ከአፍዴራ በየወሩ 300 ሽህ ኩንታል ጥራቱን ያልጠበቀ ጨው ለገበያ እየቀረበ ነው ተባለ

ከአፍዴራ በየወሩ 300 ሽህ ኩንታል ጥራቱን ያልጠበቀ ጨው ለገበያ እየቀረበ ነው ተባለ

/Ethiopia Nege News/:- በአፋር ክልል የሚገኘው አፍዴራ ጨው ማምረቻ ድርጅት ሳይታጠብና ጥራቱን ሳይጠብቅ እስከ 300 ሺህ ኩንታል የምግብ ጨው(የገበታ ጨው) በየወሩ ወደ ገበያ እንደሚቀርብ ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661/2009 “ማንኛውም ምግብ ወይም የምግቡ ጥሬ እቃ፣ ወይም ማሸጊያ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን የሚያሟላ መሆኑ ካልተረጋገጠ በስተቀር ለአገልግሎት ሊውል አይችልም።” በማለት የሚከለከል ቢሆንም የአፍዴራ የጨው ማምረቻ በአዮዲን ያለበለጸገና ለጤና ጠንክ የሆነ የገበታ ጨው ለህብረተሰቡ እየቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

የፋብሪካው ሀላፊዎች “የማጠቢያ ማሽን የሌለን በመሆኑ በጉድጓድ ውስጥ(Pond) በማጠብ በአዮዲን ለማበልጸግ በመሞከር በየወሩ 300 ሺ ኩንታል ጨው ለገበያ እያቀረብን ነው።” ማለታቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን መጋቢት 2009 ዓ.ም ድርጅቱ ምንም አይነት ምርት እንዳያመርትና ወደ ገበያ እንዳያሰራጭ እገዳ ጥሎበት የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆኑን ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለገበያ የሚቀርበው 90 በመቶ የሚሆነው የገበታ ጨው በአዮዲን ቢበለጽግም፤ ጥራቱን የሚጠብቀው ግን 26 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነውም ተብሏል።

LEAVE A REPLY