ዘመቻ አሉላ – ታሪካዊ ጀግንነትና መስዋዕትነት /ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ/

ዘመቻ አሉላ – ታሪካዊ ጀግንነትና መስዋዕትነት /ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ/

ስለ መስዋእትነት ብዙ ይወራል ነገር ግን የአገር ፍቅር የሚያንገበግበው በእኔ ትውልድ እንኳን የነበሩት ወጣት ወታደሮች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ቤተሰቦቻቸውን እርግፍ አርገው ራሳቸውን ፈንጂ ላይ አንጥፈው ሌላው ወታደር በነሱ ሬሳ ላይ እንዲረማመዱና ድል እንዲጐናፀፉ ያደረጉ ወደር የማይገኝለት መስዋእትነት ስለከፈለው ትውልድ ብዙም አይወራም፡፡
ሁለት ገፅ ነው እባካችሁ ወጣቶች አንብቡትና ራሳችሁ ጋር ተነጋገሩ፡፡ ክህደት በደም መሬት ከሚለው መፅሀፌ የተወሰደ ነው፡፡
አባቶቻችሁ እንደዚህ ዓይነት ውጊያ ውስጥ ነበሩ፡፡

ዘመቻ አሉላ – ታሪካዊ ጀግንነትና መስዋዕትነት

“ዘመቻ አሉላ” በ1969 ከፊል ምፅዋና አካባዊው በሙሉ በሻቢዕያ እጅ በወደቀበት ጊዜ የተካሄደ የጀግንነት ጦርነት ነበር፡፡ ሠራዊቱ ያንጊዜ በጥቂት ቦታዎች ላይ፣ ማለትም በአፄ ግራርና በባሕር ኃይል ቤዝ ውስጥ ተወሰነ፡፡ ለሠራዊቱ ድርጅትና ቀለብ የሚቀርበው በባሕር በኩል ከዳህላክ ደሴቶች ብቻ ነበር፡፡ ወደ ምፅዋ ከተማም ሆነ ወደ አሥመራ ወይንም ወደ ሰሜን የሚያስወጡ በሮች ሁሉ ዝግ ነበሩ፡፡ ከጦሩ ጀርባ ያለው ባሕር ብቻ ነው፡፡

የሻዕቢያ 44ኛ፣ 70ኛ፣ 23ኛ፣ እና 8ኛ ብርጌዶች ምፅዋን ተቆጣጥረው የኢትዮጵያ ሠራዊት የነበረበትን የባሕር ኃይልን ግቢ ከብበውታል፡፡ የሻቢዕያ 77ኛው ብርጌድ በተጠባባቂነት ዶጋአሊ ላይ ሰፍሮአል፡፡ አንድ 122 ሚሊ ሜትር መድፍ፣ አንድ ባትሪ 4.2 ሞርታር እና በቂ የአየር መቃወሚያ መሣሪያዎች ነበሩት፡፡ ከዚህ ውስጥ የሻቢዕያ 8ኛ ብርጌድ ከውጊያው ቀን ቀደም ብሎ ወደ አሥመራ ስለተላከ የሻቢዕያ ጦር ትንሽ ደከም ብሎ ነበር፡፡

በወገን ሠራዊት በኩል 8ኛ፣ 11ኛ፣ እና 33ኛ ብርጌዶች አንዳንድ ሻለቃ ተጠባባቂ በመያዝ በግንባር ከአፄ ግራር እስከ ሲሚንቶ ፋብሪካ የባሕር ሰርጥ ድረስ የመከላከያ ቦታ ይዘዋል፡፡ 29ነኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ ስልጠናውን አሰብና ዳህላክ ላይ አጠናቅቶ ሐምሌ 3 ቀን 1970 ዓ.ም. በሌሊት በምድረ ነክ መርከቦች ባሕር ኃይል ቤዝ ውስጥ ገብቶ ቦታ ይዟል፡፡ ድጋፍ ሰጪ መሣሪያዎች አንድ ባትሪ 122 ሚሊ ሜትር መድፍ፣ አንድ ባትሪ ቢኤም (21 መድፍ) በጥሪ የሚመጣ የአየር ኃይል(F5) አውሮፕላኖችና የተወሰነ የባህር ኃይል ድርጅት ነበር፡፡

ሠራዊቱ በዚያች የበሬ ግንባር በምታክል ወረዳ ውስጥ በሻቢዕያ ተፅዕኖ ተገድዶ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለምሽግ በተሰጠው የፖለቲካና ወታደራዊ ትምህርት በመጠቀም አካባቢውን ፍፁም ነፃ ለማውጣት ሙሉ እምነት ነበረው፡፡ በዚህም ረገድ የ 505 ግብረኃይል በምፅዋ ግንባር ከሲሚንቶ ፋብሪካው አስከ አጂፕ ድረስ መሽጐ በመከላከል ላይ ያለውን ሻቢዕያን በመደምሰስ ብዙ መሬቶችን በመቆጣጠር ዝግጅት አደረገ፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ የ505 ግብረኃይል ግዳጅ በተዋጊ አውሮፕላኖችና መርከቦች ድብደባ እየታገዘ ከአፄ ግራር ፊት ለፊት አንስቶ አስከ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያለውን አካባቢ ሐምሌ 5 ቀን 1970 ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት ላይ አጥቅቶ ሻዕቢያን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ አጂፕ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያሉትን ገዥ መሬቶች በመያዝ የከተማውን አውሮፕላን ማረፊያ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ከተማውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ነበር፡፡

