የአልጄዚራ ነገር – This is Aljazeera /ከኤፍሬም እንዳለ/

የአልጄዚራ ነገር – This is Aljazeera /ከኤፍሬም እንዳለ/

“ዚስ ኢዝ አል ጀዚራ፡፡” ነጎድጓዳማ ድምጽ፡፡

ሚያዝያ 1979 — የአሥራ ስድስት ዓመቱ ፍልስጤማዊ ሳሚር ኩንታር ሰሜናዊ እስራኤል ናሃሪያ ከተማ ከጓደኞቹ ጋር ገብቶ አንድ እስራኤላዊ ፖሊስ ይገድላሉ፡፡

አንድ መኖሪያ ቤት ግበተውም ኩንታር፣ የ31 ዓመቱን እስራኤላዊ ዳኒ ሀራንና የ4 ዓመት ዕድሜ ያላት ልጁን ኤይናትን ያግታቸዋል፣ ወደ ሌባኖስ ለመውሰድ ወደ ባህር ዳርቻው ከእስራኤል ወታደሮች ጋር ተኩስ ይከፈታል፡፡ ይሄኔ ነው ኩንታር ሀራንን ልጁ ፊት የገደለው፣ ህጻኗንም ጭንቅላቷን ከአለት ጋር አጋጭቶና በሰደፉ ደጋግሞ በመምታት ገደላት፡፡ ተይዞ ዕድሜ ልክ ተፈረደበት፡፡

ቅንጣት ታክል ጸጸት አለሳየም ነው የተባለው፡፡ ይባስ ብሎ “አባትዬውን ህጻኗን ይዘህ አትምጣ ብዬው ነበር” ብሏል፡፡ በ2008 በእስራኤለና በሄዝቡላ መካከል በተደረገ የእስረኞች ልውውጥ ተለቀቀ፡፡

ይሄኔ ነው አል ጀዚራ በቀላሉ ሊለቅ ያልቻለ ጥላሸት የተመረገበት፡፡ የጣቢያው አረብኛ ክፍል የቤይሩት ቢሮ ለኩንታር፣ የአባትና ትንሽዬ ልጁን ህይወት በጭካኔ ላጠፋው ለሳሚር ኩንታር የ‘እንኳን ደህና መጣህ’ ድግስ አዘጋጀለት፡፡

“ወንድም ሳሚር፣” አለ የጣቢያው ሀላፊ፣ “ከዚህ በላይም ይገባሃል፡፡” ምዕራባውያንም “ይኸው፣ እኛ ምን ብለን ነበር፣” አሉ፡፡ “አል ጀዚራ የአሸባሪዎች አፈቀላጤና ደጋፊ ነው ብለን አልነበር!”

አል ጀዚራ ህዳር 1፣ 1996 ከኳትሩ ኤሚር በተገኘ 140 ሚሊዮን ዶላር ከተመሰረተ ጀምሮ ነገር አላጣውም… የስለት ልጅ አንደሚሉት አይነት፡፡ ሰሞኑን ሳውዲና አጋሮቿ “ኳታር አል ጀዚራን ካልከረቸመችልን ከእነረብጣዋ እንጦረጦስ ትውረድ!” አይነት ነገር ማለታቸው ድንገተኛ የምርቃና ውሳኔ አልነበረም፡፡ ጣቢያው ላይ ጥርስ ከነከሱ ሁለት አስርት ዓመታቸው፡፡

አል ጀዚራ በምዕራባውያን የቴሌቪዥን ተመልካቾች ዓይን ውስጥ የገባው ከመስከረም 2001 ጥቃት ማግስት ጥቅምት 7፣ 2001 በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ሀይል አፍጋኒስታንን ማሾቅ ጀመረ፡፡ ቦምቦቹ መዝነብ ከጀመሩ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ኦሳማ ቢን ላደን በአል ጀዚራ ብቅ አለ፣ ፎከረም፡፡ “የመካከለኛው ምስራቅ ችግር እስካልተፈታና በአካባቢው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እስካልተዘጉ ድረስ አሜሪካ ሰላም አታገኝም፡፡” አሜሪካ ጦፈች፡፡

