የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማህበር ሰይፉፋታሁን ላይ ያላቸውን ሮሮ ገለጹ

የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማህበር ሰይፉፋታሁን ላይ ያላቸውን ሮሮ ገለጹ

/Ethiopia Nege News/:- በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ የሚቀርበው ሰይፉ ሾው ፕሮግራም ላይ በግንቦት 13/2009 የተላለፈ ፕሮገራም የሙያ ክብርን ነክቷል በሚል የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማህበር ለኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን የሚከተለውን የቅሬታ ደብዳቤ ጽፏል።

“በቴሌቪዥን ጣቢያችሁ ግንቦት 13 ቀን 2009 ዓ.ም የቀረበውን የሰይፉ ሾው ፕሮግራም አስመልክቶ የቀረብ ቅሬታ

ETHIOPIAN MEDICAL ASSOCIATION·WEDNESDAY, 5 JULY 2017

ለኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን

አዲስ አበባ

ሙያንና ባለሙያን በማንቋሸሽ የሚገኝ እውቅና ርካሽ ነው!

በቴሌቪዥን ጣቢያችሁ ግንቦት 13 ቀን 2009 ዓ.ም በቀረበውን የሰይፉ ሾው ፕሮግራም ላይ አዘጋጅና አቅራቢው አቶ ሰይፉ ፋንታሁን የኢትዮጵያውያን ሀኪሞችን ስም የሚያጎድፍና አገልግሎታቸውንም የሚያናንቅ ንግግሮች ማድረጋቸውን በማስረዳት ጉዳዩ እርማት እንዲወሰድበት በቢሮአችሁ ባደረግነው ስብሰባ ላይ መግባባት ላይ ደርሰን ነበር፡፡ይኸው እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይ የሚቀርበውን ፕሮግራም እንድንከታተል በተነገረን መሰረት ተከታትለነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቡ አሁንም በኢትዮጵያውያን ሐኪሞችና በአገሪቱ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያደረሱትን በደል በቅጡ ያልተረዱት ሆነው ስላገኘናቸው ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል፡፡ በዕለቱ አቶ ሰይፉ ፋንታሁን የተናገሩትንና ሐኪሞችን ያስከፉትን አባባሎች ከዚህ እንደሚከተለው እናስረዳለን፡፡

1. “እኔ ሁሌም የምለው ነገር አለ የኢትዮጵያ ዶክተሮች አቅጣጫ ለምን እንደሚጦቅሙ ብቻ ነው፡፡የሆነ ነገር ስትታመም መርመር መርመር አድርገው ደቡብ አፍሪካ የሚሉት ነገር አለ፤ህንድ ህንድ ህንድ – እሱማ መቼ ጠፋን አይደል እንዴ? አንዳንዴ አሁን በሰባት ቀን ነው ይህ ህክምና የተደረገው አይደለም እሱን ስታዩ ምን ተሰማችሁ; እንደሁ ለትንሽ ትልቁ የሆነ የሆነ አገር እየሄድን” አንድ የመገናኛ ብዙሓን ፕሮግራም በመርህ ደረጃ ፍትሓዊ የሆነ መረጃን ለህዝብ ማቅረብ እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ከላይ ያየነው አስተያየት ግን በመረጃ ያልተደገፈ ወደ አንድ ወገን ያደላ አባባል ነው፡፡ አስተያየቱ ሁሉም የሃገራችን ሀኪሞች ህመምተኞችን ወደ ዉጭ ሀገር እንደሚልኩ ሆኖ የተሰጠ በመሆኑ ህዝቡ በሐኪሞች ላይ ያለውን እምነት ይጎዳል፡፡ይህ አባባል ከአገራችን ታካሚዎች ምን ያህሉ ውጪ አገር ሄደው ይታከማሉ፤ ምን ያህሉስ መታከም ይችላሉ የሚለውን በቅጡ ያላገናዘበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ አቶ ሰይፉ በሚሊዮን የሚቆጠረውን የአገራችንን የህክምና ተገልጋይ ኢትዮጵያዊንና በገጠርና ከተማ የዚህን ተገልጋይ ጤና ለመጠበቅ ሌት ተቀን የሚለፉትን ሀኪሞች አያውቋቸውም ማለት ነው፡፡ ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በሚሰጠው የህክምና አገልግሎትና ከአብራኩ በወጡትና በሚያምናቸው ልጆቹ በሚያገኘው አገልግሎት ደስተኛና መንግስት በሚያቀርበው የህክምና አገልግሎትም እምነትና ተስፋ አለው ብለን እናምናለን፡፡ ችግሮችና ጉድለቶች ቢኖሩም በሂደት በመተባበር ይፈታሉ ብሎ ያምናል፡፡

