የአርብ እለት የፍርድ ቤት ውሎዎች /እነ መቶ አለቃ ጌታቸው፣ እነ ጉርሜሳ አያናና...

የአርብ እለት የፍርድ ቤት ውሎዎች /እነ መቶ አለቃ ጌታቸው፣ እነ ጉርሜሳ አያናና አቶ ዳንኤል ሽበሽ/

/ETHIOPIA Nege News/:- በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን መዝገብ የጥፋተኝነት ብይን የተላለፋባቸው ውሳኔ ተሰጠበት

የእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መዝገብ 16 ሰዎችን ያካተተ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት 9ኙን በነፃ አሰናብቶ፤ 6ቱን ጥፋተኛ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የእስራት ቅጣት አስተላልፏል።

በዚህ መሰረት፦

2ኛ ተከሳሽ በላይነህ ሲሳይ 4 ዓመት ከ 6 ወር

3ኛ ተከሳሽ አለባቸው ማሞ 4 ዓመት ከ 2 ወር

9ኛ ተከሳሽ ቢሆነኝ አለነ 4 ዓመት ከ6 ወር

11ኛ ተከሳሽ ፈረጀ ሙሉ 4 ዓመት ከ 2 ወር

12ኛ ተከሳሽ አትርሳው አስቻለው 4 ዓመት ከ 6 ወር

14ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኝ 4 ዓመት ከ6 ወር እንዲሁም

16ኛ ተከሳሽ አባይ ዘውዱ 4 ዓመት ከ2 ወር ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ህወሓት/ ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም በነበረው ቅድመ -ምርጫ ወቅት በተለይም በአማራ ክልል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርና አባላትን በእስር የማፅዳት ዘመቻ በማካሄድ በርካታ ወጣቶችን ከጎንደር፣ጎጃምና ወሎ አካባቢዎች ለእስር መዳረጋቸውና በእስር ቤትም ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ተግባር እንደተፈፀመባቸው እራሳቸው ታሳሪዎቹና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ሲገልፁ መቆየታቸውን እናስታውሳለን።

እነ ጉርሜሳ አያና

የእነ ጉርሜሳ አያናን መዝገብ ብይን ለማሰማት ፍ/ቤት ለዛሬ የመጨረሻ በማለት የተቀጠረ ቢሆንም ተከሳሾች ፍ/ቤት አልቀረቡም

የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ተሰምቶ ካበቃ በኋላ መዝገቡ ለብይን ሲቀጠር ከ3 ወራት በላይ ሆኖታል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ ላይ ሰኔ 9/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ለዛሬ ሰኔ 16/2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጥ የመጨረሻ ያለ ቢሆንም ተከሳሾች ሳይቀርቡ ለሐምሌ 6/2009 ብይን ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰቷል።

ከ22 ተከሳሾች መካከል የ19ኙ ብይን ተሰርቶ እንዳለቀና የ3ቱ ደግሞ እንዳልጨረሰ በሰኔ 9/2009 በዋለው ችሎት ዳኞች መናገራቸው የሚታወስ ነው።

አቶ ዳንኤል ሽበሽ

ዳንኤል ሺበሺ መከላከያ ምስክር ዛሬ አሰማ

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ ተከሶ በእስር ቤት ሆኖ ጉዳዩ በፍ/ቤት እየታየ ያለው የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የአመራር አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ “በእነ ዘላለም ወርቃገኘው መዝገብ” ነፃ ከተባለ በኋላ የፌዴራል አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆበት ተቀባይነት በማግኘቱ ተከላከል መባሉ ይታወቃል።

አቶ ዳንኤል የቀድሞውን የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉንና የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር አቶ የሽዋስ አሰፋን በመከላከያ ምስክርነት ዛሬ አሰምቷል። ብይን ለመስጠትም ለሐምሌ 11/2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የአረና ፓርቲ ሊ/መንበር አቶ አብርሀ ደስታ ለ3ኛ ጊዜ ዛሬም ያልቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱም በፖሊስ ተይዞ እንዲቀርብ በድጋሜ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY