“አባ ኮስትር በላይን” እንዘክረው ! /መላኩ አላምረው/

“አባ ኮስትር በላይን” እንዘክረው ! /መላኩ አላምረው/

“ስሜ በላይ፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ፣ ትምክህቴና መሐላዬ ጊዮርጊስ ነው”
እስኪ በአርበኞች ቀን የምንጊዜውንም ኢትዮጵያዊ ጀግና “አባ ኮስትር በላይን” እንዘክረው !
(መላኩ አላምረው)

“የማይቆረጠም የብረት ቆሎ
የማይጨብጡት የእሳት አሎሎ”
.
ይህች ስንኝ ለጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች የተሰነኘች ናት። አርበኞች ለጠላት እንዲህ ነበሩ። በሀገራቸው ክብርና ነጫነት ድርድር አያውቁም ነበር። ለሰወ በላው ፋሽስት እንደ ብረት ቆሎ አልቆረጠምለት፣ እንደ እሳት አሎሎ አልጨበጥለት ብለው፣ በቆመበት በተቀመጠበ ሁሉ እንደረመጥ እያቃጠሉ፣ ሲከፋም ውድ ሕይወታቸውን እየገበሩ ነፃ ሀገርን አውርሰውናል። ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል።
.
አርበኞች ሲነሱ ቀድሞ ፊታችን ላይ ድቅን የሚለው ጀግናውና ቆፍጣናው “አባ ኮስትር በላይ” ነው። አባ ኮስትር ከጎጃም አርበኞችም አልፎ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ወኔ የሆነ፣ ልባቸውን በድል ተስፋ የሞላ የነፃነት ትግል አርአያ ነበር። በተለይም መላው ጎጃም ለአርበኝነት እንዲነሳሳና ጠላትን መቆሚያ መቀመጫ እንዲያሳጣው የበላይ የጀግንነት ተምሳሌትነት ወሳኝ ነበር። አንዳንድ አጥኝዎች (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ጨምሮ) በወቅቱ 80%ቱ የኢትዮጵያ አርበኞች ጎጃም ውስጥ መሽገው እንደነበር ይስማማሉ – ለዚህም የአባ ኮስትር በላይ አስተዋጽኦ ጉልህ ነበር። ለብዙ አርበኞች ጋሻ ከለላ ነበርና። የጦር ስልትም ይችልበታል። ጠላትን መቼንል እንዴት ወግቶ ድል እንደሚያደርግ ያውቅበታል። ወዲህ ንቁና ቆፍጣና ወዲያ ደግና ሩህሩህ ነበር። በጀግንነት ላይ ደግነት የተቸረው አርበኛ – በላይ ዘለቀ።

የበላይ ጦር እንደመንግሥት ጦር ይታይም ነበር። ከ50 ሺህ በላይ ምርጥ ተኳሽ አርበኞች በስሩ ነበሩት። (በመጨረሻ ሀገር ነፃ ስትሆን ለንጉሥ ኃይለ ሥላሴ እንኳን ያስረከባቸው 44 ሺህ አርበኞች ነበሩ)። ለሀገሩ ነፃነት መዋጋትን የፈለገ ሁሉ ወደ ጎጃም መዝለቅን ይመርጥ ነበር። በዚያ በላይ አለ። በላይ ካለ ድል አለ። ስሙ በራሱ የድል መሪ… ክብርና ሞገስ ነው።

አባኮስትር “ራስ፣ ደጃዝማች…” እያለ ሹመት የሚሰጣቸው ታማኝ ጦር መሪዎቹ “ለእኛ ይህንን ማዕረግ ሰጠኸን… አንተንስ ማን እንበልህ?” ይሉት ነበር። (ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ “ራስ” ብሎ የሾመው ተመስገን ፈንታ… “እኔንስ ራስ አልከኝ። አንተ ማን ልትባል ነው?” ብሎት ነበር። መልሱ ይህ ነው..። “እኔን ተውኝ… እናቴ አንዴ ‘በላይ’ ብላኛለች። ስሜ በላይ ሀገሬ ኢትዮጵያ መሐላዬ ጊዮርጊስ ነው”።

ምንም ችግር መጣ ቢባል “ጊዮርጊስ ያውቃል “ይላል በላይ። በጊዮርጊስ በጣም ያምናል። መሐላውም ትምክህቱም እርሱ ነው። አባ ኮስትር እምነቱ ጠንካራ ነው። ይጾማል ይጸልያል። በተለይ ፍልሰታ ሲሆን ሁል ጊዜ ሱባኤ ይገባል።

“እኔ የዘለቀ ልጅ !” በላይ ሲቆጣ የሚናገራት ቃል ነች።
“በምድር በሰማይ የሚያስጉዘው ! በላይ የወንዶች ቁና” ሲፎክር ከአፉ የማትወጣው ራሱን የሚገልጽባት ቃሉ ናት።

በላይ ዘለቀ ተኩሶ አይስትም። ፍጥነቱ ደሞ ጠብመንጃ ሲደግንና ሲተኩስ እኩል ነው ይባላል። ሁሌም ውጊያ ሊጀምር ሲል “እኔ ሳልተኩስ እንዳትተኩሱ “ብሎ ያዛል። አንዳንድ ጊዜ በውጊያ ሰዓት “እርስዎ እዚህ ይቆዩን፣ እኛ እንዋጋ” ሲሉት “ምን ?” ይላል በቁጣ ! “እርስዎ ከወደቁ መሪ የለንምና ደግም አይደል” ሲሉት “ወይዱልኝ ወዲያ ! እኔ አሮጌ ነፍጠኛ ነኝ። ስንቱን ትንትልግ አፍርቼ ሞትን ልፍራ?” ይልና ግንባር ይጋፈጣል።

በላይ ዘለቀ ራሱ የሚዋጋ ከሆነ “ገምባው” የተበባለው ጥሩንባው ይነፋል። “የገምባውን” ድምጽ ሲሰማ ባንዳን ተኩላ እንደበተነው በግ ይበረግጋል። ጥልያን ምጥ እንደያዛት ሴት ይብረከረካል። የገንባው ድምጽ በላይ ሳይገድልና ሳይማርክ ላይመለስ ጦሩን መርቶ መምጣቱን ማሳያ ድምጽ ነውና። በጠላት ጦር ግንባር ተሸንፎ አያውቅም አባኮስትር በላይ!!!

ይህንን በመሰለ ጀግንነት ሀገርን ነፃ ያወጣው በላይ የመጨረሻ ሽልማቱ ስቅላት ነበር። ንጉሡ… ሀገራቸውን በክብር ጠብቆ ያስረከባቸውን ጀግና “በክብሬ መጣህብኝ” ብለው ሰቀሉት። እንዲህ ናት ይህች ሀገር። የተረገመች ናት። ጀግናን ማክበር እንዳትችል ተረግማለች። በላይም “ወንድ አይበቅልብሽ” ብሎ ረግሟታል አሉ። ርግማኑ እንደደረሰ ማሳያውም ይህ ነው። ለሀገር አንድነትና ክብር የሚተጉትን ስትሸልም ሳይሆን ስታሳድድ አለች… ትኖራለችም።

LEAVE A REPLY