የነቃና ተግባር ተኮር ማህበረሰብ አገዛዝን አይሸከምም!!! /ከሰማያዊ/

የነቃና ተግባር ተኮር ማህበረሰብ አገዛዝን አይሸከምም!!! /ከሰማያዊ/

ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ

ባለፉት ዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝብ በየወቅቱ ያጋጠሙትን የአስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የማሕበራዊና የፍትህ ጥያቄዎችን አገዛዙ መፍትሄ እንዲሰጠው በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አገዛዙ የሚያደርሰውን ግፍና በደል እንዲያቆም በህዝብ የተጠየቀውን አሻፈረኝ በማለት ጥያቄ ያነሱ ወገኖችን ሁሉ ከማንቋሸሽ፣ ከመፈረጅ፣ ከማጥላለት ከማሰር፣ ከማሳደድ እና ከመግደል ውጭ የተመለሰ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄ የለም፡፡

በእኛ እምነት በተለመደው ሁኔታ አገዛዙን መጠየቅ መጨረሻው ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ከመሆን አላለፈም፡፡ስለሆነም፡-

1.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ዜጎችን በጠራራ ፀሀይ ግንባር ግንባራቸውን በማለት የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

2.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸውና ከሀብትና ንብረታቸው አንዳይገፉና እንዳይፈናቀሉ መጠየቅ ከንቱ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና
3.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ራሱ በፃፈው ህገ መንግስት መሰረት ዜጎች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ለማስተዳደር የማንነት ጥያቄ ማቅረብ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

4.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የህዝብን በደልና ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ በየማጎሪያ ቤቱ የተጣሉ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ይፈቱ ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

5.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ አገዛዙ በየሃይማኖት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ እየገባ ማመስና መበጥበጡን ያቁም ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

6.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት ይስፈን ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

7.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ አፋኝ አዋጆች ይሰረዙ ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

8.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ፍትሃዊና ነፃ የምርጫ ስርዓት ይዘርጋ ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

9.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ የሲቪክ፣የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብቶች ይከበሩ ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

10.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ኢትዮጵያውያን በዜግነት የምንጋራቸው የዜጎችን ትስስር መስተጋብርና አብሮነት የሚያበለፅጉ እሴቶቻችን ይጠበቁ፤ ይከበሩ ብሎ መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

11.በዛሬዋ የህወሃት/ኢህአዴግ አትዮጵያ ስለ ሀገር ሉዓላዊነት፣ ዳር ድምበር እና ብሔራዊ ክበር፣በተለያዩ ሀገሮች በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል፣ ግድያና መከራ እንዲያስቆም አገዛዙን መጠየቅ ትርፉ ድካም ነው፤መልሱ ምን እንደሆነ አውቀናልና፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ዋና ዋና ሀገራዊ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ታስራዋል፣ ተገርፈዋል፣የሚወዱዋትን ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፣ የህይወት ዋጋ ከፍለዋል፡፡በመሰረቱ ዴሞክራሲ የሚወለደው አምባገነን ስርዓት ህዝብን አፍኖ ለመግዛት በሚያደርሰው በደል እና ይህን በደል አልቀበልም ብሎ በሚጋፈጥና ዋጋ በሚከፍል ማህበረሰብ መካከል በሚፈጠር የግጭት ውጤት ነው፡፡በአለም የፖለቲካ ታሪክም አገዛዝ ፈቅዶ የህዝብን መብት አክብሮ አያውቅም፤ የነቃ ህዝብንም በዘላቂነት አሸንፎ አያውቅም፡፡

ስለሆነም ይህንን መሰረታዊ መርህ በመቀበል የአንድ የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነውን የአንድ ወገን መብት መገፈፍ የሌላውም መብት መነካት መሆኑን እና ለጋራ ሀገራዊ ጥያቄዎቻችን የማይተካ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎቻችንን ከተራ የቁጥር አሃዝ በላይ የከፈሉትን መስዋዕትነት ለእኛ መሆኑን ከልባችን አምነን በተለመደው ሁኔታ አገዛዙን ከመለመን ወጥተን የማንፈልገውን ስርዓት ለውጠን የምንፈልገውን ስርዓት መትከል የምንችል ማህበረሰብ ሆነን ስንገኝ እና በተግባር እምቢ ስንል መሆኑን በማመን ቆርጠን በጋራ እንድንነሳ ጥሪያችንን አናስተላልፋለን፡፡

ሐምሌ 16 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY