ጦርና የጦር መሣሪያ በሦስቱ ክልሎች! ትግራይ፣ ኦሮምያና ዐማራ /ዘመድኩን በቀለ/

ጦርና የጦር መሣሪያ በሦስቱ ክልሎች! ትግራይ፣ ኦሮምያና ዐማራ /ዘመድኩን በቀለ/

መጋቢት 12፣ 2008 ዓም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የጦር መሣሪያ አያያዝን በተመለከተ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታት የሚያስችል ህግ ሊወጣ ነው የሚል ዜና መሥራቱ ይታወሳል። በዕለቱ የተሰማው ዜና እንደሚያትተው ከሆነ በአገሪቱ በተከናወኑ የሠላምና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር መድረክ በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሻሸመኔ ከተማ እንደተካሄደ እና በምክክር መድረኩ ላይም ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደር እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እንደተገኙና የዜና ምንጩ ያትታል።

በምክክር መድረኩ ላይ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በአገሪቱ ጸጥታ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ በሰፊው መዳሰሱን፣ የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የኦሮሚያና የጋምቤላ ክልሎች ጸጥታ ኃላፊዎች በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚፈጠሩ ግጭቶች የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ችግሩን እያባባሰ በመሆኑ መፍትሔ ሊዘጋጅለት ይገባል ማለታቸውም ተጠቅሶ እንደነበርም ተነገሯል።

በዚያ የውይይት መድረኩም ላይ የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚንስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን መገኘታቸውንና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያን መቆጣጣር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ከማዘጋጀት ባለፈም ሕብረተሰቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለው መናገራቸውንም ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በወቅቱ ዘግቦትም ነበር።

እንግዲህ ከዚህ ዘገባ በኋላ! የጦር መሣሪያን በተመለከተ በሀገራችን ክልሎች ውስጥ በምን አይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚል ጥያቄ መጠየቅ እንዲሁ አማረኝና፤ አምሮኝ ለምን ይቀራል ብዬ በማሰብ በሀገር ቤት የሚገኙ ወዳጆቼን ለምን ጠይቄ ምላሽ አላገኝም በማለት ወደ ሸገር ከፍ ወዳለ ሥፍራ ወደሚገኙ ወዳጆቼ ዘንድ በመደወል እንዲህ የሚል ምላሽ አገኘሁ።

ክልል ፩ ፦ ትግራይ!

በትግራይ ክልል ከመንግሥት ግምጃ ቤት በወጣ የጦር መሣሪያ ፤ ህጻን አዋቂው ሁሉ በነፍስ ወከፍ እስከ አፍንጫው ድረስ እየታጠቀ ነው አሉ። አሉ ነው እንግዲህ። በእኔ በኩል ትግራይ ለምን የጦር መሣሪያ ታጠቀ አልልም። ምክንያቱም ከሰሜን በኩል” ከአጎታቸው ልጆች” ጋር በጥቂቱም ቢሆኑ ጠብ ላይ ያሉ ስለሚመስሉ፤ ለክፉም ለደጉም መሣሪያ ቢታጠቁ ለምን ታጠቁ አይባሉም። ይታጠቁ። በደንብም ይታጠቁ። ጥያቄ የሚመጣው ከዚህ በታች ሌሎች ወገኖች የሚያነሱት ጥያቄ ሲነሳ ነው። ያንጊዜ አረ.! እንዲህ ነው እንዴ ጨዋታው.! የሚል ጥያቄ መነሳት ይጀምራል።

ክልል ፬ ፦ ኦሮምያ!

በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት ከኦሮሞ ብሔር የተውጣጡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ወጣቶች በክልሉ ውስጥ በከባድ ሁኔታ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው። በዚህ መጠን፣ እንዲህ በጀት ተመድቦለትና ትኩረት ተሰጥቶት የክልሉ ተወላጆችን ብቻ ያሳተፈና ሚስጥራዊ የሆነ ወታደራዊ ስልጠና በዚህ መልኩ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜም ነው ይላሉ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተልነው ነው የሚሉ ወገኖች። ሰልጣኞቹ ወታደሮች ከሥልጠናው በኋላ ወደ የትኛው የጦር ግንባር እንደሚዘምቱ ባይታወቅም፤ ነገር ግን ወደ ሆነ ቦታ መዝመታቸው አይቀርም የሚሉ ወገኖች የትየለሌ ናቸው። ብቻ የሚዘምቱበትን ቦታ መድኃኔዓለም እና ያሰለጠናቸው አካል ብቻ ናቸው የሚያውቁት የሚሉም ተቺዎች አልጠፉም። የትግራይን መታጠቅ፣ የኦሮሞዎቹን በገፍ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድና እስከ አፍንጫቸው ድረስ መታጠቅ አይተው ወደ ሌሎቹ ክልሎች መለስ ብለው ሲያዩ ያ ከላይ የተነሳው የዜጎች መጠራጠር ይበልጥ ዝሆን አክሎ እውነታው ፍጥጥ ብሎ ይታያል።

ክልል ፫ ፦ ዐማራ

በክልሉ በመንግሥት ላይ አኩርፈው ጫካ የገቡ እንደለ ይነገራል። የክልሉ ገበሬዎች ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ረጅም ድንበር ላይም እስከ አፍንጫው ከታጠቀ የሱዳን መከላከያ ጋር በነፍስወከፍ ጠመንጃ እየተዋጉ እንደሆነም ይነገራል። ይኽ ማለት ከውጭ ወራሪ ጦር ጋር እየተዋጉ ነው ማለት ነው። ገበሬዎቹን የኢትዮጵያ መንግሥት መከላከያ ሠራዊት እንኳን ሊረዳቸው፤ አንዳንድ ጊዜ ከሱዳኖቹ ጋር በማበር የገዛ ወገኖቹን እንደሚወጋ የሚናገሩም አሉ። እናም ያ ክልል ትንሽ ፈተና የበዛበት ይመስላል። በትምህርት ወደ ኋላ እንዲቀር እየተደረገ ነው የሚለውን መረጃ መንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሳይቀር በከባዱ ዘግቦታል። ጣናን የሚያህል የሀገር አድባር የሆነ ሀይቅ እነደዲደርቅ እየተደረገ ነው የሚሉ ተቃዎሞዎች እየተሰሙ ነው ። ህክምና ዜሮ ሆኗል። ወንዶች የዘር ፍሬያቸው እንዲመክን፣፤ ሴቶችም እንዳይወልዱ እየተደረገ ነው ብለው የደለበ መረጃ ይዘው የሚጮሁ የክልሉ ተወላጆች አያሌ ናቸው። በቤትና ህዝብ ቆጠራም በሚልየን የሚቆጠር ህዝብ የት እንደገባ አልታወቀም ተብሎ በፓርላማ ጭምር መነገሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። እናም ብቻ ደስ አይልም። ከምር ደስ አይልም።

እኔማ፣ እኔ ዘመዴ ትግራይ ከመንግሥት ግምጃ ቤት በነጻና በብላሽ የተገኘ የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫዋ ታጥቃ በየሁ ጊዜ.! ኦሮሚያም እንዲሁ ከመንግሥት ግምጃ ቤት የወጣ የጦር መሣሪያ ታጥቆ ባየሁ ጊዜ.!፣ ሶማሊ፣ አፋር ቤኒሻንጉልም እንዲሁ እስከ አፍንጫቸው ድረስ ከመንግሥት ግምጃቤት የወጣ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ባየሁ ጊዜ ዐማራስ ብዬ መጠየቄ እንደሁ አልቀረም።

