ኦፈን ያ ጃገማ!! /በታሪኩ አባዳማ/

ኦፈን ያ ጃገማ!! /በታሪኩ አባዳማ/

ኦፈን ያ ጃገማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ጣሊያን ግራ ገባው መብረቅ አይጨበጥ
ሲያስገመግም እንጂ አይታይ ሲያደፍጥ
ከቶ ምን ፍጥረት ነው እንዲህ የሚያራውጥ!!
ደንዲ አፋፉ ላይ ታይቷል ሲባል ጀግናው
ግንደበረት ወርዶ ጣልያንን አጨደው።
በቡሳ አቋርጦ… በሺ ላይ አድፍጦ
ዱከኖፍቱ አድሮ ጨሊያ ላይ ማልዶ…
ቦዳ አቦን ተሳልሞ ጊንጪ ላይ ብቅ አለ
በጠራራ ፀሐይ መብረቁን ነደለ።
‘ካፒቴኖ ጃገማ… ካፒቴኖ’ ጣሊያን ቢማፀነው
አገሬን ሳትለቅ ሰላም የለም አለው።
ተመለስ ጃገማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ባንዳ ተልከስክሶ ለጠላት ሊሸጣት
አገሬን ሲያስማማት
ክብሬን ሊያዋርዳት
‘ኢንተኡ፣ ዲዴ’ ብሎ ጃገማ ካለበት
በቁጣ ገንፍሎ መብረቁን ጣለበት።
ጠላትሽ ኢትዮጵያ ማደሪያ የለውም
የጃገማ መብረቅ ምቾት አይሰጠውም።
የጠላት ጦር ሰፈር በጭንቅ ተሽመድምዶ
በጠራራ ፀሐይ መብረቅ መጣል ለምዶ
ጃገማ ጃገማ ጃጋማ ተወልዶ!!!
ኦፈን ያ ጃገማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
/ሚያዝያ 1 2009/

1 COMMENT

  1. ጀግናው ያጃገማ ኬሎ ጠላትን ለማርበድበዳቸው ጸሐይ የሞቀው ታሪክ የሚያውቀው ሐቅ ነው፤ይሁንና በዘመናችን የተፈጠሩ ጉዶች የኢትዮጵያን ታሪክ አንዲት ገጽ የማያውቁ ኦሮሞነትን ለባንዳነት ፍጆታ ለማዋል፣ ጎበናዎች በማለት በተለያዩ ቅጽል ስሞች በመጠቀም ጥላሸት ሲቀቡ ይስተዋላሉ።የሚያሳዝነው እነኚህ አወቅን ባዮች ምሁራን በፈረንጆች ልሳን ተምረው፣በጻፉት መጽሐፋቸው ሳይቀር ታሪካችንን በርዘው ወጣቱን ትውልድ ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም በእነ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦም ሆነ፣ፍቅሬ ቶለሳ ባደባባይ በመረጃ ተጋልጠዋል።
    ወደፊት እድሜና ጤና ይስጠን እንጂ የእኔ የአባቴ አያት ፊታውራሪ ድሪብሣ ኡርጊ ጂጆ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሸለሙት ላንድ ሮቨር እንደነበር አልዘነጋም፤ራሱን የቻለ ታሪክ አለው።ጦራቸውም በጀኔራሉ ያ ጃጋማ ኬሎ ሥር የሚመራ እንደነበሩ አምቦ ኤጀርሳ እና ደምቢ ያሉትም በሚገባ ያውቃሉ።
    ለመሆኑ ከዛሬ ሃያ ሰባት ዓመታት በፊት በዘጠና ሁለት ዓመታቸው ሞተው ይቡዶ ተራራ ላይ ስለተቀበሩት ፊታውራሪ ድሪብሣ ኡርጊ ጂጆን ጀግንነት ማነው የሚያውቀው????…እነዚህ አንዴ በእስልምና ሥም ኦሮሞን ለአረብ አገሮች የሚያዳልሉት፤አሊያም በሐይማኖት ሽፋን ገብተው የተዋለዱትም ቋንቋውን እንጂ ታሪኩን አያውቁትም።
    አንድ አቢይ ሐቅ አለ፤ይኸውም ያ ጃጋማ ኬሎ ያለ አርበኞች ጀግንነት ድል ለመቀዳጀት ኣይቻላቸውም ነበር፤ገና መቼ ተነገረና።ዕድሜና ጤና ይስጠን።

LEAVE A REPLY