የትግራይ ሕዝብን እንደመጠቀሚያ /በኤርምያስ ቶኩማ/

የትግራይ ሕዝብን እንደመጠቀሚያ /በኤርምያስ ቶኩማ/

የአንዳንዶቹ ሰዎች ጭፍንነት ያናድደኛል፤ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ለገደሉት ህዝብ የትግራይ ህዝብ ዋጋ ሊከፍል እንደሚገባው ሲለፈልፍ ይውላል፤ አንዲት የትግራይ ገበሬ በማእከላዊ ለሚፈፀመው ቶርች በምን መልኩ ተጠያቂ ልትሆን እንደምትችል አይገባኝም፤ የትግራይ ህዝብ በማእከላዊ እየደረሰ ባለው አፈናና ስቃይ እጁ አለበት ብሎ የሚያስብ እና የሚለፈልፍ ግለሰብ ካለ በመጀመሪያ መሃይም ነው ሲቀጥል አህያ አህያን መርጣ ከአህዮች ጋር እንደምትውል ሁሉ ይህ ግለሰብ እርሱን ከመሰሉ መሃይሞች ጋር ብቻ መዋል ያለበት እንሰሳ ነው።

እነዚህ የጥላቻ ንግግር የሚያሰሙ ወገኖች በትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖረውን ሕዝብ ሄደው ቢያዩት እጅግ የሚያፍሩ ይመስለኛል። እኔ በሥራ አጋጣሚ አብዛኞቹን የኢትዮጵያ ክፍሎች እስከገጠር ቀበሌ ድረስ እየዋልኩና እያደርኩኝ ለማየት ችያለሁ አብዛኛው የትግራይ ወረዳዎችንም ማለትም እነአደባይ፣ ፍሬሰላም፣ ማይቆማ፣ ውህደት ፣ ደጋጉም፣ ማይ ወይኒ፣ ሼክ መንሻክ፣ ማይ ትረቢል፣ አዲጎሹ፣ ማይ ቀይሕ፣ ተከዜ ወንዝ ፣ሽራሮ ፣ አዲ ሀገራይ ፣ አዲ ነብርኢድ፣ አዲ ዳእሮ፣ ሽሬ፣ ውቅሮ ማራይ ፣ አክሱም፣ አዲ አቡን፣ አድዋ፣ ሽሬ ፣ ማሪያም ሸዊቶ፣ ድብድቦ ፣ እንጥጮ፣ ሴሮ፣ አህዝራ፣ ብዘት፣ ማይአለቅቲ፣ ምጉላት፣ አዲ አይኖም፣ ክሳድ አለቃ ፣ እዳጋ ሐሙስ፣ ፍሬወይኒ፣ ጎር ሞዶ፣ ነጋሽ፣ ውቅሮ የመሳሰሉትን የትግራይ ወረዳዎች በስራዬ ምክንያት ከገበሬ ቤት እያደርኩኝ ህዝቡን አይቼዋለሁ፤ የትግራይ ህዝብ እነመለስ እና ገብሩ አሥራት ከዚህ ህዝብ ነው የወጡት የሚያስብል ሲበዛ መልካም ህዝብ ነው፤ እነመለስ የአውሬ ልጆች እንጂ ከትግራይ እናት ማህፀን የወጡ አይመስለኝም፤ አንገቴን ቢቆርጡኝ የማልክደው ነገር ቢኖር የትግራይ እናትና አባቶች እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ለሰው አዛኝ እና እጅግ ሩህሩህ ሰዎች ናቸው።

የትግራይ ህዝብ ላይ የማልክደው ነገር ቢኖር አብዛኛው ህዝብ የህወሃት ደጋፊ ነው ይህ ለመሆኑ ደግሞ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባው ፋሺሽቱ የትግሬ ቡድን እያሉ የጥላቻ መርዛቸውን የሚረጩት የሃገራችን ፖለቲከኞች ናቸው፤ የትግራይ ህዝብ ተጠቅሟል ፣ ፋሺሽት ነው እያልክ እንዴትስ ከአንተ ጋር ሊያብሩ ይችላሉ? ነገ እርምጃ እንደምትወስድባቸው እየነገርካቸው እንዴት ሕወሃትን ከመደገፍ ይቆጠቡ? ሕወሃትን የሚደግፉት ወደው አይደለም አማራጭ አጥተው እና ነገ ፋሺሽት ትግሬ እያሉ የሚሰድቧቸው ወገኖች ሥልጣን እንዳይዙ ነው። ህወሃትም የአንዳንድ ዘረኛ ተቃዋሚዎችን ንግግር እየመዘዘ ለትግራይ ህዝብ በማቅረብ እኔ ከሞትኩኝ አለቀልህ ሲል ያስፈራራቸዋል።

ይህንን ስል ትግሬ በመሆናቸው ብቻ ሊኮፈሱ የሚፈልጉ የሉም ማለት አልችልም፤ በርካታ ሰዎች በተለይም ከትግራይ ክልል ውጭ የሚገኙ ትግሬዎች ትግሬ በመሆናቸው ብቻ መጠቀም ሲፈልጉ እና በተግባርም ሲጠቀሙ አይቻለሁ፤ እነዚህ ግለሰቦች የህወሃትና የአረና ፖለቲከኞችን ጨምሮ ትንሽ ፊደል ቆጠሩ የሚባሉ የትግራይ ሰዎች ሌላውን ጨቁነው መንገስ እና መዝረፍ ይፈልጋሉ እነዚህ ግን በተአምር የትግራይን ህዝብ መወከል አይችሉም። ዘወትር ከተጎዳ ሠው ጎን ልንቆም ይገባል፤ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በሌሎችም ሕዝቦች ላይ የሚካሄደውን ጭቆና እንደምናወግዝ ሁሉ የትግራይ ህዝብ በጠቅላላው ጨቋኝ ነው የሚሉትንም ልናወግዝ ይገባል። እኔ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰው በደል እንደሚያሳዝነኝ ሁሉ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚቀርበው ማንኛውም የሐሰት ውንጀላም ያሳዝነኛል።

በኢትዮጵያ ጨቋኝ መደብ እንጂ ጨቋኝ ብሔር የለም፤ አዎ ሁሉም የህወሃት አባል ትግሬ ነው ሁሉም ትግሬ ግን የህወሃት አባል አይደለም።

LEAVE A REPLY