አንዳንዶች “ከዘገቡ አይቀር እንደ አል ጀዚራ!” አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “ለዚህ ጨፍጫፊ እንዴት መድረክ ይሰጣሉ! አሸባሪ፣ የአሸባሪ አፈ ቀላጤዎች!” አሉ፡፡ ቡራኬውም፣ እርግማኑም ተዥጎደጎደ፡፡ አል ጀዚራዎች ግን “ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም” አላሉም፡፡ “ለአሁኑ ማሩን፣ አይለምደንም፣” ብለው አልተንበረከኩም፡፡

ህዳር 3፣ 2001 ቢን ላደን ወታደራዊ ልብሱን ግጥም አድርጎና ኤኬ 47 ጠብመንጃ አንግቦ እንደገና በስክሪን ብቅ አደረጉት፡፡

ምናልባትም በስህተት፣ ምናልባትም በእቅድ ከአሥር ቀናት በኋላ አሜሪካ በካቡል የአል ጀዚራን ቢሮ በሚሳይል ይቀመስልህ አለችው፡፡ ምነው! እንዴት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊቀ ጳጳስ የሚሏት አገር የሚዲያ ተቋም በሚሳይል ትመታለች! “ይቅርታ በስህተት ነው፣” ተባለ፡፡ አል ጀዚራዎች “አብራሪዎች ስፍራውን ያውቁታል፣ ሆነ ተብሎ የተሰነዘረ ጥቃት ነው” አሉ፡፡

‘ከባልንጀሮቿ ከፍ ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ፣ አንድም ለወንጭፍ’ ይላል የአገሬ ሰው፡፡ የአረቡ ዓለም ሚዲያዎች በአፍጢማቸው የተደፉት አል ጀዚራ አየር ላይ ሲወጣ ነው ይባላል፡፡ ታላላቆቹ የዓለም ሚዲያዎችም ከባድ ተወዳዳሪ የመጠባቸው ‘አልጀዚራ ኢንግሊሽ’ ብቅ ሲል ነው፡፡ ጥርስ ቢነከስበትም አይገርምም፡፡ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሳይቀሩ የአል ጀዚራን አፍ ለማዘጋት ሞክረዋል፡፡

ለምን? የራሳቸው ሚዲያዎች እንደ ልብ እየሆኑ አል ጀዚራን ምን አዩበት! “ምክንያቱማ” ብለው ነበር የአሜሪካ ባለስልጣናት፣ “ምክንያቱማ በኢራቅ ውጊያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ላይ ብቻ በማተኮር የህዝብ ስሜት ያነሳሳል፡፡”

እናስ! እውነቱን ማፍረጥረጥ የጋዜጠኝነት ዓቢይ መመሪያ አይደለም እንዴ! እሱማ ነው፣ ዘመኑ ‘እውነት እንደተርጓሚዋ ነች’ የሚባልበት ዘመን ሆነ እንጂ፡፡ ‘ከጥሬ እውነት ብሔራዊ ጥቅም ይቀድማል፣ አራት ነጥብ‘ ነው ነገሩ፡፡

የእነ ሳውዲ የይዘጋልን ቅድመ ሁኔታ ሁሉም ኢሮ አላሉለትም፡፡ ኒው ዮርክ ታይምስ እንኳን “የኳታር ተቺዎች የሱኒ እስላማዊ ሽብርተኝነትንና የኢራንን ፍላጎት ታስፋፋለች ብለው ይወነጅሏታል፡፡