የግብረኃይሉ አዛዥ ዝነኛው ኮሎኔል(በኋላ ሜጀር ጄነራል) አበራ አበበ ነበሩ፡፡ የነበረው ኃይልም፣
• ብ/ጄ/ብርሃኑ ደምሴ፣ ሻለቃ ካሣዬ ጨመዳ፣ 29ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ፣
• ብ/ጄ/ገ/መድህን መድህኔ፣ 8ኛ እግረኛ ብርጌድ፣
• ብ/ጄ/ሰሙ ንጉሥ 33ኛ እግረኛ ብርጌድ፣(በወቅቱ ሁሉም ሌተና ኮሎኖሎች ነበሩ) ሲሆን በመሣሪያ በኩል፣
• 2 ቤኤም መድፎች፣
• 1 ባትሪ 122 ሚሊ ሜትር መድፍ፣
• 10 ፐ55 ታንክ ነበር፡፡
ከባሕር ላይ የተኩስ ድጋፍ የሚሰጡና ቅኝት የሚያደርጉ፣ ለሠራዊቱ ሎጅስቲክስ የሚያቀርቡ ፈጣን ጀልባዎችም ነበሩ፡፡ ደጀን መርከብና ሁለት ምድረ ነክ ጀልባዎች(1035 እና 1036) ነበሩ፡፡

ሻዕቢያ ድሉን ለማዳበርና ምፅዋን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ባለ ኃይሉ ማጥቃቱን ደግሞ ደጋግሞ ከአንድ አስከ ስድስት ማዕበል በተከታታይ ቢልክም የጥይት ሰለባ ከመሆን በስተቀር ሀሳቡ አልተሳካም፡፡ በሁኔታው ባለመደሰቱና በመናደዱ ምሽጐቹን ከአጂፕ አንስቶ የባሕሩን ጠርዝ ተከትሎ ከሲኒማ አይዳ ጀርባ ከሚካኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት አልፎ እስከ ሲሚንቶ ፋብሪካ የባቡሩን ሀዲዶች በሙሉ ነቅሎ እጅግ የተጠናከረ እና በጣም የተኩራራበት፣ በዓይነትም የሚደነቅ ምሽግ ገነባ፡፡ በተጨማሪም የወገን ጦር ሊቀርብበት የሚችልበትን አቅጣጫ ሁሉ በፈንጂ አጠረ፡፡ ለጦሩ ማጥቃት ምንም ቀዳዳ ባለመተው የተዋጊውን ኃይል የስትራቴጂ እውቀትና ከሁሉም የበለጠ የመለዮ ለባሹንም ድፍረት የተፈታተነ በታሪኩ ወደር ለማይገኝለት ሁኔታ ተዘጋጀ፡፡

የወገን ሠራዊት ምኀ እንኳን አመቺ የሆነ ቦታ ላይ ባይሆንም የመታኮሻና የመገናኛ ምሽጐችን ሠርቶ በሙሉ ጽናትና ቁርጠኝነት መከላከል ለማድረግና አንድ ቀን ሰብሮ ለመውጣት በእልህ የመንፈስ ዝግጅት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በምሥራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ መልሶ ማጥቃት የተካፈለው 29ነኛ ብርጌድ በቅድሚያ መሰንዘር የነበረበትን ጥቃት እንዲከፍት ግዳጅ ተሰጥቶታል፡፡ ሠራዊቱ ከአሰብ ተሳፍሮ በምድር ነኮች ጉርጉርሱም ላይ እንዲወርድና በቀጥታ ናኩራ ላይ(ዳህላክ ደሴት) ሠፍሮ ሥልጠናውን ይበልጥ እንዲያዳብር ተወሰነ፡፡ የዚሁ ክፍል አካሎች የሆኑት 10 ቲ-55 ታንኮችና አንድ 122 ሚሊ ሚትር ባትሪ ሞርተሮች ምፅዋ ወርደው መከላኪያው የበለጠ አስተማማኝ እንዲሆን አደረጉ፡፡

29ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ በዚያች የበሬ ግንባር በምታክለው መሬትና በዚያ ከባድ የአየር ሁኔታ ላይ ሥልጠናውን ለሥስት ወራት ማድረጉ በእውነቱ ምፅዋ ላይ ለተገኘው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ በተከታታይ እስከ አሥመራ፣ ቀጥሎም እስከ አልጌና ድረስ ለተደረገው ማጥቃት ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በመካከሉም ወቅት የወገን ጦር የሚገናኘው መሬት ላይ በተዘረጋው ስልክ በመሆኑ ጠላት የግንባሩን ሆኔታ፣ የዘመቻውን ጊዜና ወቅት በፍፁም ለማግኘት አልቻለም፡፡ የውስጥ አሻጥረኞችም አልነበሩም፡፡ ጠላትን ለማሳሳት በታቀደው መሠረት ከውጊያው ቀን በፊት ለአስር ቀናት በ 11፡30 ሰዓት ልክ እንደ ተኩስ ዝግጅት መድፎችና ሞርተሮች በሙሉ በጠላት ላይ የተኩስ ውርጅብኝ ያወርዱ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ ጠላት የመታኮሻውን ሥፍራ ትቶ ወደ መጠለያ ምሽግ እንዲገባና አናቱን እንዲቀብር ለማድረግ የታሰበ ነበር፡፡

