ገንዘቤን ይጭነቀው – የኳታርና ሳውዲ ነገር /ኤፍሬም እንዳለ/

ገንዘቤን ይጭነቀው – የኳታርና ሳውዲ ነገር /ኤፍሬም እንዳለ/

“ልጅሽ የት አገረ ነው የሄደችው?”

“ኳታር የሚሉት አገር፡፡”

“እሰይ፣ እሰይ…”

እውነትም ‘እሰይ፣ እሰይ’ ያሰኛል፡፡ በየጓዳችን ስለ ኳታር ሲወራ እኮ አንሶላውና ብርድልብሱ ሳይቀር በዶላር ተገጣጥሞ የሚሰፉባት አገር ትመስላላች፡፡

አዎ፣ ኳታር ሀበታም ነች፣ ያውም ቅልጥ ያለችው ሀብታም፡፡ ግን ሀብታም ማለት ደግሞ ሁልጊዜ ፋሲካ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡

ማለዳ በትልቅ ማንኪያ ማር፣ ምሽት በትልቅ ማንኪያ ማር…የአብዛኞቹ የኳታር ሰዎች የዕለት በዕለት ልምድ፡፡ አማካይ ዕድሜ 78.1 የሆነው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ አሁን ግን ማር ወዳጆቹ እንደ እሬት የመረረ ጊዜ ገጥሟቸዋል፡፡ ምናልባትም ማር የለመደውን ምላስ በስኳር እሹሩሩ ማላት ይኖርባቸው ይሆናል፣ ያውም ስኳሩ እንደልብ ከተገኘ!

ሳውዲና አጋሮቿ አደሙባት፣ ልክ “ኳታር ያለውን በሳንጃ ሆዱን” የተባለ ይመስል፣ ልክ “ኳታርን የተወዳጀ ዓይኑ ጨለማ፣ እግሩ ቄጤማ” ይሁን የተባለ ይመስል ‘እኔም፣ እኔም’ እየተባባሉ አደሙባት፡፡ በስማ በለው የተማከሩ ይመስል የአየር፣ የምድርና የባህር በሮችን ሁሉ ከረቸሙባት፡፡ “የእኛ ሀብታም፣ የምትሆኝውን እናያለን” ነው ነገሩ፡፡ የዕለት ጉርሷን ከውጪ ለምታስገባው ኳታር ዙሪያ ክብ የእሾህ አጥር አስቸጋሪ ነው፡፡

ሚጢጢ አገር እኮ ነች – ኳታር፡፡ ለአገር ይሠራ እንደሁ እንጃ እንጂ ‘ከአፍ የወደቀች ጥሬ’ የምትባል አይነት፡፡ የጨርቆስ ልጆች አንዴ “ሆ…” ብለው ቢሄዱ ባይውጧት ነው! ህዝቧ ከሁለት ሚሊዮን ተኩል ትንሽ ቢዘል ነው፣ ሦስት መቶ ሺህ፣ ቀሪዎቹ መጤዎች፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ በዓመት ከ130‚000 ዶላር በላይ ነው፡፡ ምን የነፍስ ወከፍ ገቢ ነው፣ የአውራጃ በጀት ነው እንጂ!

እና….እዚች ሚጢጢ አገር ይሄ ሁሉ ‘ዓይንሽ ለአፈር’ ምን አመጣው! ያመጣውማ “ሽብርተኞችን ትደገፋለች” “እኔ እንዲህ አይነት ነገር ሰያልፍም አይነካኝ፣” አይነት የሚል በተለይ ከሳውዲ ጋር ያላት የከረመ እሰጥ አገባ ነው፡፡ ሳውዲዎቹ “ተይ ለሙስሊም ወንድማማቾች፣ ለሀማስና ለሌሎች ሽብርተኞች የምትበትኚውን ገንዘብ አቁሚ፣ ከኢራን ጋር ‘በአንድ እንትን እንትን እንበል’ ግንኙነትሽን ገደብ አብጂለት” ስንላት ስንት ዘመናችን ነው የሚሉት፡፡

