🔨 የግንቦት ሀያ ወግ 🔫 /በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ/

🔨 የግንቦት ሀያ ወግ 🔫 /በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ/

ኢሕአዴግ ለምን ዴሞክራሲ ማምጣት ተሳነው?

🔨 የግንቦት ሀያ ወግ 🔫

ሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት በአውራ ፓርቲ ሥም፣ አሀዳዊ ፓርቲ ስርዓት ዘርግቷል፡፡ መላ አገሪቱ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ የተቃኙ፣ የአንድ ፓርቲ ሰዎች እንዲሞሉት አድርጓል፡፡ ይህ አመል ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የመጣ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሕወሓት ከቀድሞ ወዳጁ ሻዕቢያ የተማረው “በአንድ ሜዳ ሁለት ኃይል አይኖርም” የሚል አባባል አለው፡፡ በዚህ ፍልስፍና ሻዕቢያ ጀብሃን አጠፋ፡፡ ሕወሓት ደግሞ ግገሓት(?)፣ ኢዴኃ (EDU)፣ ኢሕአሠን በኃይል ደምስሷል፡፡ ሕዋሓት ደርግን ከመደምሰሱ በፊት አምባገነኑን ደርግን እንወጋለን ብለው ግን ደግሞ ከሱ በጥቂቱ የተለየ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዘው ከጎኑ የተሰለፉ ኃይሎችን አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህ የጫካ አመሉ ያደገበት ሕወሓት (ኢሕአዴግን ለብሶ) ከተማ ሲገባ የቱንም ያክል “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው” እያለ ቢፎክርም፣ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን መታገስ አልቻለም፡፡

ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን ቀርቶ በውስጡ የሚከሰቱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን እንኳን መታገስ አይችልም፡፡ ትግል ላይ በነበሩት ጊዜ የተነሳው የመጀመሪያው ‹ሕንፍሽፍሽ› (ቀውስ) ‹የአሽዓ (አክሱም፣ ሽረ እና አደዋ) ሰዎች የሥልጣን የበላይነት (ልክ አሁን የትግራይ ልሒቃን የሥልጣን የበላይነት በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በዛ እንደምንለው) ፓርቲያችን ላይ እየታየ ነው› የሚል አቤቱታ ያቀረቡ አባላቱን በማስወገድ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በ1993 በተፈጠረው ቀውስ ደግሞ የሉአላዊነት ጥያቄ ያነገቡ አባላቱን የውስጥ ሕገ-ደንቡን (ሕወሓትን በማዳን ስም) ሽሮ፣ ምርጫ ቦርድ ባለበት አገር በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ማሕተም የተፃፈ ደብዳቤ ነበር ያሰናበታቸው፡፡ ይህ ባሕል ከጫካ ተከትሏቸው የመጣ ባሕል ነው፡፡ ወ/ሮ የውብማር አስፋው ‹ፊኒክሷ ሞታም ትነሳለች› ባሉት መጽሐፋቸው እንዲህ ይሉናል፦

“በሕወሓት ደንብ መሠረት አንጃ መፍጠር እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ያስከትል ስለነበር፣ የሕወሓት ፖሊት ቢሮ ይህንን ሲያስቀምጥ በማኅበሩ አመራር ውስጥ የማይፈልጋቸውና የሚጠላቸው የአመራር አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመለክት ነበር፡፡ …” (ገጽ 112፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ እንዳጣቀሰው)

እነዚህ ችግሮች ሥር ሰደው ነው የአሁኑን አማራጭ ሐሳብ የማይቋቋም ኢሕአዴግ የፈጠሩት፡፡ ይህንን የ1993ቱ የሕወሓት ቀውስ ወቅት ከፓርቲው ከወጡት ታጋዮች መካከል አረጋሽ አዳነ ለጥሕሎ መጽሔት በሰጡት ቃለምልልስ ከሥር ከሥሩ ባለመታረሙ የመጣ ጣጣ ነው በማለት ከታሪክ እንድንማር ይመክሩናል፦

“እነዚህ ሁሉ [ጥያቄዎችን በኃይል የመጨፍለቅ] ችግሮች ገና ድሮ ከመፈጠራቸው፣ [ሥ]ር ከመስደዳቸው በፊት ቀደም ብለን ለዚህ ሁሉ መሠረት የሆኑትን ችግሮች […] አስተውለን ከሥር ከሥር ወይም ደረጃ በደረጃ እየታገልናቸው ያለመምጣታችን አሉታዊ ፍፃሜ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡” (ገጽ 77፣ ዮናስ በላይ፣ የትግራይ ሕዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ)

የቀድሞ የሕወሓት ታጋዮች ፀፀትም ሆነ የአሁን ታሪኩ የሚያስተምረን ዴሞክራሲ መንገድ እንጂ መዳረሻ አለመሆኑን ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያልመጣ ኃይል ዴሞክራሲን ሊያመጣ አይችልም፡፡

LEAVE A REPLY