ሐምሌ 4 ቀን 1970 በታላቅ ምሥጢር የግብረኃይሉ አዛዥና የዘመቻ መኮንኑ፣ ከባህር ኃይል ደግሞ የቤዝ አዛዥ፣ የመርከብ አዛዦች፣ የ29ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ ዘመቻ መኮንኖች ስብሰባ ተጠራ፡፡ ተሰብሳቢው በምድረ ነኮች ተሳፍሮ ማታ ምፅዋ ሲደርስ የመርከቦቹ ድምፅ እንዳይሰማ ከባድ ተኩስ ወደ ጠላት ምሽግ መዝነብ ጀመረ፡፡ በዚህ መካከል በአጭር ጊዜ ጦሩ ወደ ተመደበለት ቦታ ገብቶ ቦታውን ያዘ፡፡

ጊዜው ከምሥራቅ የመጣው ጦር ያለምንም ዕረፍት መቀሌና ጐንደርን መሰባሰቢያ ወረዳው በማድረግ ራሱን በግብረ ኃይል አቋቁሞና ተደራጅቶ ትዕዛዝ የሚጠባበቅበት ሰዓት ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ 505 ግብረ ኃይል ምፅዋ ለይ፣ 508ኛ ግብረ ኃይል አሥመራ ዙሪያ ተደራጅተው ውጊያ የሚከፈትበትን ቀን(d-date) ይጠብቁ ነበር፡፡

በዕቅዱ መሠረት ሐምሌ 6 ቀን 1970
• 501 ግብረ ኃይል፣ በሁመራ ግንባር
• 502 ግብረ ኃይል፣ በባድመ አድርጐ ወደ ባሬንቱ፣
• 503 ግብረ ኃይል፣ ወደ ደቀመሐረ፣
• 505 ግብረ ኃይል፣ ምፅዋን እንዲያጠቃ ነበር፡፡
505 ግብረ ኃይል ይዞታውን እንዲያሰፋ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ውጊያው በኀብረት ተከፈተ፡፡ ጀግናው 505ኛ ግበረ ሐይል በኢትዮጵያ አየር ኃይልና ባሕር ኃይል የተኩስና የቅኝት ድጋፍ ውጊያውን ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ በሙሉ ቁርጠኝነት ተያያዘው፡፡ የጨበጣው ውጊያ ከመጀመረሩ በፊት የተለመደ የተኩስ ዝግጅትን የሚመስል ግን እውነተኛው የአርባ አምስት ደቂቃ ደብደባ ጠላት ላይ ሲወርድ ጠላት በአንፃሩ የወትሮው የተኩስ ዝግጅት መስሎት አንገቱን በመጠለያ ምሽጉ ቀበረ፡፡

ውጊያው እንደ ተደተከፈተ ዋናው ችግር ያንን በፊንጂ የታጠረውን ሜዳ እንዴት አድርጐ ማለፍ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ወደ ሻዕቢያ ምሽግ ከመድረሱ በፊት ብዙ ሠራዊት እንደሚያልቅ ሁሉም ተገንዝቦታል፡፡ ከጀግናው 8ኛ ብርጌድ አንድ ሻለቃ ጦር በደረቱ ተስቦ ፈንጂውን በራሱ ላይ አምክኖ የወገን ጦር በሬሳው ላይ እንዲረማመድ ፈቃድ ጠየቀ፡፡ ከ8ኛው በርጌድ 211ኛ ነበልባል ሻለቃ ከመቶ የማያንሱ ወታደሮችን በሲኒማ አይዳና በሚካኤል ቤተክርስቲያን መከከል በሚገኘው ጠባብ ወረዳ በሻዕቢያ በተጠመዱት ፈንጂዎች ላይ የራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ “እኛ ስንሰዋ በእኛ እሬሳ ላይ ተረማምዳችሁ ምሽጉን ሰበሩ” ብለው በፈጸሙት አኩሪ የጀብዱ ሥራ ሠራዊቱ በእነሱ ሬሳ ላይ በመረማመድ በጨው ረግረግ ላይ ተስቦ ከሻዕቢያ ጦር ጋር ፍጹም ጀግንነት የተሞላበት ውጊያ አደረገ፡፡ ሳንጃ ለሳንጃ፣ ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቁ ወንድማማቾች ተላለቁ፡፡ በዚህም መልክ ሚካኤል አጠገብ የነበረው የሻዕቢያ ምሽግ ተሰበረ፡፡

LEAVE A REPLY