ስማ!! /ለታሪካዊው ጀግና ሌ/ጄኔራል ጃገማ-በማህሙድ እንድሪስ/

ስማ!! /ለታሪካዊው ጀግና ሌ/ጄኔራል ጃገማ-በማህሙድ እንድሪስ/

አንተ ካንተዎች ጋር በቀቢፀ ተስፋ
።።።።።።። የጥፋት የውድቀት ታሪክ ስትሻማ
ህያው ታሪክ ሰርቶ
በጀግንነት ኑሮ
በድል አሸብርቆ
ክፍለ ዘመን ዘልቆ
ከነ ሙሉ ክብሩ
ከነ ሙሉ ግርማው
።።።።።።።።ባገር ሙሉ ፍቅር ተሸኘ ጃገማ ።

ክብር የለህ
ፍቅር የለህ
ከኩይ ምኞት በቀር ምናለህ አንተማ !!
አንተ ያገር እዳ
አንተ ያገር ሰነፍ
በል እንግዲህ ደሞ
ባይንህ ያየኸውን እውነታ ካድና ለሀሜት ተሰለፍ ።
ስማ! ! ስማ! ! ስማ! !
ጀግና ማለትኮ
ህዝብ የወደደው ነው የተደረበለት የፍቅር ከራማ ! !
እንጅማ
ሲዳክሩ መኖር በ‘ውር ድንብር ሀሳብ በብካይ አለማ
በተንኮል ሸለቆ በክፋት ጨለማ
ርካሽነት ነው
የማዕረግ ድርድር ሊያላብስ አይችልም ያባትነት ሸማ! !
ለዚህ ለመታደል
ለሀገር መኖር ነው
ህዝብህን ማክበር ነው
ሰው ሁኖ መገኘት ልክ እንደ ጃገማ! !

እንጂማ
አንተው ሁነህ እንጂ ከቅድምህ ጋራ ከቶ ማትስማማ
ስለማታይ እንጂ ስለማትስማ
አሁን በቀደም ለት
ነበር ካጠገብህ
ሊመራህ የሚችል ሊያደርስህ የሚችል ወደ ክብር ማማ ።
ታዲያ ምን ያደርጋል
ከቅናት በስተቀር
ከጥፋት በስተቀር
ማክበር የት ታውቃለህ
አንተ ላንተነትህ ክብር የለህማ ።

አንተማ! ! አዎ አንተማ
በስለት ምላስህ
በመርገምት ተንፋሽህ
ዙሪያዋን ወጋግተህ አገርህን አድማ ።
እምነት የለህማ
ፍቅር የለህማ!
………….የለህማ ።

ተወው ያንተን ነገር …… ኤዲያ ተወኝማ

ያገርን ዳር ድንበር ለማስከበርማ
ወራሪ ሶላቶን ለማንበርከክማ
ላገር ፍቅርማ
ለጀግንነትማ
እንደ በጋው መብረቅ — ማን እንደ ጃገማ!!
!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

1 COMMENT

  1. ጀግናው ያጃገማ ኬሎ ጠላትን ለማርበድበዳቸው ጸሐይ የሞቀው ታሪክ የሚያውቀው ሐቅ ነው፤ይሁንና በዘመናችን የተፈጠሩ ጉዶች የኢትዮጵያን ታሪክ አንዲት ገጽ የማያውቁ ኦሮሞነትን ለባንዳነት ፍጆታ ለማዋል፣ ጎበናዎች በማለት በተለያዩ ቅጽል ስሞች በመጠቀም ጥላሸት ሲቀቡ ይስተዋላሉ።የሚያሳዝነው እነኚህ አወቅን ባዮች ምሁራን በፈረንጆች ልሳን ተምረው፣በጻፉት መጽሐፋቸው ሳይቀር ታሪካችንን በርዘው ወጣቱን ትውልድ ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም በእነ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦም ሆነ፣ፍቅሬ ቶለሳ ባደባባይ በመረጃ ተጋልጠዋል።
    ወደፊት እድሜና ጤና ይስጠን እንጂ የእኔ የአባቴ አያት ፊታውራሪ ድሪብሣ ኡርጊ ጂጆ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሸለሙት ላንድ ሮቨር እንደነበር አልዘነጋም፤ራሱን የቻለ ታሪክ አለው።ጦራቸውም በጀኔራሉ ያ ጃጋማ ኬሎ ሥር የሚመራ እንደነበሩ አምቦ ኤጀርሳ እና ደምቢ ያሉትም በሚገባ ያውቃሉ።
    ለመሆኑ ከዛሬ ሃያ ሰባት ዓመታት በፊት በዘጠና ሁለት ዓመታቸው ሞተው ይቡዶ ተራራ ላይ ስለተቀበሩት ፊታውራሪ ድሪብሣ ኡርጊ ጂጆን ጀግንነት ማነው የሚያውቀው????…እነዚህ አንዴ በእስልምና ሥም ኦሮሞን ለአረብ አገሮች የሚያዳልሉት፤አሊያም በሐይማኖት ሽፋን ገብተው የተዋለዱትም ቋንቋውን እንጂ ታሪኩን አያውቁትም።
    አንድ አቢይ ሐቅ አለ፤ይኸውም ያ ጃጋማ ኬሎ ያለ አርበኞች ጀግንነት ድል ለመቀዳጀት ኣይቻላቸውም ነበር፤ገና መቼ ተነገረና።ዕድሜና ጤና ይስጠን።

LEAVE A REPLY