ሊነበብ የሚገባው አጭር መልእክት-የዛሬው የፍርድ ቤት ውሎዬ /ወይንሸት ሞላ/

ሊነበብ የሚገባው አጭር መልእክት-የዛሬው የፍርድ ቤት ውሎዬ /ወይንሸት ሞላ/

በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጭላንጭል ብርሃን የሚታያቸው ታላላቅ ሰዎች ናቸው!!!

በተቀነባበረ የሃሰት ክስ አራዳ ፍርድ ቤት ዛሬ ለፍርድ ቀርቤ ነበር፡፡የእለቱ ዳኛ የተቀነባበረው ክስ፣ የፖሊስ አባላት የነበሩትና አጥንተው መጥተው የሰጡትን የሃሰት ምስክርነት እንዲሁም የእኔን የመከላከያ ምስክሮች ቃል በንባብ ማሰማት ጀመረ፡፡በመጨረሻም በዓቃቢ ህግ ምስክሮች በአንዋር መስጅድ ወረቀት ስትበትንና ድንጋይ ስታስወረውር ይዘናታል በማለት የሰጡትን ምሰክርነት ስንመረምረው “አንድ ፖለቲከኛና በህዝብ ዘንድ የሚታወቅ ሰው እንደዚህ ያለውን ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በእስልምና እምነት ተከታዮች መሃል ያውም መንገድ ላይ ሱሪ ለብሳ ታደርገዋለች ብሎ ማሰብ የልጅቷን ጤነኝነት መጠራጠር ነው፣አንድ የክርስትና እምነት ተከታይ እራሱን ሳያመሳስል ይህንን ያደርጋል ተብሎ አይታመንም” በማለት የአቃቢ ህግ ምስክሮች የምስክርነት ቃል የተጠና እና ወጥ ያልሆነ መሆኑንና ድርጊቱን አለመፈፀሜን ገልፆ በነፃ እንድሰናበት ወስኗል፡፡

ይህ የዛሬው ውሎዬም ነፃ የዳኝነት ስርዓት ቢኖረን በሀገራችን ብዙ ኢትዮጵያውያን እየተሰቃዩበት ያለው ክስ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ አሳይቶኛል፡፡የተጫነባቸው የፈጠራ ክስ በአውነት ፊት ሲመዘን ጤነኛ ሰው የማያደርገው ነው ተብሎ እንደሚመዘን ሳስብ የብዙ የትግል ጓዶቼን ሲቃይና መከራ አስታወሰኝ፡፡በሀገሬ ተስፋ የማልቆርጠውም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነው ለህሌናቸው የሚያድሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ስለማምን ነው፡፡እንግዲህ ያሁሉ ድብደባ ተፈፅሞብኝ ህክምና ተከልክዬ ለአንድ ወር ያህል በእስር የማቀቅኩበት እና የተመሰረተው ክስ ከእውነት ጋር ሲቆም ጤነኛ የሆነ ሰው የማያስበው ሆነ ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም በአስቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን ከእኔ ጋር የነበራችሁና የትግል መንፈሳችሁን ለመስበር በሃሰት ክስ በሲቃይ ላይ ሆናችሁ በሙሉ ልብ የነበረውን ሁኔታ ምስክረነታችሁን ለሰጣችሁን ለጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እና ለዮናታን ተስፋዬ እንዲሁም የፍትህ ስርዓቱ አደጋ ላይ መሆኑን ብናውቅም ጉዳዩን ለታሪክ ለማስመዝገብና የተመሰረተብኝን የፈጠራ ክስ፣ የተጠናውን የፖሊስ አባላት ምስክርነት በማጋለጥ ድጋፍ ላደረክልኝ ለጠበቃዬና ለጓደኛዬ አዲሱ ጌታነህ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡

ሁሌም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን አምናለሁ ትግሉ ይቀጥላል!!!

LEAVE A REPLY