ቴዲ አፍሮ እና ሠርፀ ፍሬስብሃት /የሙዚቃ ሀያሲ/

ቴዲ አፍሮ እና ሠርፀ ፍሬስብሃት /የሙዚቃ ሀያሲ/

“ሙዚቃችንን ዕውቀት እየመራው አይደለም”- ሠርፀ ፍሬስብሃት

በኪነ-ጥበብ ሰዎች በኩልስ ወደ ሰው ሁለንተና የሚቀርቡ የሙዚቃ ሐሳቦች ይነሳሉ? …ለዚህ ጥያቄ የምሰጠው ምላሽ ብዙ ሰዎችን ሊያስከፋ ይችላል፤ ግን እውነት ስለሆነ ማለዘብ አልፈልግም:: ልልህ የምችለው በአጭሩ “ሙዚቃችን ዕውቀት እየመራው አይደለም” ነው:: አንድ ሙያ ሊያድግ የሚችለው ንድፈ ሐሳብ (ቲዮሪ) እየቀደመ ተግባር (ፕራክቲስ) እየተከተለ ሲሄድ ነው:: አንዳንዴ ተግባር ቀድሞ ንድፈ ሐሳብ ሊከተልም ይችላል:: ሁለቱም በቅብ ርቀት መገኘት አለባቸው:: ያለንድፈ ሐሳብ የሚኖር ተግባር ደመ-ነፍሳዊ ይሆናል::

ለምሳሌ የምሽት ቤቶችን ውሰድ፤ ልጆቹ የሚለማመዱባቸው መድረኮች እንጅ ዕውቀት የሚፈጥሩባቸው አይደሉም::፡ ስለዚህ እነሱ በእነዚያ ምሽት ክበቦች ስለዘፈኑ “ሙዚቃ አድጓል” አይባልም::

ድርሰት የሚባለው ፈጠራንና በሰፊው ማሰብን የሚጠይቅ፣ ከማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈልቅ ወይም ማኅበረሰቡን ወደፊት የሚያራምድ ቀዳሚ ዕይታ ነው:: መነሻው ማኅበረሰባዊ ትርክቶች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ንባብ፣ ምልከታ፣ ምናባዊ ተረክ(ኢማጅኔሽን)፣ … ሊሆን ይችላል:: የኛ ሙዚቀኞች ግን ለእነዚህ የታደለ ተሰጥዖ የላቸውም:: አብዛኞቹ ሙዚቀኞች ሕዝቡን አያውቁትም፤ ራሳቸውን በሆነ ቀለበት ውስጥ አስገብተው የሚኖሩ ናቸው::

ስለዚህ በጥልቀት ለማታውቀው ሕዝብ ከቆንጆ ልጅ ውበት የዘለለ ሙዚቃ መፍጠር ያቅትሀል፤ ለነገሩ ቆንጆዋም የምትደነቅበትን ለዛና ውበት ከባሕሉና ከሕዝቡ ውጭ ማግኜት ከባድ ነው::

አብዛኞቹ ሙዚቀኞች ከባሕሉ የተነጠሉ ናቸው፤ ከባሕሉ በተነጠሉ ቁጥር ደግሞ ከፈጠራም ይነጠላሉ:: ስለዚህ እቤታቸው በራሳቸው ቀለበት ውስጥ ሆነው ያዩዋትን ቅንጫቢ ሐሳብ ይዘው ስቱዲዮ ይገባሉ:: ይህ በመሆኑ ሕዝቡ “የኔ” የሚለው ፈጠራ አያቀርቡም::

ከእነዚህ ሙዚቀኞች በብዙ ርቀት ለይቼ የማየው ቴዎድሮስ ካሳሁንን ነው::… ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን ታሪክ ያነበበትና የተረዳበት፣ ማኅበረሰባዊ ንግርት የፈጠረበት መንገድ፣ ምዕናባዊ እሳቤ የፈጠረበት አካሄድ ሁሉ የተለዬ ነው::

