4 ወር የፈጀው የኦፌኮ (የነአቶ በቀለ ገርባ) አመራሮች የምስክር ሂደት

4 ወር የፈጀው የኦፌኮ (የነአቶ በቀለ ገርባ) አመራሮች የምስክር ሂደት

9 ቀጥተኛ ምስክሮች

7 ተከሳሾችን መለየት ያልቻሉ ምስክሮች

3 ከተከሳሾቹ ጋር የማይገናኝ በኦሮሚያ የተነሳውን አመፅ ያስረዱ ምስክሮች

1 እነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዘዝገብ ላይ እንዲመሰክሩ አቃቤ ህግ የጠራቸው የሌላ መዝገብ ምስክር

17 የደረጃ ምስክሮች

30 በአጠቃላይ በአቃቤ ህግ የቀረቡ ምስክሮች 4

ተከሳሾ ችላይ (በቀለ ገርባን ጨምሮ) አቃቤ ህግ ላይ የሰው ምስክር ማቅረብ አልቻለም
እሮብ መጋቢት 20 የአቃቤ ህግ ምስክር ብይን ይሰጣቸዋል ተብለው የሚጠበቁት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታህሳስ 2008 ዓም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮች እነ በቀለ ገርባ ላይ ምስክር የማሰማት ሂደት በየካቲት ወር 2009 ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ፕሮጀክት እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ ሚያረጋቸው የፍርድ ቤት ውሎዎች ብዛት ያላቸው የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች የተካተቱበት በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ አንዱ ነው።

ምስክር የማሰማት ሂደቱ ከህዳር 02/2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 22/2009 ዓ.ም ድረስ የፈጀ ሲሆን፤ አቃቤ ህግ በተለያዬ ምክንያቶች መስክሮችንና ማሰረጃዎችን በእለቱ ሳያቀር መቅረቱ አንዲሁም ተደጋጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቁ ዋነኛው ምክንያት ነው። አቃቤ ህግ ተከሳሾች ላይ 40 ምስክሮች አሉኝ ቢልም 4 ወር በፈጀው ምስክር የማሰማት ሂደት ከሳሽ አቃቤ ህግ ማቅረብ የቻለው 33 ምስክሮችን ብቻ ነው።

አቃቤ ህግ ካቀረባቸው 30 ምስክሮች ውስጥ 1. ኢንስፔክተር ታደሰ አምዬ፣ 2. ኢንስፔክተር ደበላ አበባ እና 3. አቶ ቶሎሳ በየነ የተባሉ 3 ምስክሮች በአጠቃላይ በክሱ ጭብጥ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ረብሻ በተነሳበት አካባቢ በተለያየ የመንግስት ሃለፊነትና በፀጥታ ማስከበር ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው። ምስክሮቹ በኦሮምያ ክልል በተነሳው ህዝባዊ አመፅ ወቅት እረብሻውን ያስነሱት የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲን መታወቂያ የያዙ ናቸው ብለው የመሰከሩ ሲሆን፤ ምስክሮቹ ተከሳሾቹን አይተዋቸው እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። የተከሳሾቹ ጠበቆች ደንበኞቻቸው ወይም ተከሳሾቹ ላይ ስላልተመሰከረ መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጠየቁ አልፈዋል ጠበቆችም በደምበኞቻቸው ላይ እንዳልተመሰከረ ከመዝገብ እንዲያያዝላቸው ጠይቀዋል።

ቀጥተኛ ምስክርን በተመለከተ ቀጥተኛ ምስክር ወይም ተከሳሾቹን ከዚህ ቀደም በአካል የሚያውቋቸውና ከተከሰሱበት ወንጀል ጋር የሚገናኝ ድርጊት ሲፈፅሙ ያዩዋቸው ምስክሮችን በተመለከተ የፌደራል አቃቤ ህግ 9 ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን

1. ቡልቻ ነገሬ፣

2. ቱሉ ግሬና፣

3. ምልካሙ ባጫ፣

4. ጋዲሳ ታደሰ

5. ኮንስታብል ሽመልስ ኩማ፣

6. ረዳት ሳጅን ሙሉጌታ ጥላሁን፣

7. አራርሳ ዋቅቶላ

8. አዱኛ ከራ እና

9. ኢንስፔክተር አባተ ፈለቀ ይባላሉ።

1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖ ፡ ቡልቻ ነገሬ እና ቱሉ ግረና በ1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖ ላይ የመሰከሩ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖን ቡራዮ ቡና ጠጡ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው እያለ በስልክ “መንግስት የኦሮሞ ተወላጆችን በድሏል፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲፈቀድልን ጠይቀናል ከከለከሉን ዳር እስከዳር የኦሮሞ ተወላጆችን ቀስቅሰን አመፅ እናስነሳለን” ሲል ሰምተነዋል ብለው መስክረዋል።