የሙስሊም ወንድማማቾች እኮ ግብጽ ውስጥ ስልጣን የያዘው በምርጫ ነው፡፡ መሀመድ ሙርሲ ታንክ ደርድረው፣ ሳንጃ ወድረው ቤተመንግሥት ሰተት አላሉም፡፡ የግብጽ ህዝብ ነው “ይመችህ፣ ሰተት ብለህ ግባ” ያላቸው፡፡ እና “የግብጽ ህዝብ የመረጠውን ቡድን ብትደግፍ ምን ሀጢአት አለው!” የሚሉ አሉ፡፡ “ሳውዲዎች ራሳቸው በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሽብርተኛ ድርጅቶች ደጋፊ አይደሉም እንዴ!” ይሏቸዋል፣ ከሦስት ሺህ ሰው በላይ ሰው ያለቀበትን የአሜሪካ የሽብር ጥቃት እያስታወሱ፡፡

“ከኢራን ጋር ያለሽን ‘ፍቅሬ ፍቀሬ በዛ’ አቁሚ” የሚሉት ነገር ለኳታር የሚዋጥ አይሆንም፣ የህልውና አደጋ የሚያስከትል ነውና፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለ የባህረ ሰላጤው ውሀ አካል ስር 43 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የጋዝ ክምችት አለ፡፡ የማውጣት መብቱ ደግሞ የኳታርና የኢራን ነው፡፡ እንዲህ ሆኖ ኳታር ለምን ብላ ነው ከኢራን ጋር የምትኳረፈው!

ለምን ብላ ነው ገመዷን እንደ በጠሰችው በቅሎ የምትሆነው! በዶሀ ዶፉን እያወረደው በሪያድ ለምን ጸሀይ ይሆናል!

ዋናው ምርቷ የተፈጥሮ ጋዝ መሆኑ በሳውዲ ተጽእኖ ስር ነው ከሚባለው የነዳጅ ላኪ አገሮች ድርጅት ንክኪ አትርፏታል፣ በጎረቤቶቿ አልተወደደላትም እንጂ፡፡ ምክንያቱም “ዋ! የምትባዪውን አታድርጊና አይደለም ማኛ ጤፍ እንጀራ፣ የዘንጋዳ ድርቆሽም አታገኚም” ብሎ ለማስፈራራት አልተመቸችማ! “ከእኛ ጋር አብሪ፣”… “ከእኛ ጋር ብቻ ጽዋ ጠጪ፣” … “በእኛ ሳምባ ተንፍሺ” ለማለት አልተመቸችማ! ሲጀመርማ፣ የተፈጥሮ ጋዝን “አሁን ምርት ተገኘና ነው!” ብለው ነበር ሀብታሞቹ ጎረቤቶቿ፡፡

ጥቅሙ ሲገባቸው ግን በቅናሽ ዋጋ ትሸጥልናለች ሁሉ ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ ኳታር ግን “ቅናሽ ነው! ሲያምራችሁ ይቅር!” አለች፡፡

ያበጠውን ቁርሾ አንደኛውን ‘ጦሽ’ ያደረገው ክስተት ላይ ላዩን ላየው፣ “አሁን ይሄ እዚህ ያዳርሳል!” የሚያስብል ነው፡፡…እስራኤልና ኢራንን የሚያወድስ ጽሁፍ በኳታር መንግሥታዊ የዜና አገልግሎት ይወጣል፡፡ ጻፉት የተባሉት ደግሞ ኤሚሩ ናቸው፡፡ በሪያድ ደምም፣ ስኳርም ከፍ አለ፣ ንዴትም ሆነ፡፡

“ይቺ ሚጢጢ እንዴት፣ እንዴት ነው የሚያደርጋት!” አይነት ነገር ተባለ፡፡ ኳታር ‘እጄ የለበትም፣ ተንኮለኞች የለጠፉት ነው’ አለች፣ ትረምፕ ‘ፌክ ኒውስ’ እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ የአሜሪካ የስለላ ተቋማትም ጣታቸውን ‘ነጭ እሾህ’ ያደረጓት ሩስያ ላይ ቀሰሩ፡፡ ሳውዲና ወዳጆቿ ግን ጆሯችውን ወደ ዝሆን ጆሮነት ለወጡት፡፡

