ፊደል፥ ቋንቋ፥ ሕዝብ /ፕሮፌ. ጌታቸው ኃይሌ/

ፊደል፥ ቋንቋ፥ ሕዝብ /ፕሮፌ. ጌታቸው ኃይሌ/

አሁንም አሁንም የሚያገረሽብን ብሔራዊ በሽታ “የቱን ቋንቋ በየቱ ፊደል እንጻፈው የሚለው ጥያቄና የሚሰጡት የተለያዩ መልሶች ናቸው። አብዛኛው ተቺ የሚስማማበት አንድ መልስ ለማግኘት ባይቻልም፥ መጀመሪያ እነዚህ ሦስት ቃላት (ፊደል፥ ቋንቋ፥ ሕዝብ) ያላቸውንና የሌላቸውን ዝምድና ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። አቀራረቡ ትምህርት ቢመስልም፥ መማር ክፋት የለበትም። ፊደል፤ ድምፅን “ንግግር ያለበት” እና “ንግግር የሌለበት” ብለን ከሁለት ዓይነት እንክፈለው።

የመጀመሪያው “የንግግር ድምፅ” ይሉታል፤ ሰዎች ሲነጋገሩ የሚሰማው ድምፅ ነው። ያ የኆኄ ስብስብ ድምፅ ነው። ስብስቡ የቋንቋ ቃል ይሆናል። “ንግግር የሌለበት” ድምፅ ምንም ዓይነት ቋንቋ የማይሰማበት ድምፅ ነው። ለምሳሌ ዝናም ጣራውን ሲመታው፥ ዕቃ ሲጋጭ፥ መብረቅ ሲበርቅ፥ ጠመንጃ ሲተኮስ፥ . . . ድምፅ እንሰማለን፤ ግን ድምፁን ሰምተን የሆነውን ልንገምት ብንችልም፥ የቃልና የቋንቋ ድምፅ አንለውም። የቋንቋ ድምፅ የምንለው ሰዎች በአማርኛ፥ በእንግሊዝኛ፥ በፈረንሳይኛ፥ በጉራግኛ፥ በኦሮምኛ . . . ሲናገሩ የምንሰማው ድምፅ ነው። ሰዎች በአንዳች ቋንቋ ሲነጋገሩ ስንሰማ ቋንቋውን ባለማወቃችን ምን እንደሚሉ ባናውቅም የምንሰማው የቃላትና የቋንቋ ድምፅ መሆኑን እናውቃለን። ቋንቋ፤ ድምፅን “ንግግር ያለበት” እና “ንግግር የሌለበት” ብለን ከሁለት ዓይነት ከከፈልነውና የንግግሩን ድምፅ “ቋንቋ” ካልነው፥ ፊደል የቃላትና የቋንቋ ድምፅ ሥዕል ነው። ሕዝብ፤ ቋንቋ ይሰማል እንጂ በዓይን አይታይም። ታዲያ በዓይን የሚታይ ካልሆነ በጆሮ የሚሰማ እንዴት ይሣላል? ጥሩ ጥያቄ ነው። ግን የቋንቋ ድምፅ በዓይን ባይታይም በኅሊና ይታያል። አሁንም ችግር አለ፤ ያንዱ ሰው ኅሊና የሚያየው ቅርጽና የሌላው ሰው ኅሊና የሚያየው ቅርጽ አንድ ሊሆን አይችልም።