ምስክሮቹ ቡራዮ ከተማ ውስጥ አመፅ ሲነሳ 1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖ ብጥብጥ ውስጥ አይተውታል ተብለው ሲጠየቁ “አላየነውም” ያሉ ሲሆን እዛው ቡና ጠጡ ቤት ውስጥ እያሉ ከተከሳሹ ተደራጅተን አብረን እንስራ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡ በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት በፓርቲ መደራጀትን ነው ወይስ ለአመፅና ብጥብጥ መደራጀትን ነው ሲባሉ “በፓርቲ መደራጀትን” ነው ብለው የመለሱ ሲሆን አቃቤ ህግ ለጠየቃቸው ተመሳሳይ ጥያቄ “ለአመፅ መደራጀትን” ነው ብለዋል መልሰዋል።

14ኛ ተከሳሽ ደረጃ መርጋ ላይ መላካሙ ባጫና ጋዲሳ ታደሰ የተባሉ ምስክሮች ቀርበው የመሰከሩ ሲሆን መላካሙ ባጫ የተባሉት ምስክር ከተከሳሾቹ ጋር አብረው በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ታስረው የነበረ ሲሆን፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል እንደነበሩና ለድርጅቱ ይመለምሉ እንደነበር ተናግረዋል።

ምስክሩ ከ14ኛ እስከ 17ኛ ያሉ ተከሳሾች ላይ ቀርበው መስክረዋል።

14ኛ ተከሳሽ የሆነው ደረጀ መርጋ ደውሎላቸው ኦነግን መቀላቀል የሚፈልጉ ልጆች ካሉ ስልኩን እንዲሰጡለት እንደጠየቃቸውና እሳቸውም የደረጀ መርጋን የስልክ ቁጥር ከዩንቨርስቲ ተባሮ ለነበረውና የእህታቸው ልጅ ለሆነው 15ኛ ተከሳሽ የሴፍ አለማየሁ እንደሰጡ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ሌላኛው ምስክር የሆኑት ጋዲሳ ታደሰ የተባሉ ሲሆን ከ14ኛ ተከሳሽ ጋር ጓደኛ እንደሆኑና ቀደም ባሉት ጊዜያት በመምህርነት አብረው ያገለግሉ እንደነበር በሳቸው ስምም ከውጪ 500 ዶላር እንደተላከላቸው ገልፀዋል።

ከውጪ የተላከው ገንዘብ ለምን ጉዳይ እንደሆነ የተጠየቁት ምስክሩ በወቅቱ ደረጀ ሁለተኛ ዲግሪ ይሰራ ስለነበር ለዛ እንዲረዳው የተላከ ይመስለኛል ብለዋል።

15ኛ ተከሳሽ ዮሴፍ አለማየሁ መልካሙ ባጫ የተባሉት ምስክር የ15ኛ ተከሳሽ የሴፍ አለማየሁ አጎት ሲሆን ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ አብረው ታስረው ቆይተው የእህታቸውን ልጅ ጨምሮ 4 ተከሳሾች ላይ ለመመስከር ተስማምተው ከማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ክስ ሳይመሰረትባቸው የተፈቱ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

የእህታቸው ልጅ የሆነው ዮሴፍ አለማየሁ አንድ ወቅት ላይ “ኦነግን የመቀላቀል እድል ካገኘው እቀላቀላለሁ” እንደሰሙትና 14ኛ ተከሳሽ የሆነው ደረጀ መርጋ “ኦነግን መቀላቀል የሚፈልግ ሰው ካለ ስልኬን ስጣቸው” ባላቸው መሰረት ለእህታቸው ልጅ ዮሴፍ አለማየሁ የ14 ተከሳሽ ደረጀ መርጋን ስልክ እንደሰጡት ተናግረዋል።

ኮንስታብል ሽመልስ ኩማና ረዳት ሳጅን ሙሉጌታ ጥላሁን የተባለው ምስክር የፌደራል ፖሊስ አባላት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ሞያሌ ኬላ በስራ ላይ ተሰማርተው ሳለ በዕለቱ 15ኛ ተከሳሽ ዮሴፍ ለማየሁ እና 16ኛ ተከሳሽ በህዝብ አውቶብስ ተሳፍረው ወደ ሞያሌ በማምራት፣ የኢትዮ ኬንያን ድንበር ተሻግረው ኦነግን ሊቀላቀሉ እንደነበር ጀምበሩ ከተባለ የደህንነት ሰራተኛ መረጃ ተቀብለው ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን መስክረዋል።

