ያውቃሉ፡፡ ከንጉሱ ቤተሰቦችና ባለሥልጣኖች የጅምላ ፍጅት  በመፈንቅለ መንግሥት እስከተረሸኑት ጀነራሎች ብሎም ኮ/ል መንግሥቱ በቀጭን ትዕዛዝ ማዕረግ ከመግፈፍ እስከ ርሸና ርምጃ ያስወሰዱባቸውን የጦር መከንኖች ከነምክንያቱ ያውቃሉ፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ ማጋነና ካልሆነብኝ ከአዳመጥኩት ሶስት ክፍል ቃለ ምልልስ (ከዩቲዩብ)  እንደረዳሁት ከሚያውቁት የማያውቁት የሚያንስም የሚቀልም ይመስለኛል፡፡

ትንሽ ሰርተው ብዙ እንዲወራላቸው የሚሹና በትንሽ እውቀት መድረክ የሚጠባቸው በሞሉበት አምባሳደር ተስፋየ የሰሩትንም የሚያውቁትንም በጓዳቸው ከመያዝ አልፈው እስከ አሁን ድረስ ሲሰሩም እዩዩኝ እያሉ ሳይሆን  ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ውጤት እየናፈቁ መሆኑ በእውነቱ አድናቆትና  አክብሮት እንዲቸራቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ርሳቸውም አንደተናገሩት ከሁኔታውም መገመት እንደሚቻለው በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ከአደባባይ ያቀቡ ለሀገራቸው ብዙ የሰሩና ብዙ የሚያውቁ እንደ አምባሳደር ተስፋየ አይነት ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ግን ምን ያደርጋል አልተገናኝቶም ሆነ፡፡

መድሀኒት ላጣው የሀገራችን የፖለቲካ በሽታ በቂ ህክምና ለመስጠትና ፈዋሽ መድሀኒት ለማዘዝም ሆነ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ላስቸገረው ተላላፊ በሽታ ክትባት ለማዘጋጀት የሀገራችንን ችግር መንስኤ ምንነት፣ የበሽታውን ምልክት፣ የሚያስከትለውን ውጤት ወዘተ በደንብ የሚያውቁ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉን አይተው፤ የሚችሉትን ያህልም ጥረው ግረው አልሆን ሲላቸው ከበሽተኞች ጋር አልቀጥልም ብለው ከተለዩት አምባሳደር ተስፋየና መሰሎቻቸው የሚቀድም አልነበረም፡፡ ግና ምን ዋጋ አለው “ጋኖች አለቁና ምንቸት ጋን ሆኑ” የሚለውን አባባል ሥልጣኔ ለውጦት ጋኖቹ ባሉበት ምንቸቶች ጋን እየሆኑ ሀገር ከበሽታዋ ትፈወስ ዘንድ ህክምናውን መስጠት ትክክለኛውነ መድሀኒትም ማግኘት ክትባቱንም ማዘጋጀት የሚችሉት የሚገባቸውም ሰዎች ውሎአቸው ከመጋረጃ ጀርባ ሆነና በሽታችን ፈወስ አጥቶ ቀጥሏል፡፡