በልጅነቴ፥ “አጎትህ ሊጠይቀን ከዳር አገር ይመጣል” ሲሉኝ በኅሊናዬ እንዳባቴ ቀይ እና ረጅም መስሎ ታይቶኝ ነበር። ሲመጣና በዓይኔ ሳየው ትቁር አጭር ሆኖ አገኘሁት። አራት ሰዎች (ከቻይና፥ ከእንግሊዝ፥ ከጎንደር፥ ከየመን) ከፊቴ አቁሜ “ተ” ብዬ ብጮህ፥ አራቱም ይሰሙኛል። የሰማችሁትን ድምፅ ሳሉልኝ ብላቸው፥ የሚያሳዩኝ አራት የተለያዩ ሥዕሎች ነው። የአንድን ቋንቋ ቅርጽ የሚያዩ ያንን ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ ተመራማሪዎች ናቸው። ፊደል በየሀገሩ የተለያየ ሥዕል የሆነው ስለዚህ ነው። የቻይና ተመራማሪዎች፥ የዐረብ ተመራማሪዎች . . . ለቋንቋቸው የሣሏቸው ፊደሎች የተለያዩ የሆኑት የተለያዩ ኅሊናዎች ያዩዋቸው ቅርጾች በመሆናቸው ነው።

ፊደልን በኅሊና ማየትና መሣል ቀላል ነገር ስላይደለ፥ ለሥልጣኔ ኋላ-ደረስ የሆኑ ሕዝቦች የሚያደርጉት ካሉት ፊደሎች ውስጥ አጠገባቸው ያገኙትን ወስደው መጠቀም ነው። ግሪኮችና ላቲኖች፥ በኋላም ሞላው የአውሮፓ ሕዝቦች ያደረጉት ይኸንን ነው። ፋርሲ በዐረብኛ ፊደል የሚጻፈው በእስልምና ሃይማኖት ምክንያት ፊደሉ እዚያው ኢራናውያን አጠገብ ስለተገኘ ነው እንጂ ፋርሲ እና ዐረብኛ ምንም ግንኙነት የላቸውም። ፊደል፥ ቋንቋ፥ ሕዝብ የሥጋ ዝምድና የላቸውም። ሕዝብ የቋንቋ እና የፊደል ፈጣሪ ነው። ሕዝብ ቋንቋን የሚፈጥረው አብሮ በመኖር ነው። ሰዎችን አንድ ሕዝብ የሚያደርጋቸው አብሮ በመኖር የፈጠሩት ቋንቋና መሰሎቹ የጋራ ቅርሶች፥ የጋራ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ታሪካቸው ናቸው። ፊደልና ቋንቋ ዝምድና የላቸውም። ያዛመዳቸው የሰው ልጅ ኅሊና ነው። ማንኛውም ፊደል የኅሊና ልጅ ስለሆነ፥ ለማንኛውም ቋንቋ ያለው ቅርበትም ሆነ ርቀት እኩል ነው። ለምሳሌ፥ የዐረብኛ ፊደል ለዐረብኛ ቋንቋ ያለው ቅርበት ለእንግሊዝኛ ካለው ቅርበት አይበልጥም፥ አያንስምም። እንግሊዝኛ በዐረብኛ፥ በአማርኛ፥ በዕብራይስጥ . . . ፊደል ሊጻፍ ይችላል ማለት ነው። አማርኛ፥ ዐረብኛ፥ አደርኛ፥ . . . በላቲን፥ በግሪክ፥ በዕብራይስጥ ፊደል ቢጽፏቸው እምቢ አይሉም። ማንኛውም ፊደል ለማንኛውም ቋንቋ መጻፊያ ሊሆን ይችላል።

