የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም መዘዝ አለው ተባለ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም መዘዝ አለው ተባለ

/Ethiopia Nege News/፦ ስድስተኛ ወሩን ያጠናቀቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣይ አራት ወራት እንዲራዘም መወሰኑን የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ማስታወቁን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ መሆኑ ታወቀ።

በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በሰፊው በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች በከፊል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማስቆም ካለፈው ኦክቶበር 2016 ጀምሮ የታወጀውና ለበርካታ ሰወች መሞትና ከ26ሺህ በላይ ሰዎች ጅምላ እስር እንደዳረገ የተዘገበው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣይ አራት ወራት እንደሚቀጥል ይፋ ሆኗል።

ላለፉት ስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠቅላይ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የአዋጁን ቀጣይነትና አሰፈላጊነትን አስመልክተው መግለጫ የሰጡ ሲሆን አሁንም ሀገሪቱን ሊያውኩ የተዘጋጁ ሃይሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የህዝብን ተቃውሞ በሃይል ማስቆም አይቻልም የሚሉ አስተያት ሰጭዎች ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝብን ተቃውሞ እንዲታመቅ አደረገው እንጂ እንዲታረቅ የሚያደርግ አለመሆኑን በመግልጽ ላይ ናቸው። አዋጁ ለአገዛዙ ቅርብ ሰዎች ገንዘብ ማካበቻ መሳሪያ ሆኗል የሚሉት አስተያየት ሰጭዎች አሁንም መንግስት ለህዝብ ጥያቄ አግባብ ያለው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እየቀለደ ሸፋፍኖ ለማለፍ የሚያደርገው ጥረት መዘዝ ሊያስከትል የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያምን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመንግስት ባለስልጣናት ህዙቡ ያነሳው ጥያቄ ተገቢ ነው በማለት ሲገልጹት በሌላ በኩል ደግሞ መንግስስትን በሃይል ለመጣል በሚል ውንጀላ በተቃዋሚዎችና ለሃገራቸው ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ላይ እስርና እንግልት ሲፈጽም እንደነበር አለም አቀፍ ተቋማት ሲዘግቡ መሰንበታቸው ይታወቃል።

Ethiopia Nege March 30, 2017/

LEAVE A REPLY