ሆኖም እስላማዊ ጽንፈኝነትን በማስፋፋትና የሽብርተኛ ቡድኖችን በመደገፍ ሳውዲ አረቢያ ከደሙ ንጹህ አይደለችም፣” ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ከሰሞኑ ንትርክ ቀደም ብሎ ሳውዲ አረቢያ ሆቴሎቿን “የአል ጀዚራን ጣቢያ ታሳዩና እናንተን አያድረገኝ!” ብላቸው ነበር፡፡

ሚያዝያ 1፣ 2003 አንድ የአሜሪካ አውሮፕላን እንደገና በባግዳድ የአልጀዚራን ቢሮ ደበደበ፡፡ ታሪክ አዩብ የተባለ ጋዜጠኛ ህይወትም አለፈ፡፡ “በስህተት ነው” ነበር አሜሪካ ማብራሪያ፡፡ ስህተት! የምን ስህተት? ኳታሮች “ቢሮው ያለበትን ትክክለኛ ካርታ ለአሜሪካ ቀድመን ሰጥተናት የምን ስህተት ብሎ ነገር ነው!” አሉ፡፡

በነገራችን ላይ፣ አሜሪካኖቹ አል ጀዚራን አንደኛውን የአቧራ ክምር ሊያደርጉት ሁሉ አስበው ነበር ተብሏል፡፡ ‘ዴይሊ ሚረር’ ሁነኛ የእንግሊዝ ባለስልጣናት ሹክ አሉኝ በሚል፣ “ጆርጅ ቡሽ የአል ጀዚራን ዋና መሥሪያ በቤት በቦምብ ዶጋአመድ ለማድረግ አስበው ነበር፣” የሚል ዜና አውጥቶ ጕድ ተብሎ ነበር፡፡

አል ጀዚራ በቦምብ ተመታም አልተመታ፣ የሽብርተኞች ደጋፊ መሆኑ በዘገባዎቹ ፍንትው ብሎ ይታያል ይሉታል፣ ተቺዎቹ፡፡ ‘ሁለተኛው ኢንቲፋዳ’ በሚባለው የፍልስጤሞች አመጽ ወቅት ጣቢያው በእስራኤሎች የተገደሉትን ፍልስጤማውያን ‘ሰማእታት’ ብሎ ሲያሞጋግሳቸው በፍልስጤሞች የተገደሉ እስራኤላውያንን ግን ከሰውም አልቆጠራቸውም ሲሉም ይከሱታል፡፡

የአል ጀዚራ መንገድ እንደሌሎቹ ታላላቅ የሚዲያ አውታሮቸ አልጋ በአልጋ አልሆነም፡፡ በእነዚሀ ሁሉ መከራዎች ውስጥ እያለፈ ጠንክሮ መቀጠሉን የሚያደንቁለት አሉ፡፡ ጣቢያው “ያላደረጉትን ሁሉ ይለጥፉብኛል” ይላል፡፡

ዶልድ ረምስፊልድ የአሜሪካ ወታደሮች ኢራቅ ውስጥ አንገታቸውን ሲቀሉ የሚያሳዩ ምስሎች እየለቀቀ እስላማዊ ወታደራዊ ቡድኖችን እያበረታታ ነው ሲሉ ከሰሱ፡፡ አል ጀዚራዎች ሲያልፍም አይነካን ብለዋል፡፡ በነገራችን ላይ አል ጀዚራ መቼም ቢሆን የሰው አንገት ሲቀላ የሚያሳዩ ምስሎች ለቆ አያውቅም ነው የሚባለው፡፡

አማካይ ደሞዛቸው በወር አስር ሺህ ዶላር ገደማ ከሆነውና የቤት ኪራይ፣ የህክምናና የሞባይል ወጪ ከሚሸፈንላቸው ከራሱ ሠራተኞቹም ተቃውሞ እየቀረበበት ብዙዎቹ “ይስፋችሁ” እያሉ ትተውት ሄደዋል፡፡ (የሆነስ ሆነና የእኛዎቹ አሮጌዎቹም፣ አዲሶቹም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሠራተኞች አማካይ ደሞዝ ስንት ነው? ይሄ ሁሉ ማስታወቂያ ትንፋሽ እያሳጠረንማ “ቀበቶህን አጥብቅ” ምናምን ብሎ ነገር አይሠራም፡፡)