16ኛ ተከሳሽ ሂካ ተክሉ፡ እንደ 14ኛ እና 15 ተከሳሽ ሁሉ መልካሙ ባጫ 16ኛ ተከሳሽ ሂካ ተክሉ ላይ የመሰከሩ ሲሆን፤ ሂካ ተክሉ ከምርጫ 2007 በኋላ የአካባቢው ካድሬዎች አላስኖር ስላሉኝ ጫካ መግባት እፈልጋለሁ ስላለኝ ዮሴፍ አለማየሁ በሞያሌ በኩል ኦነግን ለመቀላቀል ሊሄድ ስለሆነ ደውልለት አብራችሁ ሂዱ ብዬ የዮሴፍን ስልክ ሰጥቼዋለሁ በማለት መስክረዋል።

እንደ 15ኛ ተከሳሽ በተመሳሳይ ኮንስታብል ሽመልስ ኩማና ረዳት ሳጅን ሙሉጌታ ጥላሁን የተባሉት ምስክር በኢትዮጵያ ሞያሌ ኬላ በስራ ላይ ተሰማርተው ሳለ በዕለቱ 15ኛ ተከሳሽ ዮሴፍ ለማየሁ እና 16ኛ ተከሳሽ በህዝብ አውቶብስ ተሳፍረው ወደ ሞያሌ በማምራት፣ የኢትዮ ኬንያን ድንበር ተሻግረው ኦነግን ሊቀላቀሉ እንደነበር ጀምበሩ ከተባለ የደህንነት ሰራተኛ መረጃ ተቀብለው ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን መስክረዋል።

17ኛ ተከሳሽ ገመቹ ሻንቆ፡ መልካሙ ባጫ የተባሉት ምስክር ስለገመቹ ሻንቆ ሲናገሩ “በ2006 ዓ.ም ለኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ የሚሆን ቢሮ አከራየቸው ነበር፤ ካዛ ብዙም አይቼው አላውቅም ነበር በ2008 ዓ.ም የዮሴፍ አለማየሁን ስልክ ስጠኝ ብሎ ደውሎልኛል። ደረጀም መርጋም የገመቹን ስልክ ሲጠይቀኝ ሰጥቸዋለሁ። ስለምን እንዳወሩ የማውቀው ነግር የለም” ብለው ገመቹን በተመለከተ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል

22ኛ ተከሳሽ አልካኖ ቆንቸራ፡ ኮንስታብል ሽመልስ ኩማና ረዳት ሳጅን ሙሉጌታ ጥላሁን የተባሉት ምስክሮች በዜግነት ኬንያዊ እንደሆነ በክሱ ላይ የተመለከተው 22ኛ ተከሳሽ ሀልካኖ ቀንጨራን በተመለከተ ‘ሀልካኖ 500 የኬንያ ሽልንግ እየተከፈለው ተጠርጣሪዎቹን (15ኛ እና 16ኛ ተከሳሾችን) ወደ ኬንያ ሊያሻግር ነበር ብሎ የደህንነት ሹሙ ነግሮናል’ ከማለት ውጭ እንዴት እንደተያዘ እንደማያውቁ 19ኛ ተከሳሽ ለሚ አዴቶ፡ አራርሳ ዋቅቶላ የተባሉት ምስክር በቡራዮ ከተማ የኮምፒውተር ቤት ያላቸው ሲሆን 19ኛ ተከሳሽ የሆነው ለሚ አዴቶ በሚሞሪ ካርድ ፋይል ይዞ መጥቶ ብዙ ጊዜ ፕሪንት እንዳደረገ፣ መጥሪያ በሚመስል ልኬት እየቆራረጠ በማያይበት ቦታ እንዳስቀመጠ፣ ተጠራጥሮ ኮምፒውተሩን ሲያየው የቅስቀሳ ፅሁፍ እንደሆነ፤ ከዛም እንዴት እንዲህ አይነት ነገር እኔ ጋር ፕሪንት ታደርጋለህ? ሰርቼ እንዳልኖር ነው ወይ ብዬ ስጠይቀው፤ እሱ ጋር ፕሪንት ያደረገው ስለሚያምነው እንደሆነ እንደነገረው መስክሯል።

