እምቦጮ – ጣና ሐይቅን የወረረዉ መጤ አረም

እምቦጮ – ጣና ሐይቅን የወረረዉ መጤ አረም

/Ethiopia Nege News/:- በዩጋንዳ ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ እንዲሁም በግብፁ የአስዋን ግድብ የዉኃ ላይ አረም ተከስቶ ሃገራቱን አስጨንቆ ያዉቃል። ካለፉት አምስትና አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በጣና ሐይቅ ላይ የዉኃ አረም መስፋፋት መጀመሩ አሳሳቢ ሆኗል።

ለታላቁ አባይ ወንዝ መተላለፊያነቱ የሚታወቀው ጣና ከ20 በላይ ደሴቶችን እና ገዳማትን በውስጡ ያቀፈ ተፈጥሮዊ ሀይቅ ነው። በኢትዮጵያ አንደኛ ከአፍሪካ ደግሞ በስፋቱ ሶስተኛ መሆኑ ይነገራል።

በጣና ሐይቅ ዙሪያ ከሶስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደሚኖር የሚነገር ሲሆን ለመጓጓዣ፣ መዝናኛ፣ እንዲሁም ለብዙዎች የገቢ ምንጭ መሆኑ ይታወቃል። ካለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ታላቅ ሐይቅ በእምቦጭ አረም ተወሮ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖበታል። በዉስጡ የሚያስተናግዳቸው ብዝሐ-ህይወትም እንዲሁ።

እንዴት ወደ ሀገር እንደገባ የተለያዩ መላ ምቶች የሚቀርቡበት አረም፤ እምቦጭ የሚል መጠሪያ ተሰቶታል።

በብዝሃ ሕይወት ሀብቱ ስብጥር በዩኒስኮ የተመዘገበዉ የጣና ሐይቅ በዉስጡ ከ67 ያላነሱ የዓሣ ዝርያዎች ይርመሰመሱበታል። ከዓሣዎቹ ሌላ በላዩ የሚንፈላሰሱት አዕዋፍ፣ በዉስጡ የሚንቦራጨቁት ጉማሬዎች የሐይቁ ድንቅ ዉበቶች ናቸዉ።

በጣና ሐይቅ ላይ ለመንሳፈፍ የሚረዱት ደንገሎችን ለመሥራት በሐይቁ ዳር የሚበቅሉት ሰንበሌጦች ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ የሐይቁም ማስጌጫዎች ናቸዉ።

አረሙ ያረፈበት ስፍራ ዉኃዉ መድረቅ ጀምሯል፤

ዶክተር ዉብዓለም ታደሰ የኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር እንደሚሉት መጤዉ የዉኃ አረም የጣናን ሐይቅ አብዛኛውን ክፍል መሸፈኑን ተናግረው ከዚህ በፊትም በተለያዩ የሀገሪቱ የዉኃ አካላት ማለትም በአዋሽ ወንዝ እና በዝዋይ ሐይቅን በመሳሰሉት ላይ መታየቱንም ጠቁመዋል። እንደእሳቸዉ አገላለጽም እምቦጭ የተባለዉ የዉኃ አረም ጣና ላይ ጠንቷል። አረሙን ለማጥፋትም ጥረት መጀመሩን ፍንጭ ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የከተማው ነዋሪዎች፣ የአማራ ክልል መንግስትና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች “ጣናን እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ሐይቁን ከመጥፋት ለማዳን ከፍተኛ እርብርብ ላይ ናቸው።

አረሙን ለማጥፋት ከተሳተፉት መካክል

– የጎንደር ዩንቨርሲቲና ባህርዳር ዩኝቨርሲቲ የአረም ማጨጃ ማሽን በጋራ እየሰሩ መሆናቸው ታወቋል።

– ደብረታቦር ዩንቨርሲቲ 1.5 ሚሊዮን ብር ጣናን ለመታደግ ለግሷል ፡፡

– የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ጣና ላይ የተከሰተውን አረም ብቻ የሚከታተል ቡድን አቋቁሟል፡፡

– 24 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትሩ በእንቦጭ አረም ተይዞ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአርሶአደሩ ጥረት 22 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር አካባቢ ተመንጥሮ ሁለት ሽህ ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚቀር ተነግሯል፡፡

LEAVE A REPLY