ዐማራማ አለኝ የጥያቄዬ መላሽ! ዐማራማ ተፈርዶበታል። በገዛ ገንዘቡ ገዝቶ የታጠቀውን መሣሪያ እንኳ፤ በአስቸኳይ ፍታ ተብሎ ዐዋጅ ወጥቶበታል። አይደለም የጦር መሣሪያ ሊኖረውና በእጁ ሽመልና ምርኩዝ፣ ከዘራና በትር እንኳ ይዞ ቢገኝ ክላሽ እንደያዘ ተቆጥሮ ከባድ ቅጣት ይጣልበታል። ጭራሽ በእጁ እንዳይነካም ተፈርዶበታል አለኝ። እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜና ነገሩ እውነት ከሆነ፤ በእውነት ደስ አይልም። ወዴትስ እያመራን ነው.? ምንድነው የተደገሰው ድግስ አልኩ ለራሴ.! ሌሎችን እስከ አፍንጫቸው አስታጥቆ አንዱን ለብቻው ነጥሎ እንኳን የጦር መሣሪያ በእጅ ልትይዝ ይቅርና በእጅህ ከዘራ ፣ በቤትህ ማማሰያ እንዳይኖር ዋ.! ተጠንቀቅ ማለቱ ፌር ነው ወይ ብዬ ልጠይቅ ፈለግኩና፤ መልሼ ለራሴ ይሄ ደግሞ ምን ተብሎ ይጠየቃል፤ እንዴትስ ተብሎ ለሰው ይነገራል.? በማለት ” ጮጋ” ብዬ ቁጭ ብያለሁ።

1 COMMENT

 1. በዕውነት ሒሱ ይቅርና፣አስተያየትስ ትቀበላላችሁ ከሆነም፤ልበለው።

  ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግሥት በስተቀር የጦር መሣሪያ ዜጋ በጅምላ ፍቅድ የለውም ነው፤ አገር የሚያውቀው። ክልል፣ፌዴራል ብሎ ነገር የለም፣ሁሉም የመንግሥት ድርጅት ካልሆነ በስተቀር ሕጉ አይፈቅድም።ትንሽ ትንሽ እየተንፏቀቁ በሕግ እና በንብረት እያማካኙ የሚታጠቁት ሰበበኞች ግን:- ከነፍስ ወከፍ ዜጎች በልጠው ከሆኑ እስከ አፍጢማቸው ድረስ ይታጠቁ፤እያየን ነውና።ከዓማራው ይልቅ ግን:- ትግሬው የሚታጠቀው፣ ሻቢያ ስለሚያሰጋ ነው፤ የሚልና ኦሮሞው ደግሞ:-ከታጠቀ “የሚችለው” አይኖርም፤ተብሎ ከተሰጋ ከበሽተኛ አሥተሣሰብ ገናም አልተላቀቅንም ማለት ነው።
  ይህ የተጻፈው ጦማር ግን:- ይህን ዕውነታ አይደለም የሚያመላክተው፤ሰበቡ “ስለጦር መሳሪያዎች ማስታጠቅና ማስፈታት ሕዝቡ እያጉረመረመ ነው፣”ስለዚህ ግምትምታውን እንዴት እናለሳልሰው ሲሆን፤ምክንያቱ ግን ነጻነት “ለአናሳዎቹ ብቻ”እንዲጸናና”በበላይነት እንዲቀጥል ምን ይደረግ??” ለማለት ነው።ቅጥር ባለጭምብል የሕዝብ መገናኛ ሚዲያዎች እንዲያጭበረብሩ ማድረግ ነው፤በተለይም የሕዝብ የሚመስሉት አሊያም ሕዝብ ውስጥ ሆነው የማይታወቅባቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች ቢያብጠለጥሉት:- የ”ተንኮል ጊዜ እናካብታለን”ነው።እናም እያካበቱ ነው፤ብልጥነት ሳይሆን በጅል ምሁራን ጭንቅላት እየተጠቀሙ የሚፈልጉትን ክፍያ በደም ለፈረሙ መፈጸም።ይህንኑ እያነበብን ነው፣ሾላካ የተንኮል ጥያቄዎችን ይዘው ሕዝቡን ያሉትን ለማዋረድ ሽልንግ በገጽ የሚከፈላቸውን ጨምሮ፤ልብ ብላችሗል???እንግዲያውስ ልብ በሉ።

