ኢሳት እና አዳዲሶች ብሄርተኞች /መስቀሉ አየለ/

ኢሳት እና አዳዲሶች ብሄርተኞች /መስቀሉ አየለ/

ሁለት ስህተት አንድ ትክክል አይሆንም! ኢሳት እና አዳዲሶች ብሄርተኞች

ሰሞኑን አንድ የኢሳት እንግዳ በአማራ ማንነት ላይ አላገጠ ተብሎ የተነሳ ቃጠሎ ጭሱ አ ሁንም ድረስ እየሸተተኝ ነው። ስለ እውነት ፕሮግራሙን አላየሁትም። ለማየት ያልፈለኩት ሰውየው ጠቃቀሳቸው የተባሉትን ነጥቦች በኮመንት ደረጃ ተጽፈው ስላየሁዋቸውና ነገሩ ያጠነጠነበት ጠቅላላ ጭብት በከፊልም ቢሆን ስለገባኝ እዛ ውስጥ ገብቶ መዳከሩ የሚያተርፍ አልመሰልህ ስላለኝም ነው።

ሁለት ነገር ግን አልገባኝ ብሎ ተቸግሬያለሁ
፩ኛ ለምን ኢሳት በየግዜው እረመጥ እየፈለገ በራሱ ላይ መነስነስ እንደሚፈልግ ግልጽ አልሆነልኝም። አንድ ነገር የግድ መነገር ያለበት እውነት እንኩዋን ቢሆን የራሱ የሆነ ወቅትና ግዜ አለው። ቀኑን ካልጠበቀ እውነት በሰዓቱ የምትነገር ሃሰት ቁጣን የማብረድ፤ ሰላም የማስፈን ሃይል እንዳላት አባቶች ሲያጠይቁ “ዋሽቶ ማስታረቅ” የሚሉትን ፈሊጥ መከተላቸው ለዚሁ ነውና።

ሌላው ነገር ደግሞ ኢሳት የነጻነት ትግሉን ወደ ፊት ለመግፋት ኢትዮጵያውያን በላባቸው ያቆሙት አጋዥ ሃይል፤ በብዙ አይዲዮሎጅና የታሪክ ትርምስ የተከፋፈለውን ህዝብ በአንድ ላይ ያሰባሰበ ተቁዋም እንደሆነ ነበር የሚታወቀው። ቢያንስ ባንድ ወቅት የተንጋለሉባትን አንዲት ማህጸን ለሁለት የሰነጠቁት ኢህአፓና ኢሰፓ አንድ ላይ ቁጭ ብለው የታሪክ ቁጭታቸውን ሲያወጡ ያየነው በዚሁ የኢሳት መድረክ ነበርና።

ጆርጅ ቡሽና ቶኒ ብሌዬር በተፈበረከ ውሸት ኢራቅ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው ገድለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አካል ጉዳተኛና ተፈናቃይ ሲሆኑ ዛሬ ድረስ አልበርድ ብሎ መካከለኛውን ምስራቅ ወደ ምድራዊ ሲዖልነት እየቀየረው ለመጣው እልቂት እነሱ የፈጠሩት የሃይል ሚዛን መዛባት ብቸኛው ምክኛት ነው። ይኽ ነገር በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የጸጥታው ምክር ቤት ባለሙያ ልኮ ቢያስጠናውም በአሜሪካና በእንግሊዝ ተጽዕኖ ምክንያት የጥናቱ ውጤት ለሚቀጥለው ስልሳ አመት ለህዝብ እንዳይገለጥ በወቅቱ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙንና በአሜሪካ አምባሳደር ብቻ በተስማሙበት ፓስወርድ በተባበሩት መንግስታት ካዝና ውስጥ ተቆልፎዋል። የመገናኛ ብዙሃኑ ጡንቻም ሆነ የህግ የበላይነቱ እንዲሁም የነጻ ተቁዋሙ ጥንካሬ አፈ ሰማያት ላይ በደረሰበት የምእራብ አገራት አፍንጫ ስር እንዲህ አይነት ኑፋቄ ሲፈጸም ማንም የሚዲያ ተቋም ትንፍሽ ያላለው አጋዚ ተፈርቶ አይደለም። ኢንተረስታቸውን ስለሚያቁት ነው። ኢሳት ከዚህ ከነሱ በላይ ቅዱስ ለመሆን የሚሞክር ይመስለኛል።