በዛው ቢያበቃ ጥሩ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የኳታሩ ሼክ ታሚም፣ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‘ያመረቀዘው ቁስል ላይ ጨው’ ነሰነሱበት፡፡ በምርጫ ላሸነፉት ለኢራኑ ፕሬዝደንት ሃሰን ሮሃኒ ደወሉና “እንኳን ደስ አለዎት” አሏቸው፡፡ ሪያድም ጦፈች፡፡ ኤሚሩ ሆነ ብለው ‘ሳውዲዎችን ኮረንቲ ለማስጨበጥ’ ያደረጉት ነው ተባለ፡፡

ሳውዲዎች ኮረንቲ አልጨበጡም፣ “ኳታር ብትቀርስ ምን እንዳይመጣ ነው…” ብለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጠናል አሉ፣ የእገዳ መአትም ደረደሩ፡፡ አጋሮቻቸው ተከተሏቸው፡፡ ኳታር ግን “ማሩኝ፣ አይለምደኝም…” ብላ መሬት የምትልስ አልሆነችም፡፡

ለሰሚ ግራ የሆነው ነገር መተንፈሻ እንኳን ሳይሰጧት ሁሉንም ነገር ጫንቃዋ ላይ መዘርገፋቸው ነው፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን አቋረጡ፣ ድንበሮቻቸውን ዘጉባት፣ በየአገሮቻቸው ያሉ ዜጎቿን ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ ‘ከዚህ ጥፉ’ አሏቸው፣ “አውሮፕላኖችሽ በእኛ አየር ክልል ዝር እንዳይሉ” አሏት፣ “የአንቺን ፓስፖርት የያዙና የዶሀን አውሮፕላን ጣቢያን የረገጡ ሰዎች ዓይናችን አይይ” አሉ፡፡ ሳውዲ ሲያስነጥሳት አጋሮቿ ጉንፋን ያዛቸው፡፡ “ይህ ክ‘ክተት ሠራዊት፣ ምታ ነጋሪት’ ያልተለየ የእርምጃ ጋጋታ ምን አመጣው?” ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ‘አለ ነገር ወንዙን ስንሻገር’ የሚሉት ነገር የሚመጣው፡፡ (በእኛ በተራዎቹ ቋንቋ “ምቀኝነት ነው እንዴ!” ሊያስብል ይችላል፡፡ እንደ እውነቱም ምቅኝነትም አለበት የሚሉ ተንታኞችም አሉ፡፡) የእነ ሳውዲ ዋናዋ ኢላማ ኢራን ነች የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ በአካባቢው የኃያልነቱን መንበር ለመያዝ ፉክክሩ በዋነኛነት በሁለቱ መሀል ነው፡፡ የኢራን ተጽእኖ በአካባቢው እያደገ መሄድ ለሳውዲ ንጉሣውያን ምቾት አልሰጣቸውም፡፡

የሳውዲና የኳታር እሰጥ አገባ የዳዊትና የጎሊያድ ነገር እንዳይመስል ኳታር በወንጭፍ ሳውዲን ግንባሯን ብላ የምትጥልበት አጽመ ታሪክ ለልብወለድም አይመችም፡፡ የኳታር ጦር እኮ ጥቂት አስር ሺዎች ቢሆን ነው፡፡ የሳውዲ ደግሞ ወደ ሩብ ሚለዮን ይጠጋል፡፡

ሳውዲዎቹ ወደ ስምንት መቶ የሚጠጉ የጦር አውሮፕላኖች ሲኖሯቸው የኳታር መቶ አካባቢ ናቸው፡፡ ለነገሩ እንጂ በሁለቱ በኩል ወታደራዊ ንጽጽር ማድረጉ የማይታሰብ ነው፡፡

ኳታር ዓይን የገባችው ‘ዓረብ ስፕሪንግ’ በሚባለው የአረብ አገራት አመጽ ኳታር አማጺዎችን በግልጽ ስትደግፍ፡፡ በተለይ በምዕራባውያኑ አካባቢ ያኔ ነው “ይቺ ምን የሚሏት አገር ነች!” የተባለው፡፡ ኳታር የምትባል፣ ቅልጥ ያለች ሀብታም አገር፡፡