  በውርደት እያየነውም፤
  ጉጅሌን አናድነውም።
  ከእኛ ውስጥ ተፈጥሯል ብንልም ያውም፤
  በምንም አክታን አናድነውም።
  ለሃያ አምስት ዓመታት አለዚያም ለአርባ፤
  “ቢደረፍለትም ጓንዴ በሰገባ፤
  “ሕድሪ ሰውዓትና ሎሚ ዝጠለሙ፤
  ሐገርና ዝሸጡ ብደም ዝፈረሙ፤”
  ሁሉም ያገኛሉ እንደ በደላቸው፤
  አያ ጊዜ መጥቶ:-

  ይብላኝ ወዮላቸው!!!
  የሰው አክታም ሆነ ጉጅሌውም ያልፋል ፤
  አያ ጊዜ መጥቶ በሕዝብም ይተፋል።
  ግዴታ ነው አክታ ጉልጉል መተፋቱ፤
  ጉጅሌም አይቀርም በቀን መደፋቱ።

  አክታን ባፋችን ያዝ ብናደርገውም፤
  ሓቅቅቅ ብለን ከመትፋት:-

  ምንም አናድነውም።

  ከላንቃ-ጥግ ቢኩረፈረፍ፣ትፋትን ሆዳችን አምጦ፤
  እየተገመደ ቢዝለገለግ፣ካሳምባ ጥግ ተሸምጥጦ፤
  ትንፋሽ በሽምቅ እየገፋው፤እብጥ ብሎ በጉንጫችን
  ምላስ ለፍላፊው እንዳይተፋው፤ቢከላከል ከንፈራችን፤
  እየገዘፈ በጭብጥ ባዕድነቱን ስንቀምሰው፤
  ስንጠላው ለራሳችን እያጣጣምን ስንልሰው፤
  ወደድነውም፣ጠላነውም፤
  በውርደት እያየነውም፤
  አክታን ብንወደውም
  ጉጅሌን አናድነውም።
  ከንፈራችን ሲያሞጠሙጥ ላንቃ በንዝረት ከጠረገ፤
  የቀረልን ይመስለናል፤ በአፍንጫችን ከተማገ።
  አክታ ግን ከተማገ በትናጋ ታግዞ፤
  አንድም አይቀር ይወጣታል፤

  ተጎልጉሎ ጓዙን ይዞ።

  ባዕድ ሆኖ ሲኩረፈረፍ እስከትናጋችን ሞልቶ፤
  ከሕሊናችን ሲሟገት በራስ ዳኝነት ተጠልቶ፤
  ጥርስ ለማኘክ ቢሆንም-ቅሉ፣ሕሊና ያልወደደውን፤
  ያክታን መኖር ልባችን ለመቼም የማይፈቅደውን፤
  በምላስ እንደታዘለ በትንፋሽ እንኩርፍ ፈልቶ፤
  በጭ-ጮ አሊያም ባዝቶ ሲከፋ ከደም ተጣብቶ፤
  እብጥ እንዳለ ጉንጫችን፤ወደድነውም፣ጠላነውም፤
  ቢከላከልም ከንፈራችን፤
  አክታን አናድነውም።
  አፋችን ደብቆት ቢቆይ:-ጥርሳችን ቢሸፍነውም፤
  ጎልጉለን ከመትፋት በቀር በማጨቅ አናድነውም።
  በኢኮኖሚ ግንባታ በዶላር በብር ቢሸሸግም፤
  በግድብ ተስፋ ለመኖር የሕዝቡን ሥልጣን ቢፈልግም፤
  ዘረኝነትን የሚዋጋ ኢትዮጵያዊነትን የሚያነግስ፤
  ቆየ’ኮ ከተፈጠረ ግብረ-ጉጅሌን የሚያረክስ።
  የጉድፍ የእድፍ መጨረሻቸው፤
  በቃ ነውና መቃብራቸው።
  በውርደት እያየነውም፤
  ጉጅሌን አናድነውም።
  አክታን ባንወደውም
  ጉጅሌን ብንጠላውም:-
  በፍፁም ከመትፋት በቀር፤
  ለያይተን አናድነውም።

LEAVE A REPLY