ይድረስ ለጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ /ፈይሰል ክብሩ/

ይድረስ ለጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ /ፈይሰል ክብሩ/

የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” ዜማ ላይ በ”ርዕዮት ሚዲያ” የቀረበው እንከን የሞላበት ትችት

በቅርቡ የቴዲ አፍሮን አዲስ “ኢትዮጵያ!” የሚል ዜማ በማስመልከት በርዕዮት ሚዲያ ልዩ ዝግጅት ባንተ አቅራቢነትና በተሳታፊ እንግዶች የተነሰረ “ሙያዊ” የሚመስል ግልጽ ነቀፌታ አዘል ትችት ነበር። (ዝግጅቱም ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር እዚህ ሊንክ ላይ በሚገኘ የድምጽ ፋይል ይገኛል:- https://goo.gl/UvsIHe)

በበኩሌ ጋዜጠኛ ቲዎድሮስ ጸጋዬም ሆነ ሌሎች እንግዶችህ ሃሳባችሁን በግልጽ መናገራችሁ ላይ ምንም ችግር የለብኝም። ድሮም ሃሳብ የሚፈራ የለም። አንተም ሆነ እንግዶችህ ሃሳብ የማትፈሩ ከሆነም ሌሎች በተራቸው የራሳቸውን ሃሳብ ሲናገሩ በጥሞና ስሟቸው።

ለመንደርደሪያ፣ ወንድሜ ቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዚያት በተናገርክባቸው አጋጣሚዎች ባነጋገርህ ጨዋነት የሚቀርህ ነገር እንዳለና ከዚ በላይ ብዙ መሄድ እንዳለብህና እንሚገባህ ታዝቢያለሁ።በተለይ ሃሳብህን ከማስተላለፍ አልፈህ እንደ ህጻን ምትናገረው ነገርና አንዳንድ የምትጠቀማቸው ቃላት ለጋነት፣ አንዳንዴ የምታሰማው ሌሎችን የማናደድ የለበጣ ሳቅህ፣ እንዲያው ባንተ እድሜ ከማይጠበቅ አንድን ነገር ያላግባብ የመደጋገም ነገር ይታያል። መቼም ሁላችንም ጋር አንዳንድ የረጅም ጊዜ አልባሌ ባህርይ ይኖራል፣ ይህም በቀላሉ አይጠፋም። እሱስ ይሁንና ሃሳብህ ላይ ይተኮር ቢባልም፣ የሰጠኸውና እንግዶችህ የሰነዘሩት የቴዲ ትችት በብዙ መልኩ በእንከን የተሞላ ነው። በግሌ በዋነኝነት የታዘብኳቸውን ነገሮች ለማካፈል ያህልም:-

1) በፋሲካ ልዩ ዝግጅት በሚል ሰዎች በዓል መክበር ላይ ባሉበት ወቅት “የስነጥበብ ሃያሳይንን” አቅርብህ በሰዎች ስሜት ላይ ለመሳለቅ መፍቀድህ በራሱ ምን ያህን ያልጠነከረ ስብዕና እንዳለህ በትክክል ያስረዳል። የመጀመሪያው ስህተትህ የዚህ ትችት ጊዚያዊ አለመሆን ይመስለኛል፣ ልጅ ቴዎድሮስ። ይህ አስተያየት መቆየት ይችል ነበር፣ ሌላው ቢቀር ዜማው በተለቀቀበት ማግስትና በፋሲካ ቀን እንዲህ ልቅ የሆነ የቴዲ አፍሮን አስተዋጽኦ የሚያኮስስ አስተያየት ባይቀርብ ጥሩ ነበር። በመሆኑም የዝግጅቶችህን አቀራረብና ጊዜ አመራረጥ በተመለከተ ከጎንህ የሚያማክርህ ሰው ቢኖር ጥሩ ነው።

2) ይህ “ሙያዊ” የሚመስል ትችት መቆየት ነበረበት የሚያስብል ሌላ እውነታም አለ። በተደጋጋሚ አብርሃም “ይህ አልበም!” እያለ ሲናገር እየሰማህ ማስተካከል ተስኖሃል። የትኛው አልበም? ግለሰቡ ነብይ ሆኖ ነው ወደፊት መጥቆ፣ ያልወጣውን ሙሉ አልበም ያደመጠው? አብርሃም ገና ከአልበሙ መካካል አንዱን ዜማ ሰምቶ ስለ አልበሙ በዚህ መልኩ በአጽንኦት እርግጠኝነት መደምደሙ “ከፈረሱ ጋሪውን” ማስቀደሙን በግልጽ ያሳያል። ሁሉንም ዘፈኖቹን ብታደምጡና የዛኔ የተሟላ አስተያየታችሁን ብትሰጡት ያባት ነበር። ይህ ደግሞ በትንሽ አርቆ ማሰብ ማጤን የሚቻል ነገር ነበር። ቴዎድሮስም ሆነ እንግዶችህ፣ ይህም ሆነ ሌሎች ዜማዎቹ ይበልጥ ሲደመጡ የምትሉትን ነገር በግልጽ ሲያፋልሱ (ይህ የመሆኑ እድል ደግሞ እጅጉን ሰፊ ነው።) ወደፊት ምን ያህል የተቀባይነት ክስረት ውስጥ ልትገቡ እንደምትችሉ ማመዛዛን ነበረባችሁ።

3) ተወያዮቹ በተደጋጋሚ “ስነጥበብ” ስትሉ ይደመጣል። በናንተ የስነጥበብ መለኪያ፣ ሲነካኩት ጥሩ ቅላጼ ማውጣት የሚችል መሰንቆም ሆነ በኮምፒውተር ፕሮግራም ተደርጎ መዝፈን የሚችል ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ ራሱ አንድ የስነጥበብ ክህሎት አለው ሊባል ነው ማለት ነው?! ሲጀምርም፣ ቴዲ አፍሮ በዜማና ቅላጼ የራሱ ክህሎት እንዳለው ራሳችሁ ተናግራችኋል። ሲቀጥል፣ ከዚህ ብዙ እጥፍ የሚበልጠው ግን የቴዲ አፍሮን አስተዋጽኦ ጉልህ የሚያደርገው ነገር በብዙዎች የሚደነቅበት ምክንያት የግጥሞቹ ጥልቀትና የመልዕክቶቻቸው ርቀት ነው። ቴዲ አፍሮ ዝም ብሎ ባዶና የተዘጋ ስፍራ ውስጥ ሆኖ እንደሚጮህ ድምጻው ወይም የሌት ተቀን አቀንቃኝ አይደለም። አርቲስቱ በራሱ ባሁኑ ወቅት ባገራችን የተወሳሰበ ፖለቲካዊና ታሪካዊ አግባብ ውስጥ የሚገኘ አይነተኛ ክስተት/phenomenon ነው። ያገርና ህዝብ ነባራዊ እውነታ ውስጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያሳዩ ሰውን ማዝናናት ደግሞ ለኔ ከስነጥበብም በላይ ልዩ ጥበብ ይጠይቃል። በተለይም የህዝብን የጋራ አንድነትን ከሚነቅፉ የተለያዩ ጎራዎች የተቃጣበትን መሰሪ ጫና፣ እየተሸከመና በምላሹም ይበልጥ እየጠነከረ ያለ ተክለ-ስብዕና ያለው አርቲስት ነው፣ ቴዲ አፍሮ። ከዚህ አንጻር እናንተ ያላችሁበት ወንበር ላይ ቁጭ ብላችሁ “ሙያዊ” የሚመስል ግን በፋይዳው የሱን ሚና ያላመዛዘነና የማይመጥን ተጨማሪ ጫና የመፍጠር ነጻነት ስላላችሁ ባገራዊ ግዴለሽነት ታስቀናላችሁ።

4) ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ ከዚህ በፊትም በሌላ አጋጣሚ እንደታየው፣ ምናልባት ላንተ የማይታወቅህ መሰረታዊ ችግር ያለ ይመስለኛል። (በዚህ በኩል ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ፣ ካንተ በሰለ ያለና ጠንቃቃ የሆነ ይመስለኛል፣ ጓደኛ ስለሆናችሁ ስትገናኙ ብታወሩበት ጥሩ ነው።) ይህም ጎንና ጎንህን ያለውን ሃሳብ የማመዛዘን ድክመትና በአስተሳሰብ ያለመብሰልም ነገር ነው። ለዚህ አይነተኛ ማሳያው አንተ በራስህ፣ ብዙ ጊዜ “ኢትዮጵያዊነትን” እደግፋለሁ እያልክ፣ ከርዕዮተ ዓለማዊ ተቀናቃኞችህ እኩል የቴዲን ሙያዊ አስተዋጽኦ፣ በሌላ ርዕስም ቢሆን በተመሳሳይ የሱን ገጽታ ሊያጎድፍና ለነቃፊዎቹ ሊመች በሚችል መልኩ፣ ለማጣጣል መፍቀድህ ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ የዋህነት ይመስለኛል። ለዚህም ነው እንዲህ አይነቱን ድርጊት “shooting oneself on the foot” የሚሉት ምዕራባውያን። በፖለቲካ ያለመብሰል ሆኖ ነው እንጂ በትችት ቴዲን የማሳደግ ህልም አንተ በምትለው መልኩ አይደለም የሚደረገው።

በተለይም ደግሞ በዚህ ወቅት ያንተው ትችት የርዕዮተ ዓለም ተቀናቃኞችህ ልሂቃንና የቴዲን የዘወትር ነቃፊዎች ሃሳባዊ ጥንካሬን የሚሰጥ መሆኑን አለማወቅህ ይገርማል፣ በእውነት። ነገ የራስህን ትችት መልሰው የቆምክለትን እሳቤ ለማጣጣል ሲጠቀሙበት ደግሞ ይህ ነገር ይበልጥ ይገለጥልህ ይሆናል። አልፎ ተርፎም፣ ቴዲ አፍሮን ሌሎች ለምን እንደሚያደንቁት ሳይገባህ እነሱን በመንጋነት ስትተች፣ በተመሳሳይ ምክንያት ያንተን ፕሮግራሞች የሚከተሉትን ሰዎችን በመንጋነት እየተቸህ ነው። በዚህም ለተቀናቃኞችህ ራስህን ጎጂ የሚሆን የተሳሳተ ሃሳብ እያቀበልክ እንደሆነ ይገባህ ይሆን፣ ወንድም ቴዎድሮስ?! ግድ የለም እስኪ ላፍታ ቆም ብለህ ራስህን “የቴዲ አፍሮን አስተዋጽኦ እንዲህ ባደባባይ ለማኮሰስ ስዳክር፣ ከቆምኩለት ትልቅ የሚባል አገራዊ እሳቤ ይልቅ፣ በሌላ መልኩ ሊገለጥ የሚችል የስነጥበብ ልኬት እርካታዬን እንደማስቀድም ለሌሎች እያሳወቅኩ ቢሆንስ?!” ብለህ ጠይቅ።

በመጨረሻም፣ ብዙዎች ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን በሚችሉት ሁሉ ላንተ ወገናዊ ምከር ለመስጠት ሞክረዋል። እንዲያው እንዳልፎ ሂያጅ “ምከረው ምከረውና አልሰማ ካለህ መከራ ይምክረው።” በሚል አንተን ወደፊትም መምከራችን ማቆም የለብንም። ኢትዮጵያዊ ነህና! በጋራ የመጓዝ እሳቤ እንዲጎለብት ትፈልጋለህና! ይህንንም በተሻለ መልኩ እንድታረገው የብዙዎቻችን ጽኑ ፍላጎት ነውና!

ካክብሮት ሰላምታ ጋር!

LEAVE A REPLY