ሐኪሞቻችንም በእውቀታቸውና በህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት መጠን ታካሚዎቻቸውን አገልግለዋል፤ በማገልገልም ላይ ናቸው፡፡ በአገር ዉስጥ ለማይሰጥ ህክምና ታካሚን ወደ ዉጭ አገር መላክ ደግሞ የነበረ፤ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ እንደ አገር እና እንደ ህዝብ አገራችንን በማሳደግና ህክምናችንን በማበለጸግ ይህንን አሠራር ለማስቀረት ጥረት ይደረጋል፤ እተደረገም ነው፡፡ ሀኪሞቻችንም እራሳቸውን በዕውቀትና በክህሎት በማሳደግ ታካሚዎቻቸውን በአገራቸው ለማከም እየለፉና እየተሳካላቸውም ነው፡፡

አቶ ሰይፉይህንን እውነታና በአጠቃላይ የአገሪቱን የህክምና እድገት በቅርበት አለማወቃቸውን በንግግራቸው በግልጽ አሳይተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአንድን ህክምና ክብደትና ቅለት በወሰደው ቀንና በወጣው ገንዘብ መጠን ለመገመት ሞክረዋል፡፡ ይህ በጣም የተሳሳተና አላዋቂነትን የሚያሳይ አካሄድ ነው፡፡ በብዛት ከሚያውቋቸው ሀኪሞች አንዱን ለመጠየቅ እንኳን ባይፈልጉ በዚህ የመረጃ ዘመን የታካሚውን ችግር በቀላሉ መረዳት በቻሉ ነበር፡፡ የአንድን ታካሚ ህይወት ለመታደግ ደቂቃዎችና ትንሽ ወጪ የሚጠይቀውን ያህል፤ የተደረገው ጥረትና የወጣውን ወጪ ሁሉ የታካሚውን ህይወት የማይታደግበት ወቅት ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች በዚህ ውጣ ውረድና ትግል ዉሰጥ በመኖር የኢትዮጵያዊ ወገናቸውን ህይወት ለመታደግ የሚጥሩ እንጂ እሳቸው እንዳቀረቧቸው ወደ ህንድና ደቡብ አፍሪካ ለማስተላለፍ የሚተጉ የታካሚ አስተላላፊ ትራፊኮች አይደሉም፡፡

2. “አሁን ብዙ ሰዎች በአንድ ዶክተር የማያምኑበት ዘመን ላይ ደርሰዋል”

ይህ አባባላቸው ሀኪሞችን ሁሉ በቂ እውቀትና ልምድ እንደሌላቸው ፤በሽታን አክሞ የማዳን ብቃት እንደሌላቸው አድርገው ያቀረቡ በመሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠረውን ህመምተኛ እያከመ የሚኖረውን ሀኪም ብቃትና እውቀት ማጣጣል ነው፡፡ በቅርብ አመታት አገራችን የሀኪሞችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን በማሳደግ ላይ ትገኛለች፡፡ ያም ሆኖ አሁንም የሃኪሙ ቁጥር ከህዝቡ አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው፤ በዚህም ምክንያት አንድ ሀኪም ብቻ ያላቸው የጤና ተቋማት አሉ፡፡ እንደ አቶ ሰይፉ አባባል በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ታካሚዎች ሁለተኛ አስተያየት ለማግኘት ስንቃቸውን ይዘው ኪሎሜትሮችን አቋረጠው መሄድ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ብዙሀኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ማድረግ እንደሚችል ፍርዱን ለህዝብ እየተውን እሳቸው ግን አንድም የወጡበትን ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ አቅም የዘነጉት ይመስላል፡፡ በሌላ ጎን ደግሞ መንግስት ጤናን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት አያውቁም ለማለት እንድንደፍር ገፋፍተውናል ለማለት እንችላለን፡፡ አቶ ስይፉ በዚህ አባባላቸው ህዝቡ በኢትዮጵያውያን ሀኪሞች እውቀትና ክህሎት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ልናረጋግጥላቸው የምንወደው አንድ ሀቅ ግን የአገራችን ሀኪሞች በየትኛውም አገር ካሉት ሃኪሞች የማይተናነሱ መሆናቸውን ነው፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ በአገራችን ሰዎች አለመኩራትና አለተማመን በአብዛኛው ሲያጠቃን የኖረ አባዜ ነው፤ በአሁን ዘመን ይህን አመለካከት ለማፀጸባረቅ መሞከር ግን ኋላቀርነት መስሎ ይሰማናል፡፡