የሳውዲና ኳታር ጠብ ከ1995 የጀመረ ነው ይባላል— ኳታር ውስጥ መንግሥት የተገለበጠበት፣ ከትልቁ ከምችቷ የመጀመሪያውን የተፈጥሮ ጋዝ ምርት የጫነችበት ዓመት፡፡ ኤሚር ሀማድ ቢን ከሊፋ አል-ታኒ በሰላማዊ መፈንቅለ መንግሥት አባታቸውን ገለበጡ፡፡

ከስልጣን ተባራሪው ኤሚር የሳውዲ አረቢያ ወዳጅ ነበሩ፣ ልጃቸው ግን ዳዋ አለበሱት እንጂ፡፡ ኳታር የራሷን መንገድ ትከተላለች አሉ፡፡ ሳውዲ ጥርስ ነከሰች፡፡ የኳታር ጎረቤችም አጉረመረሙ፡፡ አዲሱ ኤሚር በ1996 ግልበጣ ተሞክሮባቸው ከሽፏል፡፡ ግልበጣውንም ባህሬን አደራጀችው ሳውዲ ‘ሀይ፣ ሀይ’ አለችው ተብሎ ነበር፡፡

በ2013 ስልጣናቸውን የ33 ወጣት ለሆኑት ልጃቸው አስረከቧቸው፡፡ እሳቸውም ከአባታቸው ፖሊሲዎች ቀኝ ኋላ አልዞሩም፡፡ ‘ሁሉም ጥሩ ይሆን ይሆናል’ ብለው አስበው የነበሩት ጎረቤቶቻቸው ኩም አሉ፡፡ እነ ሳውዲም ተዘባበቱ፣ “ድሮስ የማን ልጅ ሆነና!” አሉ፣ ቂምም አረገዙ፡፡

ኤሚሩ በአገራቸው የገንዘብ ሀይልም በመጠቀም ኳታርን በዓለም መድረክ ቀና፣ ቀና ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ሳውዲ አረቢያና አጋሮቿ ገና ከጠዋቱ የወጣቱን ኤሚር እጅ ለመጠምዘዝ ሞክረው ነበር፡፡ በ2014 “የውጪ ፖሊሲህን ትቀይር እንደሁ ቀይር” ብለው ዲፕሎማቶቻቻውን ከዶሀ አስወጡ፡፡ አልተሳካም፣ ተመልሰው ገቡ፡፡

የአሁኑ አድማ መጀመሪያ አካባቢ ምዕራባውያን ‘አትካረሩ፣ ረጋ በሉ’ ከማለት ውጪ ገፍተው አልሄዱም፡፡ ዶላሩስ! በየአገሮቻቸው ያለው ያ ሁሉ ቢሊዮን የኳታር ኢንቬስትመንትስ! ደግሞ የብሪታንያ፣ የአሜሪካና የፈረንሳይ የሀይል ኩባንያዎች ኳታር ውስጥ በርካታ ቢሊዮኖች ዶላር አፍስሰዋል፡፡

እንዴት ብለው ነው “ለምን የሰፈር ረባሽ ያደርግሻል!” የሚሏት! ለአሜሪካም ቢሆን በታሊባን ተይዞ የነበረ ወታደሯን አስለቅቃላታለች፡፡ አል-ኢዴይድ በተባለ ስፍራም 10‚000 ወታደሮች የከተሙበት የአየር ሀይል ሰፈር እንድትገነባ ፈቅዳላታለች፡፡ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ከዚህ እየተነሱ ነው ኢራቅን የሚያሾቋት፡፡

ስለሆነም ከበቀደሙ የትረምፕ ንግግር በዘለለ አሜሪካ፣ ኳታር ‘ከአሉታዊ ጎኗቿ ይልቅ አዎንታዊ ጎኗቿ ይበልጣሉ’ ባይ ናት፡፡ ጆን ኬሪ በአንድ ወቅት “ማክሰኞ ለሀማስ ገንዘብ የምትልከው ኳታር ሰኞ የአሜሪካ አጋር መሆን አትችልም፣” ያሏት አገር ተወደደም ተጠላም የአሜሪካ አጋር ሆና ትታሰባለች፡፡

