“በሁሉ ነገር መስማማት አለብን ወይ?” -ዲ. ዳንኤል ክብረት /ያሬድ ሹመቴ/

“በሁሉ ነገር መስማማት አለብን ወይ?” -ዲ. ዳንኤል ክብረት /ያሬድ ሹመቴ/

4ኛው ዙር የጉዞ ዓድዋ ተጓዦችን በክበር ለመቀበል በተዘጋጀው ምሽት ላይ ውብ ንግግር ካደረጉ መሀል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይገኝበታል። ንግግሩን ለንባብ እንዲመች አድርጌ በመጻፍ እነሆ ብያለሁ። በእለቱ ገና ከእስራኤል ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ከአውሮፕላን ማረፊያ እንደወረደ መምጣቱን፥ ለጉዞ ዓድዋ አባላት ያለውን ክብር ለማሳየት መገኘቱን፥ በመግለጽ ሰላምታ ሰጥቶ ንግግሩን ጀምሯል።

እነሆ ንባብ
።።።

…እስራኤልን ታውቃላችሁ ብዙውን ግዜ ትነሳለች በጦርነቱም በሰላሙም። ብዙ የሚያስጎበኙት ታሪካዊ ቦታ አላቸው። ብዙው ጉብኝቶቻቸው ኃይማኖታዊ ቱሪዝም ጋር የተገናኘ ነው። አብዛኛውን ነገር (የክርስትና እምነትን) የሐገሩ ዋና ዜጎች አያምኑበትም። ከነሱ እምነት ጋር ግንኙነት የለውም። ግን አለም በሙሉ የሚተራመስበት ትልቅ ገበያ አለው።

አለም በሙሉ ስለሚፈልገውም እነዚያ ቦታቸው ተከብረው፥ ተጠብቀው፥ ሁል ግዜ ዝናቸውም እየተወራ ይጠቀሙበታል። እስራኤሎች እንዲህ ይላሉ፡-

“ሙሴ ይሁን ሁሉ ቦታ ዞሮ ዞሮ መጨረሻ እስራኤል የመጣው ነዳጅ የሌለበት ሀገር ፈልጎ ነው ወይ? ብዙ ነዳጅ ያለበትን ሀገር ትቶ ነዳጅ የሌለበት ሀገር ለምን መጣ” ይላሉ ብዙ ግዜ።

እስራኤል ነዳጅ የላትም። ወይም ማዕድን የላትም። ትልቁ ማዕድኗ ታሪኳ ነው። እሱን ነው በዶላር እየመነዘረች የምትኖረው። ታሪኩን አያምኑበትም። ግን ትልቅ ሀገራዊ ጥቅም አለው።

ሁል ግዜ እነሱን ሳይ የእኛ ነው ትዝ የሚለኝ። ኢትዮጵያ እንግዲህ ወጥቶ እስክናየው ድረስ እስካሁን ነዳጅ የላትም…(ሳቅ) ወይም በጣም ያን ያህል እንደ ደቡብ አፍሪካና እንደ ኮንጎ በማዕድናት ሀብት የምታገኝ ሀገር አይደለችም። ወይም ብዙ ቴክኖሎጂ የምትሸጠው የላትም። የተሰራ ግን ብዙ ሀብት አላት። ዓድዋን የመሰሉ ብዙ ታሪክ አላት። የኛ ስንፍና ከነሱ የሚለየው መሸጥ አልቻልንም። መግለጽ አልቻልንም።

አንዳንዴም በሁሉም ነገር እንድናምንበት እንፈልጋለን። ትዝ ይለኛል በአንድ ወቅት ለንደን ውስጥ ከአንድ የሀገሩ ዜጋ ጋር ተገናኝቼ ስናወራ ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ አወራን። እንዲህ አለኝ፡-

“ጃማይካውያን እና ሌሎቹ አፄ ኃ/ሥላሴ አምላክ ናቸው ይላሉ” አለኝ።

“አይ ይህንን አናምንም አፄ ኃ/ሥላሴ የሚባል አምላክ አናውቅም” አልኩት።

“እናንተ ኢትዮጵያውያን እኮ የምትገርሙኝ ምን አገባችሁ ቢያመልኩ? …(ከፍተኛ ሳቅ)… አምላክ ናቸው ብለው ይጉረፉ። እናንተ አትመኑ። ለምን ትከላከላላችሁ?… ምነው እኛ ጋር በሆኑ እና አምላክ ናቸው ብለው በመጡ። ማምለኪያ ቦታ እናዘጋጅላቸዋለን። ብቻ ዶላሩን ብቻ ያምጡት። ከማመን ካለማመን ጋር ምን ያያይዘናል” አለኝ።

እውነቱን ነው። በሁሉም ነገር እንድንግባባ እና የኃይማኖት ያህል እንድንይዘው እንፈልጋለን። እንደዛ ሊሆን አይችልም። ዓድዋን ያህል ትልቅ ጉዳይ ገና እንጨቃጨቅበታለን። አንድ አንዴ ያላለቀ ያካዳሚ ክርክር ሁሉ ወደ ኤፍ ኤሙ ይመጣል። … ሌሎቹ የተቀበሉትን ያህል እኛ ለማመን ለምን ከበደን?

አሜሪካውያም የጻፉትን እያነበብን ነው። አፍሪካውያን ያሉትን እያደመጥን ነው። በዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር፡- ዓድዋ ላይ በነበረው ስነ ስርዓት፥ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኢምቤኪ የተናገረውና እኛ የተናገርነው በጣም ይለያያል። እነሱ ይሔን ያህል እያሉ እኛ መሸጥ ለምንድን ነው የከበደን?

እስኪ ዓድዋን ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን አሜሪካ ውስጥ ነው ብላችሁ አስቡ እስኪ – ለጥቂት ግዜ …

ምን የሚሆን ይመስላችኋል? (ሳቅ)… በየአንድ አንዳችን የመማሪያ መጻህፍት ውስጥ ዓድዋ ይኖራል።… አሜሪካ ስለሆነ ለዲቪ ስንል እናጠናዋለን።… አሜሪካ ስለሆነ ምን አልባት ከሚመረቱ ሞባይል ስልኮች መሀል አንዱ ዓድዋ ይሉታል። (ረዥም ሳቅ) ከአፕሊኬሽኖቹ አንዱ ዓድዋ የሚባል ይሆናል። ዓድዋ የሚባል ፋሽን ይኖራል። አግጠኛ ነኝ እኛም ከምንወልዳቸው ልጆች መሀል ቢያንስ አንዱን ዓድዋ ብለን እንጠራዋለን። ታሪኩ ያን ያህል ግዙፍ ሆኖ እያለ፥ እንደ አለመታደል ሁኖ ዓድዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ። … ዓድዋ የሚያሳዝነኝ በሱ ነው።

ለግዙፉ ዓድዋ እስከ አሁን እኮ ምንም አይነት ሙዝየም አልሰራንለትም አይደል? … እንደው ዓድዋን እንዳይጠፋ ያደረገው እግዚአብሔር ሲፈጥረው ተራራ አድርጎ ስለፈጠረው ነው። (ሳቅና ጭብጨባ)… ተራራ ስላደረገው ነው። እሱን ምንም ማድረግ ስለማይቻል። ያም ተራራ ደግሞ ወደ መሀል ሀገር የመጣ ተራራ ቢሆን፥ ወይ ለመንገድ፥ ወይ ለድልድይ እምንንደው ይሆን ነበር። (ከፍተኛ ሳቅ)

ስለ ዓድዋ የሚወራው በአመት አንዴ – እሷም ተቆጥባ። እስኪ ጋዜጠኞች እዚህ አላችሁ። ስለ ቫላንታይንስ ደይ ቀኑን ሙሉ ያወራችሁትን እና የዓድዋ እለት ያቀረባችሁትን እናንተው መዝኑት። ይሔ ሁሉ ዘፋኝ ባለበት ሀገር። እንግዲህ በቀን ከአንድ በላይ ዘፈን ይወጣል። ካሴት ባይወጣ ነጠላ ዜማ ይወጣል። ባለፈው የ121ኛ አመት በዓል ሲከበር እኮ ስለ ዓድዋ 4 ሙዚቃዎች ብቻ ነው በሙሉ ራዲዮ ጣቢያዎቻችን ቀኑን ሙሉ ሲያጫውቱ የዋሉት። የለንማ!

ለጉንጭ ለአይን ለጆሮ ለባት… ሚሊየን ዘፈን አለ። ለዓድዋ ምንም የለንም። ይሔ ምንድነው የሚያሳየን? ምንድነው የሚነግረን? መኪና የምትነዱ ሰዎች ወይንም እንደኔ የምትሳፈሩ ሰዎች እንደምታውቁት፥ የፊዚክስ ህግም እንደሚነግረው መኪና መንቀሳቀስ ሲጀምር መጀመሪያ ወደ ኋላ ብሎ ነው ከዚያ ወደፊት የሚሔደው። ማንኛውም ነገር ወደፊት ለመሔድ ከኋላ ተንደርድሮ ነው የሚነሳው።

ይሔ ታሪካችን ከኋላ አስፈንጥሮን፥ እንዴት የዓድዋው ጀግና ስንዴ እለምናለሁ? የሚል ቁጭት ወልዶ፥ የዓድዋው ጀግና እንዴት መለያየትን አሸንፌ ህብር ያለው አንድነትን መፍጠር ያቅተኛል? የሚል ትውልድ ካልፈጠርን እኮ፥ በዓድዋ ልክ ከፍ ልንል አንችልም።

