የዘንድሮው ዲቪ ሎተሪ የመጨረሻው ይሆን?

የዘንድሮው ዲቪ ሎተሪ የመጨረሻው ይሆን?

 /አድማስ ሬዲዮ/

ባለፈው ሳምንት የ2018 ዓ.ም ዲቪ ሎተሪ ውጤት ወጥቷል። በዚህ የዘንድሮው ዲቪ ሎተሪ ከመላው ዓለም 14 ሚሊዮን ሰዎች አመልክተዋል። 14 ሚሊዮኑም ውጤታቸውን ለማየት ሞክረዋል።፡ዕድለኞች የሆኑም ወጥቶላቸዋል።

ይህ የዲቪ ሎተሪ በያመቱ ለ50ሺ ያህል ከመላው ዓለም ዕጣ ለሚደርሳቸው ዕድለኞች የአሜሪካ ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ ዕድል ይሰጣል። ከሚሞሉት አንጻር ይህ 1 በመቶ መሆኑ ነው። የዘንድሮው ዲቪ ፣ ለአሜሪካው አዲስ የትራምፕ አስተዳደር የመጀመሪያው ሲሆን፣ የመጨረሻው ዲቪ እንዳይሆንም ስጋት አለ። በርግጥ ስለ ህገወጥ ስደተኞች ቁጥጥር እና እገዳ ብዙ ያወሩት ትራምፕ ስለ ዲቪ ሎተሪ የተነፈሱት ነገር እስካሁን የለም።

ቢሆንም ግን ዲቪ የሚቆምበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ምልክቶች እየታዩ ነው። ቢያንስ ሁለት ያህል ዲቪ እንዲቀር የሚጠይቁ የሪፓብሊካኖች ረቂቅ ህጎች ተዘጋጅተዋል። ዲቪ ሎተሪ ከጀመረ እነሆ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል። ብዙዎች አሜሪካ እንደተጠቀመችበት ቢናገሩም፣ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ምንም አልጠቀመንም ይላሉ። ከነዚህ መካከል የአርካንሰስ ግዛት ተወካይ ቶም ከተን ይገኙበታል። ሴናተር ቶም ከተን “የዳይቨርሲቲ ቪዛ ወይም ዲቪ ፕሮግራም ፣ በጉቦ የተተበተበ፣ ለአገራችን በኢኮኖሚም ሆነ በሌላ መንገድ ያልጠቀመ፣ ስሙ እንደሚለውም የተለየ የህዝብ ስብጥር የፈጠረም አይደለም” ሲሉ ይከራከራሉ።

ደጋፊዎቹ በበኩላቸው “የዲቪ መኖር በመላው ዓለም አሜሪካ በበጎ ዓይን እንድትታይ አድርጓል” ሲሉ ይከራከራሉ። በዚያም ሆነ በዚህ ያለፉት የዲቪ አሸናፊዎችም ሆነ የዘንድሮ አመልካቾችና አሁን ባለፈው ሳምንት ዕጣ የወጣላቸው ሁሉ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ናቸው። በዲቪ የተነሳ የብዙዎች ህይወት ተለውጧል። ከበርካታ አገራት መጥተው ራሳቸውና ቤተሰባቸውን የጠቀሙ በርካታ ናቸው።

የሁለተኛ ደረጃ መጨረስ ብቻ የሚጠበቅበት የማመልከቱ ሂደት፣ ለብዙዎች ቀላል ሲሆን፣ ዕድሉ የደረሰው ሰውም፣ የትዳር አጋሩና ልጆችም ካሉት፣ ልጆቹን ይዞ በመምጣት ወዲያው የመኖሪያ ፈቃድ የሚያገኝበት አቋራጭ መንገድ ነው። አንድ አገር 50ሺ ያህል ሰዎች በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ከላከ ግን ዕድሉን ማግኘቱ ይቆማል። ከነዚህ በፊት የዲቪ ተጠቃሚ ከነበሩና አሁን ከተከለከሉ አገራት መካከል ካናዳ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ናይጄሪያ እና ሜክሲኮ ይገኙበታል።

ይህ የ ዕድል ቪዛ አሸናፊ ፕሮግራም በግልጽ የጀመረው በ1995 ዓ.ም ሲሆን፣ ዋናው እንዲጠቀሙ የተፈለገው በጊዜው ቁጥራቸው አሜሪካ ውስጥ አነስተኛ ነው የተባሉት ምስራቅ አውሮፓ እና አፍሪካ ነበሩ። ዕድሉንም በሚገባ እየተጠቀሙበት ነው፣ በላይቤሪያና ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት – ኢትዮጵያን ጨምሮ – ከነዋሪዎቻቸው ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆነው በያመቱ ለዲቪ ያመለክታል። የዲቪ ጊዜ ሲደርስ ኢንተርኔት ካፌዎችን ጨምሮ ብዙዎች ገበያቸው ይደራል። የዚያን ያህል በኢንተርኔት ሙሉ የሚሉ የአጭበርባሪ ድረገጾችም ይበዛሉ። ብዙዎች በዲቪ የተነሳ ብዙ ገንዘብ ተበልተዋል። በደንቡ መሰረት የደረሳቸውም በ ኤምባሲ አንዳንድ ሰራተኞች ዕድላቸው ለሌላ ሰው ተሰጥቶባቸዋል። ዲቪ የደረሰው ሰውም “ልጄን አግባልኝ፣ አግቢልኝ” በሚሉ ምልጃዎች ሲወጠር ኖሯል። ዲቪ ብዙ ትዝታ አለው።

