ሆድ ካገር አይሰፋም /‎ሳምሶን አስፋው/

ሆድ ካገር አይሰፋም /‎ሳምሶን አስፋው/

ድሮ! ድሮ! ያኔ – አበው ሲተርቱ፤
አበባ ወግ ቀስመው – ማር ነገር ሲያመርቱ፤
ሆድ ካገር ይሰፋል! – ይሉ ነበር አሉ፤
በትዝብተ-ህይወት – ቁምነገር ሲኩሉ፤

የታገሱት ነገር – ችለው ያሳለፉት፤
ይበጃል እንዲሉ – ለፍቅር ጤንነት፤
የነገር መጋዘን – አርገው ሲመስሉት፤
ይሉ ነበር አበው – ሆድ ካገር ይሰፋል፤
መከራም ችግርም – ከታገሱት ያልፋል!

ግና የአበው ተረት – የጥንት የጠዋቱ፤
የሆድ አቅመ-ይዘት፤ወርድና ስፋቱ፤
ከአገር እንደሚልቅ የነገሩን ነገር፤
ዛሬ በኛ ዘመን – ትርጉም ሲመነዘር፤
ሆድ ካገር በለጠ -ቀረና መስፋቱ፤
እበላ ባይ በዝቶ – መከነ ተረቱ!

እናም እኔ እላለሁ! ሆድ ካገር አይሰፋም፤
ተሃድሶ ይሻል – ይሰረዝ ተረቱም …

የሆድ አቅመ ይዘት የዙሪያ ልኬቱ …
እንኳን ከአገር ሊበልጥ ወርድና ስፋቱ..
ከቀፈት መቀነት – ከቀበቶ አይዘለልም፤
አድሮ እዳሪ እንጂ – ስንቅ አይሆን ቅርቅቡም
እናም እኔም እላለሁ ሆድ ካገር አይሰፋም!
ተሃድሶ ይሻል – ይሰረዝ ተረቱም …

1 COMMENT

 1. የሆድ ውርስ አትስረቅ።

  ልብ በል ሳምሶን አስፋውና ይልቅ፤
  በህሊናህ እየው ሞራልክን ሳትደብቅ።
  የአገርና ነጻነት ድምሩ ሲሰላ፤
  ፖለቲካ ይሆናል መንግሥትም ቢጠላ።
  ነጻነቴን መብቴን ብለህ ከተነሳህ፤
  መታገል ብቻ ነው ሆድህ ሳያሳሳህ።
  ስሌቱ ካልገባህ እንደ አጀማመሬ፤
  መንግሥት እንዳይገድልህ አትበል አገሬ።
  አሁን ታየህ ትንሽ ሆድን የመሰለ፤
  አገር ነጻነትን ሁሌ እያበሰለ፤
  “ፖለቲካ” የሚባል ለሕዝቦች ያድለ፤
  የሁላችንም መብት ማስፈራሪያ እንዳለ።
  ይታይሃል የሆድ የግዛቱ ግዝፈት፤
  በሰው ሃምሳል ልቦና በህሊና ሲከፈት።
  ወይስ አይታይህም ያባቶች ምሳሌ፤
  እዚህች ነው የምታስብ ካጠገብህ ሁሌ።
  እንግዲያው ላስረዳህ ገባህም አልገባህ፤
  መጀመሪያ ካገር ሰው ይበልጣል ይግባህ።
  አሁንም ሩቅ ሆኖ ካልገባህ የኔ መልስ፤
  ቃል በቃል ላስረዳህ በህሊና እንመለስ።
  ለገጠመው ችግር መፍትሄ የሚሻ፤
  ትዕግስት ነው መልሱ እስከመጨረሻ።

LEAVE A REPLY