የነገድ ሰፈራና ሰብአዊ መብት /ፕሮፌ. ጌታቸው ኃይሌ/

የነገድ ሰፈራና ሰብአዊ መብት /ፕሮፌ. ጌታቸው ኃይሌ/

ወያኔዎች ክልል የሚባል ፖለቲካ አምጥተው የታሪክ ሂደት አንድ ሀገር፥ አንድ ሕዝብ፥ አንድ ኢትዮጵያ ያደረገንን፥ ወደኋላ መልሰው፥ ብዙ ሀገሮች፥ ብዙ ሕዝቦች፥ አልቦ ኢትዮጵያ አደረጉን። መንሥኤያቸው ግልጽ ነው። በነሱ አስተሳሰብ፥ መንግሥቱ የትግሬዎች ነበር፤ አማሮች ወሰዱባቸው። እንደሚመስላቸው፥ የተጐዱት ኢትዮጵያ በአማሮች ትጋት ከትግራይ ውጪ የተስፋፋች ጊዜ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ኢትዮጵያን ማን እንዳኮማተራት እንጂ ማን እንዳስፋፋት፥ መቸ እንደተስፋፋች የሚያስረዳ ሰነድ የለንም። ያሉት ማስረጃዎች የሚያመለክቱት፥ ከአጼ ዓምደ ጽዮን ጀምሮ የነገሡ ነገሥታት በዛጔዎች ዘመንና በዘመነ መሳፍንት የተዳከመችውን ኢትዮጵያ ሲያጠነክሩ፥ የጠፋውን ሲያገኙ፥ የተቈረጠውን ሲቀጥሉ ነው። ከአማራ ክፍለ ሀገር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንም እንዴት አማራ የሚለውን ስም እንደወረሱ የነገረን የለም። ያለን ጭላንጭል፥ የንጉሡ ወታደሮች አማሮች ስለነበሩ፥ ዘምተው እዚያው ለቀሩበት አገር ሕዝብ ስማቸውን አወረሱት የሚል ነው። አሁን ወያኔዎች የሚያደርጉት ጥረት መኖሩ ገና ያልተረጋገጠውን የትግራይን ክብር ከኢትዮጵያ ነጥቆ ማጎናጸፍና (ትንሣኤ ትግራይ) ኢትዮጵያን አልቦ (የሌለች) ማድረግ ነው። ከኢሐፓ ጋር የነበራቸው ቅራኔ ይህ ነበር። እነሱ ወይ ትግራይ ወይ ሞት ሲሉ፥ ኢሐፓዎች ወይ ኢትዮጵያ ወይ ሞት አሉ።

ያልተረጋገጠ የትግራይ ክብር የምለው፥ የምንኰራበት አክሱም ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንጩ የኛ አባቶች ናቸው የሚሉትን ነው። የአክሱም መንግሥት ሲወድቅ ንጉሡ የሸሸው ወደማን ዘንድ እንደሆነ፥ መንግሥቱን በ1263 ዓመተ ምሕረት ያስመለሰው የልጅ ልጁ እንደሆነ ያልሰሙ ይመስላሉ።

ወያኔዎች ከትንሣኤ ትግራይ ዓላማቸው ለመድረስ የሚያደርጉት አንዱ የአድፍጦ እርምጃ ለጎሳዎችና ለነገዶች መብት የሰጡ መስለው መገኘት፥ አማራን በደለኛ አድርጎ ማሳየት ነው። ትግራይን በሚያስፋፋ ዘዴ ነገዶችን በክልል አጥሮ ማስቀመጥ የነገዶች መብት ማስከበር ሊሆን አይችልም። እንኳ ሰው ከብትም ቢሆን በአጥር ቢከልሉት ይወራጫል እንጂ፥ ባለውለታ አይሆንም። በወያኔ የክልል ፖለቲካ ደስተኛ ካለ፥ ከጥንቲቱ ኢትዮጵያ ላይ ከሚገባው በላይ ተቦጭቆ የተሰጠው ወገን ብቻ ነው። እሱም ቢሆን ተከልሎ የተሰጠው መሬት ምንም ትልቅ ቢሆን ትልቋን ኢትዮጵያ ለመንፈግ መሆኑን ልብ ሊለው ይገባ ነበር። ለዘመኑ አስተሳሰብ ኋላ ቀር ስለሆንን የትልቅነትና የዲሞክራሲ ጥቅም አይታየንም።

በነገድ መስፈር ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ፥ አማራ፥ ትግራይ፥ በጌምድር፥ ወሎ፥ አሩሲ፥ አገው ምድር፥ የሚባሉት ክፍለ ሀገሮች የሚጠሩት በጥንት ሰፋሪዎቹ ስም ነው። ግን አሰፋፈራቸው የፖለቲካ ትርጕም አልነበረውም። አዲሱ ነገር ወያኔ ያመጣው ከፖለቲካ ጋር ማያያዝ ነው። ነገዶች በመሬቱ ላይ በብዛት ስለሰፈሩበት እንደመንገድ፥ እንደ ትምህርት ቤት፥ እንደ ሐኪም ቤት በስማቸው ተጠራ እንጂ የመሬቱ የጅምላ ባለቤቶች አልነበሩም። በመንገዱ ላይ ማንም መንገደኛ።

እንደሚሄድበት፥ በትምህርት ቤቱ ማንም ልጅ እንደሚማርበት፥ በሐኪም ቤቱ ማንም ሕመምተኛ፥ እንደሚታከምበት፥ በነዚህ ክፍለ ሀገሮች ማንም የንጉሡ ዜጋ (ኢትዮጵያዊ) ሊኖርባቸው መብቱ ነው። የሀገሩ ባለቤት አስገባሪው ንጉሡ ብቻ ነበር።

ነገዶች መብታቸው የሆነውን መብታቸው ካልሆነው ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል። መብቶቻቸው የሚባሉት በተባበሩት መንግሥታት የተወሰኑት ብቻ ናቸው። ከዚያ ያለፈ መብት አይጓጉ፤ የሌሎች መብት መንካት ይሆናል። መብቴን አትንኩብኝ ይባላል እንጂ መብታችሁን ልንካ አይባልም፤ የሌላውን መብት መጋፋት ወንበዴነትና የወያኔ ግብር-አበርነት ነው። ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር የኢትዮጵያውያን ሁሉ ስለሆነች፥ ነገዶች የጋራ ኢትዮጵያዊ መሬትን ከልሎ የግል ሀብት የማድረግ መብት የላቸውም። መሬትም ሆነ ወይም ማንኛውን ጥሪት የግል የሚሆነው ወይ በግዢ ወይ በውርስና በስጦታ ነው። የጎሳ ሀብት ባህልን ማዳበር፥ ሃይማኖትን ማስተማር፥ ማኅበር ማቋቋምና የመሰሉትን ማኅበራዊ ሥራዎች መሥራት ነው። ከዚህ አልፎ በወያኔ የክልል ፖለቲካ የሚያምን ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላት ነው። የጠላትነቱ ምንጭ ኋላ ቀርነት ነው።

LEAVE A REPLY