ትራምፕ፡ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ያስቀናል! /አብርሃ ደስታ/

ትራምፕ፡ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ያስቀናል! /አብርሃ ደስታ/

ዴሞክራቱ ባራክ ኦባማ በሚመራው መንግስት ስር ሀገራዊ ምርጫ ተካሄደ። የተቃዋሚው (የሪፐፕሊካን) ፓርቲ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕና ዴሞክራቷ ሂላሪ ክሊንተን ተወዳደሩ። አማራጫቸውን ያለምንም ገደብ ለህዝብ አቀረቡ። ምክንያቱም በሀገረ አሜሪካ ፓርቲና መንግስት የተለያዩ ናቸው።

የገዢው ፓርቲ ዕጩ የመንግስት ሀብትና የስልጣን መዋቅር ተጠቅሞ የተቃዋሚውን ዕጩ ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ አይችልም። በመንግስት ዓይን ሁለቱም ተወዳዳሪዎች እኩል ናቸው። ነፃ ሚድያም አለ። ሚድያ ህዝብን ያገለግላል። የሁለቱም ተፎካካሪዎች አማራጭ ሐሳብ ለህዝብ ያደርሳል። የተሻለውን ሐሳብ የሚመርጠው ህዝብ ነው። እንደኛ ሀገር ሚድያዎች ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚያገለግሉ አይደሉም።

ትራምፕ ሐሳቡን ሲገልፅ እነ ኦባማ በሐሳብ ለመተቸት ሞከሩ እንጂ ደህንነትና ፖሊስን ልከው አላሳሰሩትም። ምክንያቱም የአሜሪካ ፖሊስ፣ ደህንነትና መከላከያ የህዝብና የሀገር አገልጋይ እንጂ የገዢው ፓርቲ ቅምጥ አይደለም። እንደኛ ሀገር በስልጣን ላለው አካል የሚሰሩ ሳይሆን ለህዝብና ለሀገር የሚሰሩ ህገመንግስታዊ ገለልተኛ ተቋማት ናቸው። እናም ትራምፕ የስልጣን ስጋት ስለሆነ ብቻ “አሸባሪ” ተብሎ ወህኒ አልወረደም።

ምርጫው ተካሄደ። ህዝቡም ትራምፕን መረጠ። የህዝብ ድምፅ ተከበረና ትራምፕ ስልጣን ያዘ። ምክንያቱም አሜሪካ ነው። እንደኛ ሀገር የህዝብን ድምፅ በመስረቅ የምርጫ ዉጤትን መገልበጥ አይቻልም። ምክንያቱም የምርጫ ቦርዱ የገዥው ፓርቲ አካል ሳይሆን ነፃ የህዝብ አገልጋይ ነው።

ትራምፕ ስልጣን ያዘና ሚድያዎች ይተቹት ገቡ። ትራምፕም ሚድያዎቹን ከመሳደብ የዘለለ ነገር ማድረግ አልቻለም። ምክንያቱም አሜሪካ ነው። የተቹትን ጋዜጠኞች እንደፈለገ ማሰር፣ ሚድያውን ማስዘጋት አይችልም። ህግ አለ።

ትራምፕ ስልጣኑን ተጠቅሞ የዉጭ ዜጎችን የሚከለክል ህግ ሲያወጣ የፍርድቤት ዕግድ ገጠመው። ምክንያቱም ትራምፕ ህግን ጥሶ የራሱን ፍላጎት ብቻ ማስፈፀም አይችልም፤ ፍርድቤቱም ማዘዝና ማስገደድ አይችልም። ፍርድቤት ከፕረዚዳንት በላይ ነው። እንደ ኢትዮጵያ አይደለም። በኛ ሀገር ፍርድቤት ባለስልጣናትን ለማገልገል የተቋቋመ ሲሆን የአሜሪካ ፍርድቤት ግን ህዝብና ሀገርን ለማገልገል የቆመ ነፃ ተቋም ነው።

ትራምፕ አሁንም ኦባማኬር (Obama Care) በሌላ ሄልዝኬር (Healthcare) ለመተካት ያቀደው በኮንግረስ ዉድቅ ሆኖበታል። የራሱ ፓርቲ (የሪፐፕሊካን) አባላት ጭምር ድምፅ ያልሰጡ አሉ። ምክንያቱም የኮንግረስ አባላቱ በህዝብ የተመረጡ፣ ለህዝብና ለሀገር የሚቆሙ እንጂ እንደኛ ሀገር በፓርቲ ተመርጠው ለፓርቲ የሚያገለግሉ አይደሉም። ዕቅዱ ለህዝብና ለሀገር አይጠቅምም ብለው ካመኑ የራሳቸው ፓርቲ ዕቅድም ይቃወማሉ። ምክንያቱም የአሜሪካ ዴሞክራሲ ሊበራል (Liberal Democracy) ነው። በአሜሪካ የተማዕከለ ዴሞክራሲ (Democratic Centralism) የለም። በኛ ሀገር ቢሆን የገዢው ፓርቲ አባላት የፕረዚዳንቱን (ጠቅላይ ሚኒስተሩን) ሐሳብ የመደገፍ ግዴታ አለባቸው። ካልደገፉ ከዴሞክራሲያዊ ጥርናፈ ስለወጡ ከፓርቲ አባልነታቸው ይባረራሉ። ለዚህ ነው ሁሉም የፓርላማ አባል እጁ የሚያወጣ። በአሜሪካ ግን የትራምፕ የራሱ ፓርቲ አባላትም ተቃውመውታል። ግን ማንም ከፓርቲ አባልነታቸው የሚያባርራቸው የለም።

ምክንያቱም አሜሪካ ነው። የአሜሪካ ዴሞክራሲ ያስቀናል። አንድ ፓርቲ ወይ ግለሰብ ባለስልጣን እንደፈለገ የሚሆንበት አይደለም። በህግና በተቋማት የሚመራ ሀገር ነው።

LEAVE A REPLY