የአምባሰደርን ቃለ ምልልስ እያዳመጥኩ ከዚህ በላይ ያነሳሁትን  በአእምሮየ እወጣሁ እያወርድኩ ሀገርን ከበሽታዋ እንፈውሳለን፣ ከችግር እናላቅቃለን፣ ለዴሞክራሲ እናበቃለን ወዘተ ብለው በፖለቲካው መድረክ ላይ የሚታዩትንና አምባሳደር ተስፋየን ጨምሮ በተለያየ ግዜ ወደ መገናኛ ብዙኃን ብቅ ብለው ያወቅናቸውንና ከመጋረጃ ጀርባ አሉ ብየ የገመትኳቸውን በህሊና ሚዛን መመዘን ውስጥ ገባሁ፡፡፡ እስቲ ምዘናውን አግዙኝ፡፡ በሚዛኑ አንደኛው ወገን  ላይ የሚቀመጡትን ስም መዘርዘር ሳያስፈልግ እነ አምባሳር ተስፋየ አብዲ እንበልና በዛኛው ረድፍ ሰሩም አልሰሩ በገሀድ ያሉ ስለሆነ ስማቸውን መጥቀሱ የህግም የሞራልም ጥያቄ አያስከትልምና ከሰማያዊዎቹ ይልቃልና የሺዋስ እስከ መድረኩ በየነ ጰየጥሮስ፣ ከኢዴፓው ጫኔ ከበደ እስከ መኢአዱ በዛብህ ደምሴ፤ ከቅንጅቱ አየለ እስከ ጫሚሶ እስከ ኢፍዴኃግ  ግርማይ ሀደራ፣( ይህን ግንባሩም መሪም ብዙ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ የማወቅ ጉዳይ ከተነሳ አንድ ጥያቄ አስቀምጬ ልለፍ፡፡ የፕ/ር በየነን ፓርቲ ሙሉ ስም ምን ያህል ሰው ያውቀው ይሆን ? መድረክን አይደለም፣፡ አለማወቅ ሀጢአትም ወንጀልም አይደለምና በሚያመቻችሁ መንገድ ተናገሩ፡፡ከሚያውቀው የማያውቀው ከበዛ በዚሁ መስመር ብቅ ስል ሹክ እላችኋላሁ እስከዛው ግን የቤት ሥራ ይሁን፡፡) ከኢሰዴፓው ይመር እስከ ኢአዴዱ አድማሱ ሀይሉ፣ ከመኢብኑ መስፍን ሽፈራው እስከ ራዕዩ ተሻለ ሰብሮ ወዘተ በሌላኛው የሚዛኑ ጫፍ ደርድሩና መዝኑዋቸው፡፡ ያለ ጥርጥር የሚገኘው ውጤተ ወይ ነዶ ነው ፡፡  (ማእረጋቸውና አንቱታው የቀረው ለአጠራር አንዲያመች እንጂ ሌላ ምክንያት የሌለው መሆኑን  በአክብሮት እገልጻለሁ፤ እንዲሁም የሀገር ቤቶቹን ብቻ የጠራሁት ስለ ውጪዎቹ ብዙም እውቀት ስለሌለኝና አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው ስለሀገር ቤቶቹ ፓርቲዎች ከአባላቱ አይደለም ከመሪዎቹ በላይ እናውቃለን እንደሚሉት ድፍረቱ ስለሌለኝ ነው)

በዛኛው የሚዛኑ ጫፍ የደረደርናቸው ሀገሪቱን ከበሽታዋ እንፈውሳለን የሚሉን  “ፖለቲከኞች” ለሀያ አምስት አመት እንዳየናቸው አይደለም ሀገር ሊያድኑ ለስማቸው መጠሪያ የሆኑዋቸውን ድርጅቶቻቸውን በሽታ እንኳን ማወቅተስኖአቸው  የአልጋ ቁራኛ ያደረጉ ናቸውና ሚዛን  የሚደፉ ሆነው አልታዩኝም፡፡

ምንቸቶች ጋን ሆነው ጋኖቹ ቦታ አጥተው፤

መድሀኒቱ ጠፍቶ ስቃይ ሆነ ኑሮው፣

እስቲ አንነጋገር ከቶ በዚህ ጉዳይ  ተጠያቂው ማነው?

