መልካም እረፍት ለወንድሜ ታድዮስ በየነ! /‎ሙሉነህ ኢዩኤል/

መልካም እረፍት ለወንድሜ ታድዮስ በየነ! /‎ሙሉነህ ኢዩኤል/

የቅንጅት አባላትና ደጋፊ በመሆናቸው ብቻ ህይወታቸውን ያጡ፥ ለአካል ጉዳት የተዳረጉ፥ የታሰሩ አልያም ከስራ ወይም ከቀየ የተፈናቀሉ እጅግ ብዙ ነበሩ። በኢትዮጵያውያን ላይ የሚወርደው መአት በቅንጅት ጊዜ የጀመረ ባይሆንም ዛሬም ግን አላባራም።

ይህን ጥሁፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ ሰው ግን በቅንጅት ጊዜ የነበረውን እንዳስታውስ አድርጎኛል። ታድዮስ በየነ ይባላል። ቅንጅት ካስተዋወቀኝ ብሩህ ወጣቶች አንዱ ነው። በተለይ ከአራቱ የቅንጅት ፈጣሪ ፓርቲዎች ውህደት በኋላ የአራቱን ፓርቲዎች ወጣቶች በአንድ የድርጅት መዋቅር ውስጥ አድርጎ እንደገና ማዋቀር ትልቅ ስራ ነበር። በዚህ ስራ ውስጥ በተለይ በአዲስ አበባ በነበረው የማዋቀር ሂደት በንቃት ተሳታፊ የነበሩ ሶስት ወጣቶችን ታድዮስ በየነን፥ ሰብለወርቅ ታደሰንና አለማየሁ መሰለን መዘንጋት የሚቻል አይመስለኝም።

በተለይ በቅንጅት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት እነዚህ ወጣቶች ብዙ ደክመዋል። በመጨረሻም የድካማቸውን ዋጋ በእስራት ተቀብለዋል። እነርሱም ለድካማቸው በተከፈላቸው ዋጋ የሚጸጸቱ አይመስለኝም። ለራሳቸው ነጻነትና ለአገራቸው ህዝብ የህይወት መሻሻል ላደረጉት ድካም እስራትን እንደጸጋ የሚቆጥሩ ይመስለኛል።

ታድዮስን ዛሬ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፤ በእድሜ ታናሼ የሚሆንን የታዲዮስ በየነን ማረፍ ሰምቼ በጣም ቢያሳዝነኝ እንጂ። ምንም እንኳን በጠና መታመሙንና በህይወት የመቆየት ተስፋው የመነመነ መሆኑ በሃኪሞቹ ተነግሮት በስደት ከሚኖርበት አውስትራሊያ በህይወት የሚቆይባቸውን የመጨረሻ ቀናት ከቤተሰቦቹና ከዘመዶቹ ጋር ሊያሳልፍ ወደኢትዮጵያ የመመለሱን አስደንጋጭ ዜና አስቀድሜ ብሰማም ማረፉን ስሰማ ግን በጣም ደንግጫለሁ፤ በጣምም አዝኛለሁ።

ታድዮስን ሳስብ ሁል ጊዜ የማይረሱኝ ሶስት ነገሮች አሉ።እነርሱም፦ የታዲ ሳቅ፥ የታዲ ትህትናና፥ የታዲ ብሩህ አእምሮ። ይህን እየጻፍኩ እንኳ ታዲ ፊቴ ላይ ቆሞ እየሳቀ በአይነ ህሊናዬ ይታየኛል።

ታዲ በወጣትነቱ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከልቡ የታገለ ረጅም እድሜን ቢታደል ብዙ ብዙ ሊያበረክት የሚችል ወጣት ሰላሳዎቹን እንኳ ሳያጋምስ አርፏል።

ታድዬ ሳንጠግብህ ስለተለየሀን ሃዘንህ ቢበረታብንም የብሩህ አእምሮህ፥ የትህትናህና የሳቅህ ትዝታ በህይወት እስካለን ድረስ አብሮን ይኖራል።

መልካም እረፍት
ለወንድሜ ታድዮስ በየነ!

LEAVE A REPLY