ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ተፈረደበት ቅጣቱን ከአንድ ወር በኋላ ይጨርሳል

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ተፈረደበት ቅጣቱን ከአንድ ወር በኋላ ይጨርሳል

/Ethiopia Nege News/፦ የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 7(1)ን በመተላለፍ፤ ከግንቦት ሰባት ድርጅት አመራሮች ጋር  በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ የተለያዩ  መረጃዎችን  በማስተላለፍ በሚል በፌ/አ/ህግ የቀረበበት የሽብርተኝነት ክስ ውድቅ ተደርጎ፤ በመደበኛው  የወንጀል ህጉ አንቀጽ 257(ሀ/መ) በመተላለፍ ተከላከል ተብሎ በእስር ላይ የቆየው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ  የነበረው ጌታቸው ሽፈራው ዛሬ አንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራት ተፈረደበት።

ተከላከል የተባለበት የወንጀል ክስ ዋስትና የማያስከለክል ቢሆንም ከፍተኛ ፍ/ ቤት ዋስትና በመከልከሉ ከታህሳስ 15/2008ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።

ጌታቸው ሽፈራው የመጀመሪያ ስራውን  የጀመረው INSA(Information Network security Agency) ቢሆንም  የቀድሞን ጠ/ሚኒስት መለስ  ዜናዊን ተችተህ ፃፍክ በማለት በኢንሳ  ባለስልጣናት ልዩ ትዕዛዝ “ ከስራው”  እንደተባረረ በወቅቱ በሚዲያ ገልጿል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ከመሆኑ በፊ፤ በመሰናዘሪያ ጋዜጣ፣እንቁና ላይፍ መፅሔት በአምደኝነት ሰርቷል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው በሚቀጥለው ሰኔ 15 ከታሰረ 18 ወራት ስለሚሞላው የእስር ጊዜውን ጨርሶ እንደሚወጣ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY