ታዋቂው ‎ደራሲና የህግ ባለሙያ አቶ አሰፋ ጫቦ አረፉ

ታዋቂው ‎ደራሲና የህግ ባለሙያ አቶ አሰፋ ጫቦ አረፉ

/Ethiopia Nege News/:- በ1966ቱ ኢትዮጵያ የለውጥ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ከሚጠቀሱ የፖለቲካ ሰዎች አንዱ የሆኑትና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ የሚታወቁት የህግ ባለሙያ አቶ አሰፋ ጨቦ በዳላስ ቴክሳስ ህይወታቸው ማለፉ ታወቀ።

በደርግ ዘመን ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ኢጭአት በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ ድርጅት መስራችቾች መካከል አንዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው አቶ አሰፋ ጫቦ በወጣትነት ዘመናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በዘመኑ አሜሪካን ሀገር በተደረገ የክርክር ውድድር ላይ ከኮ/ል ጎሹ ወልዴ ጋር በመሆን ባደረጉት ክርክር አሸናፊ እንደነበሩ ይታወቃል።

አቶ አሰፋ በደርግ የስልጣን ሽኩቻ ድርጅታቸው ከተመታ በኋላና በፊት ከሊቀመንበር መንግስቱ ጋር በነበራቸው ቅርበት በድፍረት አስተያየታቸውን ይሰጡ እንደነበር ሲገለጽ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ደርግ ሙሉ ለሙሉ ስልጣኑን ሲቆናጠጥ ለእስር እንደተዳረጉ ይታወቃል። ከ10ዓመት በላይ በደርግ እስር ቤት ማእከላዊ ከታሰሩ በኋላ እንደተፈቱ የግል ታሪካቸውም ያስረዳል።

በደርግ ዘመን የሰሯቸውን ስራዎች የሚቃወሙ እንዳሉ ሁሉ አቶ አሰፋ ጨቦ በተለይ አርባምንጭ አካባቢ ወጣቱ ላይ ሊደርስ የነበረውን የግድያ ሂደት በመታደግና ለመግታት ከፍተኛ ጠረቶቻቸው እንደተሳኩና የበርካቶችን ህይወት እንዳተረፉ  በአርባ ምንጭ አካባቢ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ለኢትዮጵያ ነገ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ህወሀት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት በትረ ስልጣኑን በተቆጣጠረበት ወቅት የሽግግር መንግስቱ አካል በመሆን ፓርላማ ገብተው ክርክሮችን ሲያደርጉ የነበሩት አቶ አሰፋ ጫቦ ድርጊታቸው በህወሃቶች እንዳልተወደደና ድጋሚ ለእስር ሊዳረጉ እንደሚችሉ በመረዳታቸው ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደበቁ በተለያዩ በቃለ ምልልሶቻቸው ገልጸዋል።

በድፍረት በሚጽፏቸው ጽሁፎቻቸው ብዙ አድናቆትን ያተረፉት የህግ ባለሙያው አቶ አሰፋ ጫቦ በስደት በሚኖሩበት ዳላስ ቴክሳስ ህክምና ሲደረግላቸው ቆይቶ ዛሬ ህይወታቸው ማለፉን ለመረዳት ተችሏል።

የአቶ አሰፋ ጨቦ አስከሬን በሚወዷት ሀገራቸው እንዲሆን ባስታወቁት መሰረት ውደ ሃገርቤት እንደሚላክ የሚጠበቅ ሲሆን ሂደቱን ለማስተባበር በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ መጀመሩን ለመረዳት ችለናል።

ለመላ ቤተሰባቸው ለአድናቂዎቻቸውና ወገኖቻቸው በሙሉ የኢትዮጵያ ነገ ድረ ገጽ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን ልንገልጽ እንወዳለን።   /ኢነዝክ/

 /Ethiopia Nege April 23, 2017/

1 COMMENT

  1. May God Have Mercy On Him. May The Almighty The Magnanimous, The Omniscient, The Omnipresent Have Mercy On His Soul!!!

LEAVE A REPLY