እናም፣ በ2012 ጣቢያውን የለቀቀው የበርሊኑ ዘጋቢ አክትሃም ሱሊማን “የአረቡ ዓለም አመጽ (አረብ ስፕሪንግ) ከመጀመሩ በፊት የለውጥ ድምጾች ነበርን፣ …አሁን ግን አል ጀዚራ ፕሮፓጋንዳ አሰራጭ ሆኗል፡፡ በሚዘግብባቸው አገሮች በጋዜጠኝነት መርሆች ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በኳታር መንግሥት ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ፍላጎት ላይ የተሰመረተ ግልጽ አቋም ይይዛል፣” ብሎ ነበር፡፡

መጋቢት 2012 ሁለት ጋዜጠኞች የጣቢያውን የሶሪያ ጦርነት አዘጋገብ በመቃወም ሥራ ለቀቁ፡፡ “ስልኮችና የሳተላይት መገናኛዎች ለሶሪያ አማጽያን በድብቅ እንዲገቡ አል ጀዚራ ሀምሳ ሺህ ዶላር” ከፍሏል አሉ፡፡ በተጨማሪ ጋዜጠኞቹ ለሞቱ የሶሪያ ተቃዋሚዎች ‘ሰማእት’ የሚለውን ቃል እንዲጠቀሙና ለመንግሥት ሀይሎች ግን ያንን እንዳይጠቀሙ ጫና አሳድሮባቸዋል ተብሏል፡፡

በለንደን፣ ፓሪስ፣ ሞስኮ፣ ቤይሩት እና ካይሮ ዘጋቢዎቸና ዜና አንባቢዎች የጣቢያው ፖሊሲ አልተስማማንም በሚል ሥራቸውን ለቀዋል፡፡ ሐምሌ 2013 የሙስሊም ወንድማማቾችን የሚደግፉ ወገንተኛ ዘገባዎችን ያስተላልፋል ያሉ 22 ሠራተኞች በአንድ ጊዜ ‘ሆ’ ብለው ከካይሮው ቢሮው ወጥተዋል፣ ሌሎችም እንዲሁ፡፡

ብዙ ሀገራት በየጊዜው እገዳዎች ጥለውበታል፡፡ እስራኤል በተደጋጋሚ ማእቀቦች ጥላበታለች፡፡

በያስር አራፋት ሞት የመሀሙድ አባስ እጅ አለበት የሚል ዘገባ አሰተላላፏል በሚል ሐምሌ 2009 የፍልስጤም ብሔራዊ ሸንጎ የዌስት ባንክ ቢሮውን ዘግቶበት ነበር፡፡ ጥር 27፣ 1999 የአልጄሪያ ተቃዋሚዎች የአልጄሪያ ጦር ጅምላ ጭፍጨፋ አካሂዷል ብለው በአል ጀዚራ መግለጫ እየሰጡ ሳለ በበርካታ የአልጄሪያ ከተሞች መብራት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

ባሀሬን እንኳን ጣቢያው የእስራኤል ደጋፊ ነው በሚል ግንቦት በ2002 አግዳው ነበር፡፡ ኢራቅ ውስጥ በተደጋጋሚ ታግዷል፣ የዘጋቢዎቹ የጋዜጠኝነት ፈቃድ ተሰርዟል፡፡

በኩዌይትም ፖሊሶች ሰልፈኞችን ሲደበድቡ በማሳየቱና የተቃዋሚዎችን ቃለ መጠይቅ በማስተላለፉ ታግዶ ነበር፡፡ በስፔን ዘጋቢው ታይሰር አሉኒ የተባለው ዘጋቢው ከአልቃይዳ ሰዎች ጋር ተገናኝተሀል በሚል ሸቤ ይገባል፡፡ አል ጀዚራዎች ለምን የልጅና የእንጀራ ልጅ ታደርጉታላችሁ ነገር አሉ፡፡

