ሳዑዲ አረቢያ የሁለት ኢትዮጵያዊያንን አንገት ቀላች

ሳዑዲ አረቢያ የሁለት ኢትዮጵያዊያንን አንገት ቀላች

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ዛሬ በሪያድ አንገታቸው በሰይፍ የተቀላው ሁለት ኢትዮጵያዊያ የታክሲ አሽከርካሪ ነበር የተባለን ፓኪስታናዊ ለመዝረፍ ሲሉ መግደላቸውን የ“ሸሪያ ፍ/ ቤት” ውሳኔ በማሳለፉ ነው ሲል የሳውዲ ሀገር ውስጥ ሚንስትር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

መግለጫው የሁለቱን ኢትዮጵያዊያን ሙሉ ስም በመጥቀስ ባቀረበው ሐተታ በፓኪስታናዊው ላይ ግድያውን የፈጸሙት ወደ ገጠራማ አካባቢ ወስደው በያዙት ስለት በመውጋት ገድለው የያዘውን ገንዘብና ቁሳቁስ በመዝረፍ ወንጀሉን በፈጸሙበት ቦታ ንብረቱን ተካፍለው መመለሳቸውን ያትታል።

ሟቹን የተሽከርካሪው ወንበር ጋር አስረውት ስለነበረ ወንጀለኞቹን ለማግኘት እንደረዳቸው ጠቅሰዋል።ኢትዮጵያዊያኑ ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነዋልም ተብሏል።

የአገር ውስጥ ሚንስትር ይህንን የቅጣት ዜና ይፋ የሚያደርገውም ፍትህ ለማስገኘትና የሸሪዓን ህግ ተፈጻሚ ለማድረግ ነው በማለት አስረድቷል።

የሳውድ አረቢያ ንጉሳዊ አገዛዝ እጅግ ሗላ ቀር የሆነ የአስተዳድር ዘይቤ ከሚከተሉ ሀገራት ቀዳሚ እንደሆነ ይገለፃል። ከዚህ ቀደምም የሳውድ አረቢያ መንግስት የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት በየጊዜው “ውሀ ቀጠነ” በማለት ሲቀጥፍ መቆየቱ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያን በዲፕሎማሲ ከጎናቸው የሚቆምላቸው መንግስት ባለመኖሩ ምክንያት የተለያየ በደል በአለም ዙሪያ በተለይም በአረቡ አለም የምደርስባቸው ጥቃት እየተበራከተ መምጣቱን ብዙዎች ይስማሙበታል።

በሌላ በኩል ተጨማሪ የተሰጠው የአንድ ወር “የእፎይታ ጊዜ” ትናንት ተጠናቋል፡፡ ከ400 ሽህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ያለመኖሪያ ፈቃድ በሳውዲ እንደሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ይገልፃሉ። “የውጡልኝ” አዋጁን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው የተመለሱትም ከ100 ሺህ እንዳልበለጡ ታውቋል።

ሳውዲ አረቢያ የዛሬ አራት ዓመት በርከታ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ ከሀገሯ እንዳስወጣች የሚታወቅ ነው።

LEAVE A REPLY