የኢትዮጵያ ፊደል፤ ኢትዮጵያ የትም ከሌላ አገር የማይገኝ የራሷ ፊደል አላት። የሩቅ ምሥራቁን (የቻይናን የኮሪያን . . .) ለብቻ ትተን የቀረውን ስናየው የተለያዩ ቋንቋዎች ፊደሎቻቸው ዝምድና እንዳላቸው ምልክት እናያለን። በላቲንና በኢትዮጵያ ፊደል መካከል ያለው ዝምድና እንኳን ደብዛው ፈጽሞ አልጠፋም። ለምሳሌ እነዚህን እናስተያያቸው፤ አ (A), ተ (t), መ (m), ወ (w), ቀ (q). ግን ከፊደሎች ሁሉ ከኢትዮጵያው ፊደል ጋር የበለጠ ዝምድና የሚታይበት “የደቡብ ዐረብ” ወይም “የሳባውያን” የሚባለው ፊደል ነው። ሆኖም፥ የፊደሎችን ተመሳሳይነት በማየት ብቻ “ዝምድናቸው አንዱ የሌላውን ከመውሰድ የመጣ ነው” ማለት አይቻልም። ይቻል ቢሆንማ፥ “የላቲን ፊደል ከኢትዮጵያ ፊደል የተወሰደ ነው” እንል ነበር። አንዱ ከሌላው (የሳባው ከኢትዮጵያው ወይም የኢትዮጵያው ከሳባው) ላለመውሰዱ ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፥ ተመሳሳይነታቸው ፍጹም አይደለም። ፍጹም ማለት እንደ እንግሊዝኛ፥ እንደ ፈረንሳይኛ፥ እንደ ጣሊያንኛ ፊደሎች መመሳሰል ነው። ሁለተኛ፥ የሌሎቹ ፊደሎች በ “አ” ጀምረው ሲዘልቁ፥ የኢትዮጵያው የሚጀምረው በ “ሀ” ነው። ስለዚህ፥ ለማለት የሚቻለው፥ “አንድ ጥንታዊ ሕዝብ የጀመረውን ፊደል ሌሎች ሕዝቦች ወስደው ለራሳቸው ቋንቋ መጻፊያ እንዲሆን አስተካክለውታል።

ከነዚህ ሕዝቦች ውስጥ ኢትዮጵያውያንና ሳባውያን ይገኙበታል” ነው። የኢትዮጵያ ፊደልና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፤ የኢትዮጵያ ፊደል ከምንጩ የተቀዳውና የተስተካከለው የግዕዝን ቋንቋ ለመጻፊያ ነበር። በዚያ መሠረት፥ ግዕዝን እስከዛሬ እያገለገለ ነው። ከዚያ ቀጥሎ የአማርኛ መገናኛነት ሲስፋፋና የትምህርቱ ኀላፊዎች፥ ማለትም አስተማሪዎቹና ደራሲዎቹ፥ አማሮች ሲሆኑና፥ በዚያ ላይ የውጪ ሰዎች ሃይማኖታቸውን በአማርኛ ማስተማር ሲጀምሩ፥ ላለመቀደም፥ በአማርኛ መጻፍ አስፈለገ።

“አንድ ቋንቋ የሌላውን ፊደል መውሰድ ሲያስፈልገው፥ መምህራኑ የሚወስዱት አጠገባቸው ያገኙትን ፊደል ነው” ባልኩት መሠረት፥ የአማራ መምህራን የግዕዝን ፊደል ወሰዱ። የወሰዱትን የግዕዝ ፊደል ለአማርኛ እንደሚያስፈልገው አስተካክለው እነሆ እየሠራንበት ነው። ማስተካከል ማለት የግዕዝ ፊደል ኆኅያት ለአማርኛ ቋንቋ አልበቃ ስላለ የሚያባቁ ኆኄያት ፈጠሩለት ማለት ነው። ለምሳሌ፥ በግዕዝ ፊደል “ጀመረ”፥ “ጨረሰ”፥ “ሸኘ”፥ “ቸኮለ” ብሎ መጻፍ አይቻልም። ምክንያቱን በግዕዝ ፊደል ውስጥ “ጀ”፥ “ጨ”፥ “ሸ” ፥ “ኘ”፥ “ቸ” የሉም። አማሮች የነዚህ ኆኄዎች ምንጮች የቶቹ የግዕዝ ኆኄዎች እንደሆኑ አጥንተው፥ “ጀ”ን ከ “ደ”፥ “ጨ”ን ከ “ጠ”፥ “ሸ”ን ከ “ሰ”፥ “ኘ”ን ከ ”ነ”፥ “ቸ”ን ከ “ተ” አስወለዱ። ማንኛውም ፊደል ለማንኛውም ቋንቋ መጻፊያ ሊሆን ይችላል ባልኩት መሠረት፥ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በገበያ ላይ ካሉት ፊደሎች (የግሪክ፥ የላቲን፥ የዐረብኛ፥ የቻይና፥የኢትዮጵያ . . . ፊደሎች) የትኛውንም ፊደል መርጠው ሊወስዱ ይችላሉ። ግን በሚወሰድበት ጊዜ፥ እንኳን ፊደልን ያህል ትልቅ ነገር ቀርቶ፥ ነገ አርጅቶ የሚጣል ዕቃ እንኳን የሚገዛው አማርጦ፥ አገላብጦ አይቶ፥ ይበልጥ የሚስማማ የመሰለው ተመርጦ ነው።