ዓድዋን በደንብ አድርገን መመንዘር አለብን። ወጣቶቻችን እንዲቆጩ፥ እንዲያዩት፥ ሁል ግዜ በህሊናቸው እንዲስሉት መስራት አለብን።

ቅድም (በምስጋናው ታደሰ) ሲዘረዘሩ የነበሩት፥ ከቅኝ ግዛት ለማምለጥ ምክንያት የሆኑ ምስጢራት፥ የአመራር ጥበብ ያልናቸው፥ አንድነት ያመጡ ጉዳይ ያልናቸውን፥ ሰብእና ያልናቸውን… ለምንድነው አሁን የማንጠቀምባቸው? ለምንድነው ኢትዮጵያዊ የአመራር ጥበብ የማይኖረን? ሁል ግዜ የአመራር ጥበብ ሲባል ከእንግሊዝኛና ከፈረንሳይኛ መተርጎም አለበት? በዓድዋ ከፍታ የሚራመድ ትውልድ፥ በዓድዋ ከፍታ የምትመራ ሀገር እንዲኖረን እኮ ዓድዋን ከፍ ማድረግ አለብን።

ዓድዋ ኢትዮጵያን ተራራ ላይ ክፍ አድጎ ሰቀላት። የኛ ትግል ከዚያ ታራራ አውርደን ከእግሩ ስር ለመጣል ነው።… አዲስ አበባ ውስጥ እኮ ‘የዓድዋ አደባባይ የት ነው?’ ተብሎ ቢጠየቅ ብዙ ሰው ይምታታበታል። በየከተሞቻችን ዓድዋ ለምንድነው የሌለው? “ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” ይባላል።

ኡጋንዳ ሒጄ የገረመኝ ነገር፥ እንደ አንድ ትልቅ ጉዳይ የሚያስጎበኙት ነገር የምድር ወገብ ነው። የምድር ወገብ የሀሳብ መስመር ነው እንደምታውቁት (ከፍተኛ ሳቅ)… ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ስለተማርኩት ጉጉት አደረብኝና ሔድኩ።

አስጎብኚው አንድ የሆነ ሳፋ ነገር አመጣ። መሀሉ የተቀደደ ነው። እዚህ ጋር ቁም አለኝ። ቆምኩ። መሀሉን ከድኖ ውሀ ጨመረበት። ክዳኑን ሲለቀው፥ ውሃው ሰሜን ሲሆን ክሎክ ዋይዝ ይዞራል ደቡብ ደግሞ ሲሆን አንቲ ክሎክ ዋይዝ ይዞራል። ልክ ምድር ወገብ ላይ ሲሆን ደግሞ አዙሪት የለውም ቀጥ ብሎ ይወርዳል። “ይሔ ነው ምድር ወገብ በቃ” አለኝ (ከፍተኛ ሳቅ) እና? “አሁን አንተ ምድር ወገብን የጎበኘህ ሰው ስለሆንክ ሰርቲፊኬት ይሰጥሀል” ብሎ ሰርቲፊኬት ሰጠኝ። (ከፍተኛ ሳቅ)… እኔ ዓድዋ ስንት ግዜ ሔጃለው። ማንም ሰርቲፊኬት አልሰጠኝም። (ከፍተኛ ሳቅ) ሰው የሀሳብ መስመር እየሸጠ እኛ እንዴት የእውነት ተራራ፥ የእውነት ታሪክ መሸጥ ያቅተናል።

በግሪክ ሚቶሎጂ (አፈ ታሪክ) የግሪክ ወጣቱን አምላክ ሌላ ሴት አምላክ በፍቅር ወዳው እሱ እምቢ ብሏት፥ ሀይለኛ ስለነበረች ማልታ ውስጥ የሚገኝ ዋሻ ውስጥ አምጥታ አሰረችው” የሚል የግሪክ ሚቶሎጂ የአፈ ታሪክ አለ።

ማልታዎች ዋሻውን አፈ ታሪኩ ላይ እንዳለው አድርገው ሰሩት። አሁን ይጎበኛል። እኔም አይቼዋለሁ። “ታስሮ በነበረ ግዜ እዚህ ነበር ይተኛ የነበረው። ምግብ ደግሞ እዚህ ነበር የሚበላው” ውሀ አለ ደግሞ ዋሻ ውስጥ “እዚህ ነበር ገላውን የሚታጠበው።” እያሉ ያስጎበኛሉ። ተረት እኮ ነው የሚያስጎበኙት። ተረት። (ሳቅ)… እኔ እነ ስንዝሮ ያሳዘነልኑኝ ይህንን ሳይ ነው። (ከፍተኛ ሳቅ)… ስንዝሮ ለካ ሰው አጥቶ ነው እንጂ እንደዚህ ይሰራለት ነበረ! ስንዝሮን ዘፋኝ ብቻ አድርገነው መከራ ከምናሳየው።