“በርካታ ጊዜያት ምዕራባውያን ጋዜጠኞች ከህቡእ ድርጀቶች ጋር በምስጢር ተገናኝተዋል፡፡ ሥራቸውን እየሠሩ ስለሆነም ምንም አይነት ህጋዊ እርምጃ አልተወሰደባቸውም፡፡ ለምንድነው አሉኒ ከዚህ ውጪ የሆነው?” ሲሉም ለስፔይኑ ጠቅላይ ሚነስትር ጻፉላቸው፡፡

በተለይ ግብጽ ለአል ጀዚራ ጋዜጠኞች ምቹ አልነበረችም፡፡ ታህሳስ 2013 ጋዜጠኞቹን ፒተር ግሬስቴ፣ መሀመድ ፋህሚና ባህር መሀመድን ይዛ ችሎት ገተረቻቸው፡፡ የ7 እና የ10 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው — ሀሰተኛ ወሬ በማሰራጨትና ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋር በማበር በሚል፡፡ መስከረም 23፣ 2015 ምረናችኋል ተባሉ፡፡ ከዛም በኋላ ሌሎች ጋዜጠኞችን አስራባቸዋለች፡፡

በእርግጥም ምዕራባውያን ሚዲያዎች ሲሠሯቸው ‘የምርመራ ጋዜጠኝነት’ እየተባሉ የሚወደሱ ዜናዎች አል ጀዚራ ሲሠራቸው ለምን ሌላ ትርጉም ይሰጣቸዋል የሚል መከራከሪያም ይነሳል፡፡

አረረም፣ መረረም እንደሚባለው አል ጀዚራ ምን ያህል አከራካሪ፣ ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‘ኮንትሮቨርሻል’ ጣቢያ ቢሆንም የፈረጠመ ጡንቻ እንዳለው አስመስክሯል፡፡

ይህ ጡንቻ ሊጠነክርም በጫና ብዛት ሊልምም ይችላል፡፡ ሊያኮሰምኑት የሚፈልጉት ምን ያሀል ይሳካላቸዋል የሚለው ከርሞ የሚታይ ነው፡፡

አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው፡ በሆነ ምክንያት አል ጀዚራ ከአየር ቢወርድ የተመልካች ድርቅ የመታቸው የአረቡ ዓለም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስርየት ይሆንላቸዋል፡፡ ሳውዲና አጋሮቿም ‘እሰይ ስለቴ ሰመረ’ን ይዘምሩ ይሆናል፡፡ የዓለም ህዝብ ግን የዓበይት ዜናዎችን — በተለይ ደግሞ መካከለኛ ምሰራቅን የተመለከቱ — ሌላኛ ወገን ዘገባና ትንታኔ አጣ ማለት ይሆናል፡፡ የሚፈጠረው ክፍተትም በቀላሉ የሚሞላ አይሆንም፡፡

በነገራችን ላይ አል ጀዚራዎች ከእኛ ጋር የሆነ የትብብር ስምምነት ፈርመዋል ተብሎ አልነበረም እንዴ! ምን ደረሰ? ብቻ ገደ ቢሶች እንዳይሉን፡፡ መቼም “ኤሚራችን እዛ ሄደው ሲመለሱ ኳታር ላይ አድማ ተመታ፣ እኛ ደግሞ ከእነሱ ጋር የጋራ ስምምነት ስንፈራረም “ይዘጋልን” ተባልን” አይሉንም፡፡ አይደል እንዴ!

‘ዚስ ኢዝ አል ጀዚራ’ የሚለው አጉረምራሚ ድምጽ ምን ያሀል ከእነ ግርማ ሞገሱ ይቆይ ይሆን!

LEAVE A REPLY