የዓለም ፖለቲካ እንዲሁ ነው፡፡ የሀገራት ዋናው ጥያቄ “ምን ብናደርግ ነው ለእኛ ህዝብ ፍላጎቶች የሚጠቅመው!” የሚል ነው፡፡ ኳታርን በተመለከተ ምዕራባውያኑ፣ የእነሱን አባባል ለመጠቀም፣ ‘የሚረግጡትን ድንጋይ እየመረጡ’ የሚራመዱት፣ ‘ሳሩን አይቶ ገደሉን እንዳላየው’ በሬ ላለመሆን፡፡

ኳታር ቢነስርም፣ ቢከስርም በዓለም ገበያም ገንዘቧን እንደ ዝክር ንፍሮ ነው የምትበትነው፡፡ በየሀገራቱ ያላት ሀብት ከ330 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የኳታር አየር መንገድ እንኳን ሰማንያ ኤርባስ ኤ350 አውሮፕላኖች ለመግዛት አንድ፣ ሁለት ብሎ ቆጥሮ 16 ቢሊዮን ዶላር ከፍሏል ይባላለታል፡፡

ያለው ማማሩ ማለት እንዲህ አይደል! አበድሩኝ የለ…‘ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ’ የለ…“የአይ.ኤም.ኤፍን ልብ ያራራልን” የለ…አውጥቶ ሆጭ ማድረግ! ለ2022 ዓለም ዋንጫ እንኳን አንዳንዶቹ እስክ 80‚000 ሰው መያዝ የሚችሉ ዘጠኝ እጅግ ዘመናዊ ስቴዲየሞች መገንባት ጀምራለች፡፡

የሰሞኑ ጫና ኢራንን ይጠቅማል ይባላል፡፡ ከምግብ ፍላጎቷ 40% የሚገባበት የሳውዲ ድንበር ሲከረቸም ክፍተቱን ኢራንና ቱርክ ይሞሉታል፡፡ ይኸው የተለያዩ የምግብ ግብአቶች እየላኩላት ነው፡፡

የዓለም ፖለቲካ እንዲህ ነው — የአንዱ እርግማን ለሌላው ጽድቅ፡፡ እስራኤልም በደስታ ‘እሼሼ ገዳሜ’ እያለች ነው ተብሏል፡፡ በእርግጥ ነገሮች አንድ ሺህ ቀይ መስመሮች ቢያልፉም ኳታር መራብ ደረጃ አትደርስም፡፡ ሆኖም እገዳው የሚያስከትለው ህመም ከ‘ቆረጠመኝ፣ ጠዘጠዘኝ’ ንጭንጭ ሊያልፍ ይችላል፡፡

የኳታርና ሳውዲ ቡድን ትንቅንቅ ፊት ለፊት በየዜና እወጃው ከሚነገረው አልፎ የሚሄድ የተወሳሰበ ነው፡፡ እኛም ብንሆን “ያልፍልኛል፣” “ጨልማብኝ የኖረችው ፀሀይ ፏ ትልልኛለች” ብለው እዛ የሄዱ ወገኖቻችን እጣ ፈንታ ያሳስበናል፡፡ ምክንያቱም የኳታራውያን ኑሮ ሞልቶ ከመትረፍ ወደ “ቀበቶ አጥብቁ” ከወረደ የሚሆነው አይታወቅምና፡፡

ደጉን ዘመን ያምጣውና በቅርቡ የጎበኙን የኳታሩ ኤሚር ከዶላሩ ወደ እኛ በተን ብቻ ሳይሆን ዘርገፍ እንዲያደርጉት ልቦናውን ይስጣቸውማ! ሚጢጢዬዋ አገርም “ገንዘቤን ይጭነቀው” የምትልበትን ጊዜ ይመልስላት፡፡

LEAVE A REPLY