፪ ሌላው አዳዲሶቹ የአማራ መሳፍንቶች ለምን በማንነታቸው እንደሚሰማቸው ሊገባኝ ያልቻለው ነገር ነው።
አማራው በሽህዎች አመታት የተጋድሎ ታሪክ የገነባው የአቸናፊነት ስነልቦና እንዴት በወያኔ የሁለት አስርተ አመታት ተግዳሮት ተጨፍልቆ እንዲህ አይነት ሰዎች ሊፈጠሩ እንደቻሉ ቀመሩን ላገኘው አልቻልኩም።

፪፤፩ አየርላንድ ከእንግሊዝ ነጻ ለመውጣት ስምንት መቶ አመት ነው የተዋጋው። እንግሊዝ የባርነት ፍንገላውን የጀመረው በ አፍሪካ ሳይሆን በአይርላንድ በመሆኑ በእንግሊዝ ውስጥ በተሰሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸና የባህር ውስጥ ከተማ የሚመስሉ እንደ አልጋ ሽቦ የተጥለፈለፉ ናቸው የሚባሉትና በየቀኑ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ባቡሮች የሚርመሰመሱባቸው የከርሰ ምድር ውስጥ የባብሩ ሃዲዶች የተቆፈሩት በዋናነት በአይሪሾች ሲሆን ያም አልበቃ ብሎዋቸው ከራሳቸው ውስጥ ወታደር መልምለው ከኢሽያ ጫፍ አስትራሊያ-ህንድ -ኒውዚላንድ ወዘተ እስከ ደቡብ አሜሪካ ፎክላንድ ; ከላይ ክኬንያ ጫፍ እስከ ደቡብ አፍሪካ ያለውን ግዛት ሲወሩ የአይሪሽ ህዝብ ዝሆንና ግመል በመጎተትም፣ እንደ አህያ በመጫንም፣ በመወጋትም እራሱን ባርነት ሌሎቹም ላይ ለመጫን የራሱን ሚና ተጫውቶዋል። በባርነት ፍንገላ ወደ አዲሲቱ የአሜሪካ ግዛት ተጭኖ የሄደው አይሪሽ ዛሬ ቴክሳስና አላባማን ጨምሮ አብዛሃኛውን የደቡቡን ክፍል ይዞ በፋንታው ጥቁሮችን ባሪያ አድርጎ ሲኖር በዋናነት የዋሽንግተኑን የፖለቲካ መዘወሪያ ቁልፍ የያዙት የሰለጠኑት እንግሊዞች “የባሪያ ፍንገላን ስርዓት በአሜሪካ ምድር ሊቆም ይገባል” ሲሉ ባወጡት አዋጅ አልስማማም ብሎ የ አሜሪካንን ሲቪል ወር የተጀመረበት አንዱ መነሻ ለጥቁሮቹ የማዘንና ያለማዘን ሳይሆን ያው በአስራሁለተኛው መቶ ክፍለዘመን አውሮፓ ውስጥ የተጀመረው የአንግሎ-አይሪሽ ትንቅንቅ ሌላኛው መገለጫ እንደነበር የታሪክ ጸሃፊያን የተስማሙበት ነገር ነው። ዛሬ አይሪሹም ሆነ ጥቁሩ በማንነቱ የሚሰማው እንዲህ ያለ ጠባሳ በውስጡ ስላለ ነው።

