የቴዲ አፍሮን ‘ኢትዮጵያ’ የተቹት ርዕዮቶች ይቅርታ ጠየቁ

የቴዲ አፍሮን ‘ኢትዮጵያ’ የተቹት ርዕዮቶች ይቅርታ ጠየቁ

ቴዎድሮስ ካሣሁን የእናንተ የመኾኑን ያህል የእኛም ነው

እሑድ ኤፕሪል 16 ቀን 2017 ዓ.ም በርዕዮት ኪን ዝግጅት ላይ የቴዎድሮስ ካሣሁን ‘ኢትዮጵያ’ የተሰኘው ዘፈን ርእስ ሆኖ የመነጋገሪያ ጭብጥ ነበር፡፡ ይህ ዝግጅት መቅረቡን ተከትሎ በርካታ ተከታታዮቻችን ቅሬታዎቻችሁን በጽሑፍ እና በድምጽ መልዕክቶች፣ በኢሜይል እና ባሉት የመገናኛ መንገዶች ኹሉ ተጠቅማችሁ ገልፃችሁልናል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ሥራ በባሕሪው ከብዙኃን ጋራ ያለው ግንኙነት የዕለት ተዕለት እና እጅግ የጠበቀ መኾኑ እውነት ነው፡፡ በዚህም ከብዙዎች ጋር በሚደረግ መስተጋብር፣ የሐሳብ መሻከሮች፣ ቅሬታዎች እና መከፋቶች ይከሰታሉ፡፡

ርዕዮትም ኾነ በሥሩ በኢንተርኔት የሚቀርቡት ዝግጅቶች ኢትዮጵያን የሚያከብሩ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚዘምሩ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ ለመኾናቸው ከእናንተ እና ከሥራዎቻችን በላይ ምስክር የለንም። (በኢትዮጵያዊነት ላይ ካሰናዳናቸው በርካታ ዝግጅቶች መካከል ለናሙና እንዲኾኑ የጥቂቶቹን ሊንክ በግርጌ አኑረናል።)

የርዕዮት አባላት ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለን እጅግ ጥልቅ ፍቅር በሐሳቦቻችን፣ በሥራዎቻችን እና በድርጊቶቻችን የተመሰከረ ነው፡፡ አትሮኖስ ስንል፣ ርዕዮት ኪን ስንል፣ የርዕዮት ዜና መጽሔት ስንል፣ T&T ስንል ዛቢያ እና ምሕዋራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ምኞታችንም ኹለንተናዊ ብልጽግና ያላት፣ በመንፈስም ኾነ በቁስ አካል የዳበረች ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ የቅሬታ መነሻ የኾነው የርዕዮት ኪን ዝግጅት ዓላማም የአገራችን ኪነጥበብ እንዲጎለብት እና በኪነጥበባችን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማጉላት ይቻል ዘንድ ጥበብ ሠሪዎቻችንን ማበረታታት ነው፡፡

በመኾኑም እናንተ ውድ ተከታታዮቻችን እንድትገነዘቡልን የምንሻው የሚከተሉትን ነጥቦች ነው።
1) በኪነጥበባችን፣ በፖለቲካችን፣ በማኀበራዊ መስተጋብራችን ኹሉ የአስተሳሰብ እና የአተያይ አማራጮች እንዲኖሩ፣ ኀለዮቶች ለሐሳብ ገበያ እንዲቀርቡ፣ በሐሳብነታቸው ተመዝነው የላቁት እንዲሰፍኑ፣ ያልጠሩትም ነጥረው እንዲወጡ የሚያስችል ከባቤ መፍጠር ትልማችን ነው፡፡ የቴዎድሮስ ካሣሁንን ኢትዮጵያ የተሰኘ ዘፈን አስመልክቶ ውይይት ያደረግነው በግልጽነት፣ ይበልጥ ውበት፣ ይበልጥ ጥራት ፍለጋ እንጂ ከሌላ ከምንም ዓይነት እናንተ ከማታውቁት ድብቅ አጀንዳ ተነስተን አይደለም።
2) የርዕዮት መነሻ ምክንያትም ኾነ መዳረሻ ግብ እናንተ ታዳሚዎቻችን ናችሁና ለእናንተ ያለን ክብር ይህ ነው ተብሎ የሚገለፅ አይደለም፡፡ እናም በምንም ኹኔታ አድማጮቻችንን የመዝለፍ፣ የማንቋሸሽ እና የማንኳሰስ ዓላማም ኾነ ፍላጎት የለንም። ኾኖም፣ በእሑድ ኤፕሪል16 ቀን 2017 ዓ.ም. በርዕዮት ኪን ዝግጅት ላይ በድምፀታችን፣ በአቀራረብ ጉድለት እና በቃላት ምርጫችን ያዘናችሁ ታዳሚዎቻችንን በይፋ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
3) ቴዎድሮስ ካሣሁን የእናንተ የመኾኑን ያህል የእኛም ነው። ቴዎድሮስን ለመሔስ አንደበታችንን የከፈትነውም የእርሱ በሞያው መሰለጥ ለአገርም ለወገንም ይበጃል ከሚል ቅን ሐሳብ በመነሳት ነው። ጊዜ ሰጥተን አተያዮቻችንን ማቅረብ የፈለግነውም ቴዎድሮስ ካሣሁን ብዙዎች ለጣልንበት ኃላፊነት ይበልጥ ጥኑ ኾኖ እንዲገኝ ይረዳው ዘንድ ብቻ ነው። ቴዎድሮስ ካሣሁን የኢትዮጵያዊነታቸው ድምፅ የኾነላቸው በርካታ ዜጐች መኖራቸውን አንስተውም።