ዲቪ ይቅር የሚሉ ሰዎች ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች አንዱ በ2002 ዓ.ም አንድ በዲቪ አሜሪካ የመጣ ግብጻዊ ሁለት ሰዎችን ሎስ አንጀለስ ውስጥ መግደሉን እንደምክንያት ያቀርባሉ። ይኸው አሸባሪ በዲቪ ነበር የመጣው። በ9/11 ጥቃት ዋና አስተባባሪ የነበረው ግብጻዊ መሃመድ አታ፣ ሁለት ጊዜ ዲቪ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቶ በሌላ መንገድ አሜሪካ የገባ ነበረ።

ይህን ያዩት የቨርጂኒያው ሴናተር ቦብ ጉድላቴ “አሸባሪዎች አሜሪካ ለመግባት ዲቪ ቀላል መንገዳቸው ነው” ይላሉ። “ጥቂት መቶ የሚሆኑ አሸባሪዎች ዲቪ ቢሞሉ፣ አንዳቸው ዕድሉን ማግኘታቸው የማይቀር ነው” ሲሉም ይከራከራሉ። ለዚህም ነው በ2011 ዓ.ም የዲቪ ይቅር ረቂቅ ህግ ለኮንግረስ ያስገቡት።

እስከዛሬም ድረስ ግን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ “ዲቪ የደረሳቸው ሁሉ ዝም ብለው ይመጣሉ ማለት አይደለም፣ ማንነታቸው ይጣራል” ሲል በመከራከር ላይ ነው። በ2013 ዓ.ም እንዲሁ የዲቪ ይቅር ህግ ለኮንግረስ ቀርቦ ሳይጸድቅ ቀርቷል።

ዲቪ እስከዛሬ ድረስ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሱ ሰዎችን ከሌሎች አገራት ወደ አሜሪካ እንዲመጡ አድርጓል። በርግጥ ዲቪ የደረሳቸው ሁሉ መጥተዋል ማለት አይደለም። ዲቪው ደረሳችሁ ከተባሉ በኋላ ባለው 6 ወር ጊዜ ውስጥ መረጃዎቻቸውን አሟልተው ሳይቀርቡ በመቅረታቸው የተቃጠለባቸው ብዙ ናቸው። መጓጓዣና ስፖንስር አጥተውም ነገሩ የቀረባቸው እንዲሁ ብዙ ናቸው።

ከ2015 ወዲህ ደግሞ ነገሮች እየተቀየሩ ነው። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከ6 በተለይ የ እስልምና እምነት ከሚከተሉ አገራት ሰዎች አሜሪካ እንዳይገቡ አግጃለሁ ካሉ በኋላ ከነዚህ አገራት ዲቪ የደረሳቸው ሰዎች ግራ እንደተጋቡ ናቸው። በ2016 ዓም፣ በርካታ ዲቪ ከደረሳቸው አገራት መካከል ሱዳን እና ኢራን ሲገኙበት ፣ እነዚህ አገራት ደግሞ በ እግዱ ስማቸው ከተነሳው መካከል ናቸው።

ምንም እንኳን በፍርድ ቤት የትራምፕ እገዳ ተሽሯል ቢባልም፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ “ጥብቅ የሆነ የቪዛ አሰጣጥ እንዲኖር” ማዘዙ፣ የአንዳንዶቹን የቪዛ ማግኘት ጉዳይ ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል።

በዚህም ሆነ በዚያ ዲቪ እንዲህ እየተንገዳገድም ቢሆን እስካሁን አለ፣ ከዚህ በኋላ ግን ፕሬዚዳንቱም፣ ሴኔቱም ሆነ ምክር ቤቱ በሪፓብሊካኖች ቁጥጥር ስር በሆነበት ወቅት ለውይይትና ለድምጽ መስጠት ተራውን የሚጠብቀው የዲቪ ይቅር ረቂቅ ህግ ላያልፍ ይችላል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። ለዚህም ነው ዜና አውታሮች የዘንድሮው ዲቪ የመጨረሻ ይሆን ሲሉ የሚጠይቁት።

LEAVE A REPLY