በወታደራዊ ትምህር አንድ እግር በመሬት የሚሉት ህግ አለ። ከመዝለልህ በፊት አንድ እግርህ መሬት እንደያዘ ማወቅ አለብህ ይላሉ። አልያ ስትዘል ያልሆነ ድንጋይ ረግጠህ ልትወድቅ ትችላለህ ይላሉ። እኛም አንድ እግራችንን እንደ ዓድዋ አይነት ታሪካችን ላይ ተክለን ነው ወደፊት መስፈንጠር ያለብን። … እና ጉዞ ዓድዋ ይህንን ሀሳብ እንድንስፈነጠርበት ስላደረገን ያውም በአድካሚ እግር ጉዞ።

ያኔም አይደረግም የሚባለው ድል ነበር የተደረገው። ዛሬም በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በመኪና እንኳን መሔድ አሰልቺ በሆነበት ግዜ ጉዞ ዓድዋ በእግር በመሔድ ሁለቱን ታሪኮች እንዲገጣጠም ያደረገ ትውልድ ስለሆነ መቀጠል አለበት።

ሁል ግዜ ወጣቶቻችንን በመውቀስ ምንም አናመጣም። የሚሰሩትን በማበረታታት ነው ለውጥ የሚመጣው። ሊቃውንት እፍ… ያነዳል። እፍ… ያጠፈል። ይላሉ። ዋናው አጠቃቀማችን ነው።… እኛ ግን ብዙውን ግዜ እድል የምንሰጠው ለመጥፎዎቹ ነው።

… በየቀኑ መኪና የሚያጋጭ፥ በየቀኑ መብራት የሚጥስ፥ በየቀኑ የመንገድ ምልክቶችን የሚያፈርስ ሰው፥ እዚች ሀገር ውስጥ ታሪክ አለው። መንገድ ትራንስፖርት ብትሔዱ፥ “በዚህ ቀን ገጭቷል። በዚህ ቀን ይህን አደጋ አድርሷል” የሚል ትልቅ ፋይል አለው በስሙ የተከፈተ።… (ሳቅ) … ሃያ አመት አደጋ ሳያደርስ የነዳ ሾፌር ፋይል የለውም። (ሳቅ)… ስለዚህ እዚህ ሀገር ታሪክህ እንዲፃፍ አደጋ ማድረስ አለብህ ማለት ነው። መቼ ነው? “እገሌ እኮ የዚህ መኪና ሾፌር ሆኖ ምንም አይነት አደጋ ሳያደርስ ሃያ አመት አሽከርክሯል” ብሎ የሚሸለመው?

ራዲዮውም ጋዜጣውም ቴሌቪዥኑም ታሪካቸውን የሚዘግበው የአጥፊዎቹን ነው። የጎበዞቹን የሚናገር ማንም የለም። የዛሬ 40 አመት ታሪካቸው ለፊልም ቢፈለግ መዝገብ ላይ የሚገኘው የአጥፊዎቹ ነው። ሃያ አመት አደጋ ሳያደርስ ያሽከረከረው ሰው ፎቶው የለም ቪዲዮው የለም ፋይሉም የለም። ስለዚህ እድል እየሰጠን ያለነው፥ ለአጥፊዎች ነው ማለት ነው። ለውጥ ያመጡትን ሰዎች ወደፊት ባመጣን ቁጥር አጥፊዎቹ ራሳቸው እየጠፉ ይሔዳሉ። ስለዚህም ጉዞ ዓድዋን ማበረታታት አለብን።

ብዙ ያልተነገሩ ታሪኮች ያልተነገረላቸው ባለታሪኮች አሉ። ከመሪዎቹ ባሻገር ብዙ ያልተነገረላቸው ብዙ ጀግኖች አሉ። እውነት ይህ ትውልድ ቢበረታ ያልተነገረላቸውን ሰዎች ታሪክ እየፈለፈልን በአፈ ታሪክ ያሉትን በጽሁፍ ታሪክ መቀየር ነበረብን።

ተስፋ አደርጋለሁ። 125ኛው አመት የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር፥ ከዚህ በላቀ መንፈስ፥ ከዚህ በላቀ ሀገራዊ ስሜትና ከዚህ በላቀ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ከፍ ላለች ኢትዮጵያ እናከብረዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

አመሰግናለሁ።

                               ።።።

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!
#የዓድዋ_ድል_ይከበር_ይዘከር_ለዘላለም!!

ሼር በማድረግ ለወዳጆችዎ ያላፍሉ

LEAVE A REPLY