ኹሌም ቢኾን በርዕዮት አዘጋጆች ላይ የተሰነዘሩትን ዓይነት ክብረ ነክ፣ መጠንና መስመር የተላለፉ ዘለፋዎች ገንቢ ሚና እንደማይኖራቸው፤ ለተዋስዖ፣ ለነጻ ሐሳብ መንሸራሸር እና ለመሻል እንደማይረዱ አጥብቀን እናምናለን፡፡ በውይይት አደባባዮቻችን ላይ አንድ ወጥ ሰልፍ ብቻ ይኑር መባሉና መጨፍለቁ አግባብ እንዳይደለ፣ ይኽ አዝማሚያም ለአገርም ኾነ ለወገን ጠንቅ መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ የዴሞክራሲን እና የነፃነትን እሴቶች እንደምንነታችን እና ማንነታችን መገለጫ አድርገን ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጣቸዋለን።

ማንም የሚያምንበትን በምክንያት ተደግፎ እና በሰከነ መንገድ ለማቅረብ ጨርሶ ሊሸማቀቅ እንደማይገባው፤ ይኽም ሰው በመኾኑ የሚያገኘው ተፈጥሯዊ ሽልማት እንደኾነም እናምናለን፡፡ እናንተን ታዳሚዎቻችንን ማሳዘን ግን ጨርሶ ሐሳባችን አልነበረም፣ አይደለምም፡፡ የሰነዘርናቸውም ኾነ ወደፊት የምናቀርባቸው ሐሳቦች ብቸኛ ዓላማ ጥበብ ሠሪዎቻችን የበለጠ እንዲሰሉ፣ እጅግም እንዲደምቁ ነው፡፡ ሌሎች ሒስ እንዲቀበሉ እንደምንጠይቅ ኹሉ፣ አመክንዮ ተመርኩዞ በሚዛን የሚቀርብብንን ሒስ በትኀትና እንቀበላለን፡፡ ወደፊትም እንከን ስታዩ፣ በእናንተ ለመታረም ኹሌም በጎ ፈቃድ ስላለን ሐሳቦቻችሁን እናስተናግዳለን፡፡ ስለኛ ስላሳያችሁት ግድ እናመሰግናለን፡፡ ውዴታችሁን እናከብራለን፡፡ ገንቢ አስተያየቶቻችሁንም ከልብ እናደምጣለን፡፡

በኢትዮጵያዊነት ላይ ካሰናዳናቸው በርካታ ዝግጅቶች ጥቂቶቹን እነኾ:
በፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ በይፋ ተቃውመናል፡፡
ክብራችን የሆነውን የአድዋን ድል በገጾቻችን በ9ሰአታት ያልተቋረጠ ዝግጅት በኩራት ዘክረናል፡፡
የየካቲት 12ን በብዙ ሺኅ የተቆጠሩ ሰማእታት ወገኖቻችንን ለሰአታት በቀጥታ ስርጭት አስታውሰናል፡፡
አርበኛውን በላይ ዘለቀን አውስተናል፡፡
የቴዎድሮስ ራዕይ የቲያትር ጉዞ፡፡

LEAVE A REPLY