የአቶ አሰፋ ጫቦ የቀብር ስነስዓት ዛሬ በቅድስተ ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

የአቶ አሰፋ ጫቦ የቀብር ስነስዓት ዛሬ በቅድስተ ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

/Ethiopia Nege News/:- በነጻው ፕሬስ የህትመት ውጤቶች እና በተለያዩ ድረ ግጾች ላይ በተከታታይ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁት አቶ አሰፋ ጫቦ የቀብር ስነ ስርአት ዛሬ ሚያዚያ ቀን 27, 2009 ዓ.ም በቅድስተ ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡ የጋሽ አሰፋ ሽኝት በዶርዜ ባህላዊ የሃዘን ጭፈራ የታጀበ ነበር፡፡

በቀብሩ ስነ ስርአት ላይ መላ ቤተሰቦቻቸው፡ ወዳጆቻቸውና አድናቂዎቻችቸው የተገኙ ሲሆን ከቀዳማዊ ኅይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በትምህርት ቤት፡ በአብዮቱ እና በ1983 ተቋቁሞ በነበረው የሽግግር መንግስት ወቅት እንዲሁም በስደት አሜሪካን ሃገር ህይወታቸው እስኪያልፍ የከወኗቸውን ተግባራት ያካተተ አጭር የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

አቶ አሰፋ የመሰላቸውንና የሚያምኑበትን ፊት ለፊት በመናገር የሚታወቁ ሲሆን ጋሞነቴ ኢትዮጵያዊነቴን አይከልለውም በማለትም የኢትዮጵያዊነትን ጥልቀት ሲያስረዱና ህይወታቸውን ሙሉ በተለያዩ ጽሁፎች ኢትዮጵያዊነትን ሲሰብኩ እንደነበር ግለ ታሪካቸው ያወሳል፡፡

አቶ አሰፋ በደርግ ዘመን የጭቁን ህዝቦች ድርጅት በመባል የሚታወቀውን ድርጅት አቋቁመው ከደርግ ጋር ሰርተዋል በሚል የሚቃወሟቸው ሰዎች ትችት እንደሚሰነዘርባቸው ይታወቃል፡፡

አቶ አሰፋ በደርግ ዘመን ከ 10 ዓመት በላይ በማእከላዊ እስር ቤት ቆይተው የተፈቱ ሲሆን በህወሃት/ሻእቢያ የሽግግር መንግስት ወቅትም የኦሞ ህዝብን ወክለው ፓርላማ በመገኘት በተለይ የኤርትራ ጉዳይ በአግባቡ እንዲፈታ በአጽናኦት ሲከራከሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ጋሽ አሰፋ በስደት አሜሪካን ሃገር መኖር ሲጀምሩ ህይወታቸው ካለፈ አስከሬናቸው በሃገር ቤት እንዲያርፍ በተናዘዙት መሰረት ቤተስቦቻቸው ይኖሩበት ከነበረው ዳላስ ቴክሳስ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር የአቶ አሰፋ ጫቦ ፈቃድ እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡

ለመላ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን እንመኛለን /ኢነዝክ/

LEAVE A REPLY