እንዳለመታደል ሆኖ በሱ መንገድ የሚሄዱ ተከታዮች አላፈራም:: አድማጭ እንጅ ተከታይ ባለሙያ አልተገኘለትም:: በነገራችን ላይ የቴዎድሮስ መንገድ እንዲሁ ከቤቱ ተቀምጦ የተከፈተለትም አይመስለኝም፤ በጣም ያነባል፤ ወደ ሕብረተሰቡ ታሪክ ጠልቆ ይገባል፣ ከብዙ ሰዎች ጋርም ይነጋገራል፤ …::

ቴዲ እንደሌሎች ቀለበት ውስጥ ራሱን ያልከተተ ሰው ነው:: ሥራዎቹ ከዕለት ተዕለት ገጠመኙና አስተሳሰቡ፣ ከማኅበረሰቡ አረዳድ፣ ከኪነ-ጥበቡ መሻት ጋር የተዋሐዱ ናቸው::

ፍቅር እስከ መቃብርን እኮ ሁላችንም አንብበነዋል፤ ሁሉንም ገፀ-ባሕርያትና ድርጊታቸውንም እናውቀው ይሆናል፤ እንደ ቴዲ ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ግን የጎጃምን ሁለንተና ማናችንም ገልፀንበት አናውቅም፤ በቃ ፈጠራ እንዲህ ነው::

ምሁራዊነት የታከለበት ጥበብ የለንም፤ ስለዚህ ነው በጨረተ ሙዚቃ የምንደርቀው:: በእነጥላሁን ገሰሰ ጊዜ በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ ወደ ፍልስፍና ደረጃ የደረሱ የግጥም ደራሲያን ነበሩን፤ እነሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ … ነበሩ:: እነዚህ ሰዎች ሙዚቃውን ከብዙ ምንጭ ስለሚቀዱት ያረካን ነበር::

ወደ በኋላ የመጡት በእነአበበ ተካ አካባቢ ደግሞ እንደነሙሉጌታ ተስፋዬ ዓይነት ገጣሚዎች ነበሩ፤ የወሎ፣ ዋግና ሌሎችም አካባቢዎችን ባሕል ጠንቅቀው የሚያውቁ:: ከዚያ ተነስተው የ“ወፊቱ”ን ድርሰት ያፈለቁ ናቸው::

ዛሬ ከእነዚያ አልፈን “ትብላው ብሬን” የሚል ሙዚቃ ላይ ደረስን፤ ድርሰቶቻችን ሄደው ሄደው “ፍቅር ወጣ ወጣ!” የሚባልበት ዘመን አደረሱን:: ከዚህ በላይ ከባሕላችንና ማንነታችን መነጠላችንን የሚሳይ የለም፤ በዚህ ማንም ላይደሰት ይችላል፤ ግን የማያስደስተን ሁሉ ስህተት አይደለም፤ ይህ እውነት ነው::

እኔ ባለኝ አቅም ልክ ሙዚቀኞቻችንና ሙዚቃን ለማገናኘት ጥረት አድርጌያለሁ፤ ግን አይችሉበትም:: የጣዕም ልኬት ፕሮግራምን እንኳ አድማጭ እንጅ ሙዚቀኛው አይከታተለውም:: ሙዚቀኞቹ ለምሁራዊ ውይይት የሚበቃ የአረዳድ ደረጃም ፍላጎትም የላቸውም:: ለዚህም ነው ሙዚቃችን እየቀጨጨ የመጣው፤ ለዚህ እኮነው ይህንን ትውልድ ቁጭ ብድግ የሚደርግ ሙዚቃ መሥራት ያቃተን:: ለዚህ ዘመን የሚመጥን ሙዚቃ እኮ ስለሌለን ትውልዱ ወደኋላ ተመልሶ የ60ዎቹንና 70ዎቹን ሙዚቃ እያዳመጠ ነው::

(በኩር ጋዜጣ ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም)

LEAVE A REPLY