ምንቸቶቹ ያልሆኑትን አይደለም ሊሆኑ የማይችሉትን ጋን ነን ብለው አለቦታቸው በመገኘታቸው በድፍረታቸው በዚህም ባደረሱትና እያደረሱ ባሉት ጥፋት ተጠያቂ ናቸው ብንል እንዴ ቦታውን ባዶ ሲያገኙት፣ አረ እናንተ ምንቸት አንጂ ጋን አይደላችሁም፣ ካለ ቦታችሁ ምን ታደርጋላችሁ የሚላቸው ሲጠፋ እነርሱ ምን ማድረግ ነበረባቸው ክፍት የተገኘ ቤት ቀድሞ የደረሰ ነው የሚገባበት የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል፡፡

ጋኖቹ ቦታቸውን ማስጠበቅ ጋንነታቸውንም በተግባር ማሳየት ነበረባቸውና በጋኖች ቦታ ምንቸቶች እንዲፈነጩ በማድረጋቸው  እነርሱም ተጠያቂነት አለባቸው ብሎ ለመድፈር ደግሞ  ባልተገራ ምላስና በላሰላ ብእር የሚካሄደው የአየር በአየር የቃላት ተኩስ ጋኖቹን መች በቦታቸው የሚያቆይ ነውና የሚል ተቃራኒ ሀሳብ አእምሮ ያፈልቃል፡፡

ጋንና ምንቸትን መለየት የማይቸግረው ተገልጋዩ አንድም ምንቸቶች በጋን ቦታ አለን ሲሉ ወግዱ ይሄ ቦታችሁ አይደለም ማለት ሁለትም አቅማቸውን አውቀው በምንቸትነታቸው አገልግሎት አንዲሰጡ አንጂ ጋን ነን እያሉ አንዳይንጠራሩ ማድረግ ነበረበት ይህን ለማድረግ ደግሞ የማንም ወገን ፈቃድና ክልከላ የማያግደው የራሱ ግላዊ መብት ነው በማለት የተጠያቂነቱ ሚዛን ወደ ህዝቡ እንዳይገፋ ተቧድነው ብቅ በማለት ወኪልህ ነን ይላሉ አንጂ መች ወክለን ይሉታል፣የምንልህን ተቀበል ይሉታል እንጂ ምች ያዳምጡታል፣ወዘተ የሚለው ሀሳብ በተቃራኒ ይከሰታል፡፡ እንዲህ እንዲህ ቢባልም ይነስም ይብዛ ይክበድም ይቅለል እንጂ ሁላችንም የድርሻ ተጠያቂነት አለብን፡፡በሽታችንን ለማወቅ ያላስቻለን ትልቁ ችግርም ይሄ ነው፤ ጣትን ወደ ሌላው ለመቀሰር ያለንን ድፍረት እሩቡን ህል አንኳን ወደ ራስ ለማዞር አለመድፈር፡፡

ከድፍረት አይቆጠረብኝና በቦታቸው ያልተገኙትን ጋኖች ለመውቀስም ለመክሰስም ሳይሆን (ደሞስ ማን ሁኜ) ዝምታ ለምን በሚል ሶስት ጥያቄዎችን ላንሳ፡፡

  1. አንዳንዶቹ አንደ አምባሳደር ተስፋዬ ከነበረው መንግሥት በግዜ ቢፋቱም አንዳንዶቹም እስከ መጨረሻው አብረው ቢዘልቁም( እንደውም አንዳንዶቹ ከንጉሡ ዘመን ነው የሚጀምሩት) ዛሬ ሀገሪቱን የሚያብጠውና ትውልዱን ርስ በርስ የሚያባላው በሽታ ከእነርሱ የተላላፈ ነውና በሽታውን የማወቅም ሆነ መድሀኒቱን የመፈለግ ኃላፊነት አለባቸውና ዝምታ ለምን ማለት ከጀለኝ፡፡
  2. ሀገራቸው እንዳደረጉላት ባታደርግላቸውም ዜጎች ናቸው፡፡ በአምባገነን አገዛዝ የሚሰቃየው ህዝብ ወገናቸው ነው፡፡ የበሽታውን እንዴትነት የመድሀኒቱንም ምንነት የሚያውቁት እነርሱ ወደ ጎን ሆነው ፤ በአላዋቂ ሀኪም ሀገርና ህዝብ በበሽታ ሲሰቃይ ማየት አንዴት አስችሏቸው ነው ዝም የሚሉት ለማለትም ስሜቴ ገፋፋኝ፡፡
  3. የብዙዎቹ ልጆች ከሀገር ውጪ እንደሆኑ ቢገመትም ኢትዮጵያዊነታቸውን አውልቀው የሚጥሉት አይደለምና ሀገር ከበሽታዋ ተፈውሳ ጤናማ ብትሆን ሀገሬ ብለው ሊወጡ ሊገቡ እንዳም ሲል ጓዛቸውን ጠቅለው ሊመጡ ይችላሉ፡፡እናም ሀገራቸው ለእነርሱ ልትሆን ላለመቻሏ የእነርሱም ድርሻ አንዳለበት ሁሉ በተቃራኒው ለልጆቻቸው እንድትሆን በማድረጉ እጃቸው ሊኖርበት ይገባል ብዬም አሰብኩና ዝምታ ለምን ለማለት ደፈርኩ፡፡፡ “አባት ያበጀው ለልጁ በጀው ” አይደል የሚባለው ፡፡

ይህ ስሜት ኢሳት ከአምባሳደር ተስፋዬ ጋር ያደረገውን ውይይት በመስማቴ የተፈጠረ ሳይሆን የቆየ ነው፡፡ኢሳትና ቪዥን ኢትዮጵ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ሳይ ይሄው ስሜቴ ተቀስቅሶ  ግንቦት 2008 “መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የሰው ድሀ ሀገር ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ  ብሽቀት ቁጭቴን ጽፌ ነበር፡፡ ያንን ጽሁፌን ያሳረኩበትን አንቀጽ ዛሬም ልድገመው፡፡

መቼ ይሆን! ኢትዮጵያ ልጆቿ  ቁጥራችን ብቻ ሳይሆን ቁም ነገራችንም በዝቶ ሰው እያላት የሌላት የሰው ድሀ ከመሆን የምትወጣው? መቼ ይሆን! በዘር፣ በሀይማኖት፣ በአመለካከት ልዩነት ተለያይተው የመቶ ሚሊዮኖች እናት ግን የሰው ድሀ ያደረጉዋት ልጇቿ ከምንም ነገር በፊት እናታችን ብለው እውቀታቸውን አቀናጅተው ሀይላቸውን አስተባብረው  ነጻነት የሚያቀዳጇት? መቼ ይሆን! ልጆቿ ከራስ በላይ ነፋስ አስተሳሰብ ተላቀው፣ ከመጠላለፍ አዙሪት ወጥተው፣ ከቁልቁለት ጉዞ የሚያቃኑዋትና  የነበረ ዝናና ክብሯን መልሰው የሚያቀዳጁዋት? አረ መቼ ይሆን! ልጆቿ  ዴሞክራሲ እየተረገዘ የሚጨነገፍበትን ሲወለድም   በአጭር የሚቀርበትን በሽታ ተርደተው መድሀኒትም አግኝተውለት ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ የሚበቁት ? አረ መቼ ይሆን! ልጆቿ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር የሰው ድሀ የሆነችው እነርሱ ተለያይተው በመቆማቸው፤ በስልጣን ጥም በመታወራቸው፤ ከእኔ በላይ በሚል አስተሳሰብ በመታጠራቸው፣ለራስ እንጂ ለመጪው ትውልድ የማይጨነቁ በመሆናቸው ወዘተ መሆኑን ተረድተው ከየራሳቸው ታርቀው፣ ርስ በርሳቸው ፍቅር መስርተው፣ እንደ ብዛታቸው ቁም ነገራቸውም ለሀገርና ለወገን ሲበጅ የሚታየው ? መቼ አረ መቼ !

– See more at: http://ecadforum.com/Amharic/archives/17470/#sthash.Xw69dq7t.dpuf

LEAVE A REPLY