3. “ዶክተሮቻችን አሁን ደግሞ አይታችሁ ከሆነ ሁለት ሶስት ስራ ነው የሚሰሩት፤ ያው የኑሮ የወጪ ነገር ይመስለኛል ብቻ የመዳከም ብቻ እንዲህ አይነት በሰባት ቀን ሊድን የሚችል…”

በመሰረቱ ሀኪሞች በትርፍ ሰዓታቸው ተጨማሪ ስራ እንዳይሰሩ የሚከለክል ህግ የለም፡፡ ህጉ በግልጽ የሚያስቀምጠው ማንኛውም የጤና ባለሙያ በመደበኛውም ሆነ በትርፍ ሰዓት በሚሰጠው የህክምና አገልግሎት አኩል እንክብካቤ እንዲሰጥ ነው፡፡ አሁን ካለው የሃኪሞችና የታካሚ ቁጥር አለመመጣጠን ጋር ሲገናዘብም ሀኪሞች በትርፍ ሰዓታቸው በተለያየ ቦታ መስራታቸው ሊበረታታ እንጂ ሊነቀፍ አይገባም ብለን እናምናለን፡፡ አንድ ሃኪም በመደበኛውና በትርፍ ሰዓት አገልግሎቱ ላይ ልዩነት አድረጓል ከተባለ እንኳን ለሚመለከተው ክፍል በማቅረብ አሰፈላጊው እርምት እንዲደረግ ማድረግ ሲቻል ሚሊዮኖች በሚከታተሉት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ወጥቶ የሁሉም ሀኪሞች ችግር እንደሆነ ማቅረብ ከጋዜጥኝነት ስነምግባርም ሆነ ከህሊና ዳኝነትም አንጻር ተገቢ አይደለም እንላለን፡፡ እንደሳቸው ያለና በሚዲያው ውስጥ አመታትን ያስቆጠረ ግለሰብ ደግሞ የሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሆኑ ባለስልጣኖቹን ማግኘትና ችግሩን ማስረዳት ይቸግራቸዋል ብሎ ማሰብ ግን ይከብደናል፡፡ የዶክተሮቻችንን ኢኮኖሚያዊ ህይወት ለማስረዳት ከተፈለገ ደግሞ ማህበራቸውም ሆነ በሺዎች የሚቆጠሩት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተሰማሩት ሀኪሞች ፈቃደኛ እንደሚሆኑ በዚሁ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

4. አቶ ሰይፉ ፋንታሁን በራሳቸው ላይ የደረሰባቸውን በዋቢነት በአቀረቡበት አባባል ላይ ሁለተኛ ላይ ያያቸው ሀኪም መጀመሪያ ያያቸውን ሀኪም “የጋራዥ ሰራተኛ ነው እንዴ?” ብሎ እንደጠየቃቸው ተናግረዋል፡፡ከህክምና ስነ-ምግባር መርሆች ዉስጥ አንደኛው ሀኪሞች እርስ በእርስ የሚኖራቸው መከባበርና ግንኙነት ነው፡፡ ማንም ሀኪም በታካሚ ፊት የሌላን ሀኪም ስምና ሰብዕና እንዳያጎድል አድርጎ ከተገኘ ግን በስነ-ምግባር ህጉ መሰረት እነደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ እኛም እንደ ሙያ ማህበርነታችን ይህን ጉዳይ ተከታትለን ህግ ፊት ማቅረብ ግዴታችን ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ መረጃውን እንዲያካፍሉን እየጠየቅን የሚመለከተው የመንግሰት አካልም ጉዳዩን እንዲያውቀው በዚህ ደብዳቤ ግልባጭ ማሳወቃችንን እንገልጻለን፡፡ የህክምና ስነ-ምግባርን ማስከበር የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን አቶ ሰይፉም ሆኑ ቴሌቪዥን ጣቢያችሁ ተረድታችሁ ጥያቄያችንን እንደምትቀበሉና መረጃውን አንደምትሰጡንም ምንም ጥርጥር የለንም፡፡