21ኛ ተከሳሽ አብዲሳ ኩምሳ ፡ አዱኛ ከራ የሚባሉ ሲሆን ተከሳሹን በ9-04-08 ዓ.ም ኦሮምያ ክልል ም/ሸዋ ዞን ጃጂ ከተማ ኃይሉ መጋዘን አካባቢ ከጓደኞቻቸው ጋር ሰብሰብ ብለው በሚጫወቱበት ሰዓት እንደተመለከቱትና ተጠርጣሪው ለአካባቢው አዲስ መሆኑን ተገንዝበው ለፖሊስ ጠቁመው እንዳስያዙት ገልጸዋል፡፡

ሌላው ምስክር ኢንስፔክተር አባተ ፈለቀ በኢሉ ገላን ወረዳ ተከሳሽ አብዲሳ ኩምሳን እንዳዩት ገልፀው የወረዳው አስተዳዳሪ እና የፀጥታው ሀላፊ ይዘውት እንደመጡ፤ ተከሳሹ በኢሉ ገላን ወረዳ ይኖር እንደነበረ እና አዲስ አበባ ቆይቶ በታህሳስ 9/2008 ተመልሶ እንደመጣ በፖሊስም ይፈለግ እንደነበረ የፀጥታ አላፊው ሲናገሩ እንደሰሟቸው ተናግረዋል፡፡ ተከሳሹም በፈቃዱ በአዲስ አበባ ከተማ ኳስ ሜዳ የሚባል አካባቢ በየሳምንቱ እሁድ እሁድ የሚሰባሰቡበት ማህበር እንዳለ፤ የኦነግ አባል እንደሆነ እና ሌሎቹም እንደሱ የኦነግ አባላት መሆናቸውን፤ ማህበሩ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ፣ ገንዘብ ያዥ፣ ፀሃፊ እና ም/ፀሃፊ እንዳለው፤ በየሳምንቱ አቅማቸው የፈቀደውን ለኦነግ እንደሚያዋጡ ሲናገር እንደሰሙት ተናግረዋል፡፡ እኚህ ምስክር 21ኛ ተከሳሽ አብዲሳ ኩምሳን ከተከሳሾች ለይተው ማሳየት አልቻሉም።

የምስክሮች ዝርዝር

ተከሳሾችን መለየት ያልቻሉ ምስክሮች

አቃቤ ህግ ካቀረባቸው ምስክሮች ውስጥ 7 ምስክሮች፡

1. ታደሰ ታፈሰ

2. እንዳለ በርሄ

3. ፍቅረአለም አዳነ

4. ሀብታሙ ሀይሌ

5. አብርሃም ሀይሌ

6. አብርሃ ወልዴ እና

7. ኢንስፔክተር አባተ ፈለቀ ፍርድ ቤት ቀርበው የሚመሰክሩበትን ጉዳይና የተከሳሹን ስም ከተናገሩ በኋላ በፍርድ ቤቱ ዳኖች ተከሶሾቹን እንዲለዩ ቢጠየቁም ማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል።

አቃቤ ህግ 4 ተከሳሾች ላይ ቀጥተኛ ምስክርም የደረጃ ምስክርም ማቅረብ አልቻለም ከታሰሩ ከ1 አመት በላይ ቢያስቆጥሩም እውቁን ፖለቲከኛ በቀለ ገርባን ጨምሮ 4 ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ ምስክር አልቀረበባቸውም፡፡ 1. 4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ 2. 9ኛ ተከሳሽ ፈራኦል ቶላ 3. 10ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ደረጀ 4. 13ኛ ተከሳሽ አሸብር ደሻለኝ የደረጃ ምስክሮች ነገር የፌደራል አቃቤ ህግ 17 የሚደርሱ የደረጃ ምስክሮች ፍርድ ቤት አቅርቦ ያሰማ ሲሆን አብዛኞቹ ተመሳሳይ ምስክር ሰጥተዋል።

በተለምዶ የደረጃ ምስክር የሚባለው ተከሳሾቹ በቁጥጥር ስር ውለው መኖሪያ ቤታቸው ሲበረበር የተመለከቱ፤ ከተከሳሾቹ መኖሪያ ቤት ወረቀት ሲገኝ አይተናል ብለው ወረቀቱ ላይ የፈረሙ፤ ተከሳሾቹ ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ በነበሩበት ወቅት ከተከሳሾቹ ኢሜል አድራሻ፣ ፌስቡክ አካውንት፣ ኮምፒውተር፣ ሚሞሪ ካርድ ፅሁፎች ፕሪንት እየተደረጉ ሲወጡ የተመለከቱ ግለሰቦች ናቸው።