አውጥተን አውርደን ስናየው፥ ምርጫው ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያ ከሆነ፥ በብዙ ምክንያት፥ ከኢትዮጵያ ፊደል የተሻለ ፊደል የለም። አንደኛ፥ አጻጻፋችን ከቋንቋው ጋር አብሮ ይሄዳል። ቋንቋው ሲለወጥ አጻጻፉም (the Spelling) አብሮ ይለወጣል፤ ተለውጦ በጊዜው ትክክል የሆነው ቃል ይጻፋል። ለምሳሌ፥ ዱሮ “ኸየት”፥ “አንቲ” ነበር የሚባለው። ወደሸዋ ስንመጣ “ኸየት” ተለውጦ “ከየት” ሆኗል፤ “አንቲ” ከሁሉም አገር “አንቺ” ሆኗል። አጻጻፉ አብሮ የማይለወጥ ቢሆን ኖሮ፥ አሁንም የትም ቦታ “ኸየት”፥ “አንቲ” እያልን እየጻፍን፥ “ከየት”፥ “አንቺ” እያልን (ያልተጻፈውን) እናነብ ነበር። ምሳሌውን ከእንግሊዝኛ ባመጣ የበለጠ ይብራራ ይሆናል። ለምሳሌ፥ በእንግሊዝኛ laugh, doubt የሚሉ ቃላት አሉ። ቃላቱ ተለውጠው ሳለ፥ አጻጻፉ (the Spelling) ባለመለወጡ አሁንም የሚጻፈው laugh, doubt እየተባለ ነው። ቃላቱ ግን ተለውጠው laf, dout ሆነዋል። የአጻጻፍ ልምዳችን የተማርነውን ሳይሆን የምንሰማውን ነው። የአማርኛ ፊደል የሚመረጥበት ሁለተኛው ምክንያት “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” የሚባለው ነው። የሚፈለገው ለመጻፍ ከሆነ የሌላ አገር ፊደል የሚመረጥበት ምክንያት የለም። ስለኦሮምኛ አጻጻፍ በምንወያይበት ጊዜ፥ “የላቲኑ ፊደል የተመረጠው፥ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ነው” የሚለው ክርክር ይነሣል። አያዋጣም፤ “የአማራ ፊደል አንፈልግም” ብሎ እቅጩን መናገር እውነተኛ ያደርጋል። አጥኒዎቹ ምርጫ የሚደረገው ለመጻፍ መሆኑን ብቻ ዓላማቸው ያደረዱ ገለልተኞች የቋንቋ ምሁራን መሆን አለባቸው። ሦስተኛው ምክንያት፥ ብሔራዊ አንድነት ነው። አንድ አገር አንድ ፊደል። በሰማንያ ጎሳ ላይ ሰማንያ ፊደል ማምጣት፥ ለሀገራችን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሆናል። አራተኛው ምክንያት፥ ቋንቋው ያልሆነ ብሔራዊ ዜጋ ሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋ ለመማር ቢፈልግ አዲስ ፊደልና አዲስ አነባበብ መማር አያስፈልገውም።

የኢትዮጵያ ፊደል የሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያ እንዲሆን ተሞክሮ ፈተና አልፏል። “ወድቀሃል” አንበለው። “የአማራን ባህል አያሳዩን፥ አታሰሙን” ከሚሉ ሰዎች መካከል፥ “የኢትዮጵያ ፊደል እንኳን ለሌላዎቹ ቋንቋዎች ለአማርኛም አይስማማውም” የሚሉ አሉ። እንዲህ የሚሉ ፊደላችንን ለማጣጣል እንዲመቻቸው ነው እንጂ፥ እውነት ለአማርኛ አዝነውለት ወይም በአማርኛ የሚጽፉ ሰዎች ሲቸገሩ አይተው አይደለም። የትኛውን የግዕዝና የአማርኛ መጽሐፍ ነው በኢትዮጵያ ፊደል ስለተጻፈ ሳናነበው ያለፍነው? አንዳንዶቹን መጻሕፍትማ ከመውደዳችን የተነሣ፥ ከእጃችን እንዳይወጡ እስከምንፈልግ ድረስ እንንከባከባቸዋለን። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፤ አንባቢ ልብ ብሎት ከሆነ፥ “ፊደል የሚመረጠው ለመጻፍ ከሆነ” የሚል ሐረግ ደጋግሜ ጽፌያለሁ። ፖለቲካም አለበት ለማለት ነው። ለአማርኛ ባህል ቢደብቁት የማይደበቅ፥ እንደ እሳት የሚያቃጥል ጥላቻ አለ። “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወገጥ” እንደሚሉ፥ አማርኛም በአማሮች ላይ ከተሰነዘረው ጥላቻ ገፈት ቀማሽ ሆኗል። የአማርኛን ቋንቋ ለልጆቻችን አናስተምርም ማለት የፍቅርና የአብሮ መኖር ምልክት አይደለም። አንዳንዶቹማ፥ “ኦሮሞዎች የኢትዮጵያን ባንዲራ ተሸክመው ማይጨው የዘመቱት ተገድደው ነው” እስከ ማለት ደርሰዋል። ይህን ለማለት እስከነ ክቡር ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ኅልፈት ድረስ መታገሥ አልቻሉም።

“ኦሮሞዎች ለኦሮምኛ የሚስማማውን ፊደል (ላቲንን) መርጠውለታል፤ ይህ ያለቀ፥ የደቀቀ ጉዳይ ነው፤ ኦሮሞ ያልሆኑትን የሚገዳቸው ጉዳይ አይደለም” የሚሉም ሰምቻለሁ። እውነት ነው፤ ጉዳዩ የኦሮሞዎች ብቻ ከሆነና ኦሮሞዎች ከተስማሙበት በጥላቻ ላይ የተመሠረት ምርጫ ሊያደርጉ ይችላሉ። ኦሮምኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ከታሰብ ግን፥ ጉዳዩ ብሔራዊ እንጂ የኦሮሞዎች ጉልማ ሊሆን አይችልም። ጥያቄውም ከሌሎቹ ቋንቋዎች ይልቅ በኦሮምኛ ላይ የሚነሣው በዚህ ምክንያት ነው። የእነሱ ፖለቲከኞች ቋንቁቸውን የአማርኛ ባላጣ አላደረጉም። አማሮች ኢትዮጵያን የመሰለች አገርና መንግሥት ለመፍጠር፥ ትምህርት ለመዘርጋትና ሕዝቧን በዓለም ደረጃ ለማስከበር ምክንያት ሆኑ እንጂ፥ በአገሪቱም ሆነች በመንግሥቱ በረይቱማና ቦረን የተጠቀሙትን ያህል አልተጠቀሙም። በረይቱማና ቦረን ነባሩን ሕዝብ ጨርሰው በሰባው መሬት ላይ ሰፍረዋል። ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆኑ አንዳንድ የአማራ ቤተ ሰብ በአጠገባቸው ቢያዩ፥ ለወያኔ ዕድሜ እየለመኑ ፈጇቸው። አማሮች “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” እያሉ ሲጮሁ፥ እነሱ “የኢትዮጵያን ባንዲራ አታሳዩን” እያሉ ይጮኻሉ። ምነው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ነገር “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ሆነብን!!

LEAVE A REPLY