ቴሌቪዥን ጣቢያችሁ ኢትዮጵያዊ ባህሎችንና እሴቶችን በማሰተዋወቅ ረገድ፤ በህክምናው ዘርፍ በአገሪቷ እየተከናወኑ ያሉትን እምርታዎች በማስተዋወቅ ረገድ እየተወጣ ያለውን አስመስጋኝ ስራ ከሚያውቁትና ከሚመሰክሩት ውሰጥ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አንዱ ነው፡፡ እናንተም እኛም የሙያን ክቡርነትና የስነ-ምግባር መርሆዎች በግልጽና በጥልቅ እናውቃለን፡፡ የሚዲያ ስራ ለሚሊዮኖች የሚቀርብ ስለሆነ ደግሞ ስራው ኃላፊነት የበዛበትና ተጠያቂነት የሞላበት ነው፡፡ የህግ ተጠያቂነት ባይኖር እንኳን የህሊና ተጠያቂነት አለበት፤ ይህም ሁለቱን ሙያዎች ያመሳስላቸዋል፡፡ ለምንናገራቸው ንግግሮች ጥንቃቄ ካላደረግን የምናደርሰው ጉዳት ከምንጠብቀው በላይ ይሆንብናል፡፡ የአገራችን አዋቂ ይህን ተገነዝቦ ነው “ጦር ከፈታው፤ ወሬ የፈታውና የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” የሚሉ ብሂሎችን የተጠቀመው፡፡ ይህንን ሐቅ ብዙ ዘመናቸውን በሚዲያ ዉስጥ ያሳለፉት አቶ ሰይፉ ፋንታሁን እንደሚያውቁ ጥርጥር የለንም፡፡ እሳቸውም ሆኑ ቴሌቪዥን ጣቢያችሁ በኢትዮጵያውያን ሃኪሞችም ሆነ በኢትዮጵያ የህክምና አገልግሎት ላይ ቂም ወይም ጥላቻ ይኖራችኋል ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ እውቅናን ለማግኘት ነው እንዳንል የአቶ ሰይፉን መናገር ባንችልም ጣቢያችሁ ግን በአለም የታወቀ፤ የተከበረና ሙያዊ ስነ-ምግባርን የተላበሰ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡ ስህተት ቢኖር እንኳን በመነጋገርና በመተራረም የምታምኑ እንጂ ለርካሽ እውቅና የማትሮጡ እንደሆናችሁ ያለፈው ስራችሁ ምስክራችሁ ነው፡፡ ነገር ግን በእኛም ዉስጥ እንዳለው በእናነተም ዉስጥ ሙያውን የሚያሰድቡ እንክርዳዶች አይጠፉምና እነዚህን ነቅሶ ማውጣት አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ላጠፉት ጥፋት ካሳ መክፈል ባይኖር እንኳን ጥፋትን ተቀብሎ ይቅርታን መጠየቅ ትልቅነትና ኢትዮጵያዊ ባህልም ነው፡፡ አቶ ሰይፉ ፋንታሁንም ሆኑ ቴሌቪዥን ጣቢያችሁ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞችን አስከፍታችኋል፤ በጤናው ዘርፍ የተሰራውንም ስራ አጣጥላችኋል ብለን ስለምናምን ባለሙያውን በይፋ ይቅርታ ልትጠይቁ ይገባል እንላለን፡፡

ከሠላምታ ጋር

ዶ/ር ገመቺስ ማሞ

የኢትዮጵያ ህክምና ማሕበር ፕሬዚዳንት

ግልባጭ

• ለፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስተር

• ለዶ/ር ከበደ ወርቁ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ

• ለዶ/ር አሚር አማን

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ

• ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር

• ለጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር

የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

• ለጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር

የህክምና ግብአቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር

• ለኢትዮጵያ የምግብ፤ የመድኃኒትና፤ የጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን

• ለኢ.ፌ.ድ.ሪ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

• ለኢ.ፌ.ድ.ሪ የብሮድካስት ባለስልጣን

• ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር”

LEAVE A REPLY