ካሁን በፊት ለማሳየት እንደሞከርኩት በየትኛውም የአለም ጫፍ ያሉ ህዝቦች በአንድም በሌላም ከማንነታቸው ጋር የተያያዘ ጥቁር ጠባሳ የሌለባቸው የሉም። በአንድ ወቅት የሮማን ኤምፓየርን ግዛት መስርቶ አለምን ለስድስ መቶ አመት ያህል የገዛው ጣልያን እንኳን አድዋ ላይ የደረሰበትን የስነልቦና ጠባሳ ለማዳን ሲል እንድ ትልቅ ዋርካ የሚያህል የአክሱም ሃውልት ከኢትዮጵያ ወስዶ መሃል ሮም አደባባይ ላይ ተክሎ “ተሸንፌም እንዳልቀረሁ እወቁልኝ !!”ሲል መኖሩን በማስላት ብቻ የአድዋን ውበት መለካት እንችላለን። ሮም በአመት ሰላሳ ሚሊዮን ያህል ቱሪስት የሚጎበኛት ከተማ መሆኗ ይታወቃል። በአንጻሩ በየዘመኑ የሚነሱትን ሃያላን ልክ በማስገባት አኩሪ ታሪክ ያለው መሰረቱን በዋናነት በአሁኑዋ ራሽያና ሰርቢያ ላያ ያደረገው የስላቭ ህዝብም ሆነ የመጨረሃው ኤምፓየር በመሆን አለምን አሁን ባላት መልኩ ለመቅረጽ የቻለው እንግሊዝ ህዝብ ጋር የአማራው ህዝብ ተመሳሳይነት ያለው የስነልቦና የበላይነትን ገንዘብ ማድረግ የቻለው በዚሁ የወርቃማው የተጋድሎ ታሪኩ ነው።

ዛሬ ማንም ህዝብ መጥቶ እንግሎዞችንም ሆኑ የራሺያን ህዝብ ተሳድቦ ማበሳጨት የማይችለውና እነሱም ቢሆኑ ማንም ምን ቢል ጉዳይ የማይሰጣቸው በስድብ የሚቀየር ነገር ስለሌላ ብቻ ሳይሆን በስድብ ቀርቶ በጋለ ብረት የሚፈርስ ስነልቦነ ስለሌላቸውም ጭምር ነው። እስከ ማውቀውና እስከ ገባኝ ድረስ የአማራ ሆደ ሰፊነትና መረጋጋት ከዚህ ሁሉ የዳበረ የአቸናፊነትና የተረጋጋ ስነ ልቦና የበላይነት የመጣ መሆኑ ነው። ሌላው ቢቀር ማንም ሰው ያለ ብሄሩ መጥቶ የሚሰራበትና እግሩን ዘርግቶ የሚኖርበት ብቻ ሳይሆን ስልጣን ይዞ እንደፈለገ የሚሆንበት ክልል የአማራው ክልል እኮ መሆኑ አማራው ስለማያውቅ፣ ወይንም ሞኝ ስለሆነ፣ ወይንም ወያኔ አማራውን ያለ ተቆርቁዋሪ ለማስቀረት “ባእዳንን” በላዩ ላይ በመሾም አማራውን ለማቆርቆዝ የሚያሰላውን ተራ ስሌት ስለማያውቀውም አይደለም። አሁንም እለዋለሁ; በማንነቱ የማይሰማው፣ ወደ ሁዋላ አዙሮ በማየት የሚያክከው ቁስልና ውርደት የሌለው፣ ዘመኑን ሁሉ በተጋድሎ ታሪክ የጻፈ፣ ወደ ፊት ለመሄድ የስነልቦና አቅም ያለው፣ ከማንነት ወጥቶ ወደ ሰውነት ደረጃ ያደገ፣ በጥቅር ህዝብ ታሪክ ብቸኛው የሰው ዘር ነው።

ዛሬ ማንም ወጥቶ የፈለገውን ቢል ጥፍሬ ድረስ ዘልቆ ያንቀጠቅጠኝ ዘንድ እኔ መለስ ዜናዊ ወይንም ጃዋር መሃመድ ወይንም ጸጋዬ አራርሳን አይደለሁም። ኢሳት ግን እንደ አንድ በጸረ ወያኔ ግንባር እንደ ተሰለፈና ህዝቡን አንድ አድርጎ ወደ ቀራኒዮ የማድረስ አላፊነት እንዳለበት ብቸኛ ተቋም እንዲህ ያለ ነገር ውስጥ በየግዜው እየደረተ መቀጠሉ “ቢያንስ የተወሰኑ ሰዎችን ማስኮረፉ አይጎዳኝም፤ እኔ የዊኪ ሊንኩን ጁሊያን አሳናጅ ወይንም ኤድዋርድ ስኖውደንን መርህ እንጅ ቢቢሲንና ሲኤን ኤንንም የመሳሰሉትን አልከተለም” ካለና “ተጽእኖውን መቋቋም እችላለሁ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ባለው ትግል ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ የለውም ካለ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት ነው የምለው።

LEAVE A REPLY