የደረጃ ምስክሮች ዝርዝር

1. ዘመኑ በየነ፣

2. ሳሙኤል ተሾመ

3. ሰላም ውድነህ፣

4. ታደሰ ታፈሰ፣

5. አቶ ሞሌ ጌታነህ

6. ፍቅረአለም አዳነ፣

7. እንዳለ በርሄ

8. ዘሪሁን ታምሩ፣

9. ሻምበል አሰፋ ተሾመ

10. ተስፋዬ ጎሽሜ፣

11. ሀብታሙ ሀይሌ

12. ተክሌ ገ/ህይወት

13. ግሩም አለማየሁ፣

14. ዳንኤል ደረጀ

15. አብርሃም ሀይሌ

16. ስጋቲ ከድር፣

17. አብረሃ ወልዴ ከላይ የተዘረዘሩት ምስክሮች ከዚህ ቀደም በብዙ የምስክር ሂደቶች ላይ እንደሚስተዋለው ሁሉ ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ለስራ ጉዳይ ሄደው ፖሊስ በታዛቢነት እንዲገኙ የተጠየቅን ነን ብለው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የደረጃ ምስክሮች ለፍርድ ቤቱ ሲናገሩ ተከሳሹ ካለምንም ጫና የተከሳሽነት ቃሉን ሲሰጥ እንደታዘቡ፤ አንዳንዶቹም ተከሳሹ ሻይ ተጋብዞ እየጠጣ እየተሳሳቀ ነበር በሙሉ ፍቃደኝነት ቃሉን የሰጠው ብለዋል። በተከሳሽ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ ወቅትም ከዚህ በፊት በፖሊስ እየተደወለላቸው ብዙ መዝገብ ላይ መስክረው እንደሚያውቁ ያመኑ የደረጃ ምስክሮችም አሉ። የ2ኛ ተከሳሽ ቤት ሲበረበር የተገኙት ዘመነ በየነ የተባሉት ታዛቢ “የአቶ ደጀኔ ጣፋ ቤት ሲበረበር ፖሊስ የብርበራ ትእዛዝ ወረቀት አልያዘም ነበር፤ በብረበራ ወቅት የተገኙ ወረቀቶች፣ ሲዲዎች ላይ አቶ ደጀኔም ታዛቢዎችም የፈረሙ ሲሆን ብርበራው ሊጠናቀቅ መጨረሻ አካባቢ እቃ ቤት ውስጥ የኦነግ ባንዲራና በራሪ ወረቀቶች ተገኝተዋል፤ አቶ ደጀኔም የኔ ስላልሆነ አልፈርምም ብለዋል” በማለት የደረጃ ምስክሩ አስረድተዋል።

የ3ኛ ተከሳሽ አቶ አዲሱ ቡላላ ቤት ሲበረበር በታዛቢነት ተገኝቻለሁ ያሉት ሌላኛዋ የደረጃ ምስክር ሰላም ውድነህ የአቶ አዲሱ ቡላላ ቤት ሲበረበር ላፕቶፕ፣ ሲዲዎች፣ ጽሁፎች፣ መጽሃፎች፣ ሞባይሎች እንደተገኙ ገልጸዋል፡፡ ምስክሯ በአቶ አዲሱ ቤት ሻንጣ ውስጥ ከልብሶች በላይ የኦነግ መተዳደሪያ ደንብ፣ እንዲሁም ከሻንጣው ላይ በወረቀት ተጠቅልሎ የኦነግ ባንዲራ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ አቶ አዲሱ የኦነግ ባንዲራና መተዳደሪያ ደንቡ የእሳቸው እንዳልሆነ በመከራከር አልፈርምም ብለው እንደነበር፣ ነገር ግን ታዛቢዎቹ ‹‹እኛም እኮ ይህ ቤትህ ውስጥ ስለመገኘቱ እንጂ ያንተ ነው አላልንም፤ ስለዚህ መፈረም አለብህ›› በሚል አግባብተው እንደፈረመ መስክረዋል፡፡

2ኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ እና 3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ ላይ ከመሰከሩ የታዛቢ ምስክሮች ውጩ ያሉ ታዛቢ ምስክሮች ሁሉም ተመሳሳይ ጭብጥ ያለው ምስክርነት ሰጥተዋል።

የኦፌኮ አመራሮች የክስ ሂደት በዚህ ሳምንት ይቀጥላል…

Ethiopia Human Rights Project·Monday, March 27, 2017

LEAVE A REPLY