15ኛውን በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ አሰራር ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ያወጡት...

15ኛውን በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ አሰራር ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ያወጡት መግለጫ

እ·ፈ·አ· ከጁላይ 26 እስከ ጁላይ 29·2017 በጣሊያን ሮማ የተካሄደው ዝግጅት ከጅምሩ ድብቅ በሆነ አሰራርና የገዢውን ስርዓት ፍላጎት ለማሟላት ተብሎ ዝግጅቱ ሮማ እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ የፌስቲቫሉን ፖለቲካዊ ጠለፋ አስተማማኝ ማስረጃዎችን አቅርበን ህብረተሰቡ በዝግጅቱ ላይ የወያኔን የንግድ እቅድ ተረድቶ የራሱን ማዕቀብ እንዲያደርግ ጣሪ ስናደር መቆየታችን ይታወቃል። ዝግጅቱ ከተጀመረ በኋላም የታዩት ነገሮች ቀደም ሲል የነበሩትን መረጃዎች ይበልጥ የሚያጠናክሩ ሆነውም ታይተዋል።

በዝግጅቱ ስፍራ የነበሩትን የንግድ ተቋማትና ድንኳኖችን ዞር ዞር ብሎ የተመለከተ ሁሉ ዝግጅቱ የወያኔ ስለመሆኑ ይመሰክራል። ለምሳሌ ያህልም ከነበሩት አስር የምግብ ድንኳኖች ውስጥ ስምንቱ ከአንድ ዘር ለሆኑ የስርዓቱ ነጋዴዎች ሲሰጥ ሁለቱ ደግሞ ከወያኔ ጋር ለተለጠፉ አቅራቢዎች የተሰጠበትን እውነት መጥቀስ ይቻላል። የስርዓቱ ሰዎች ከኢትዮጵያ ድረስ ሸቀጦችንና መጠጦችን እንዲሁም ጫት አምጥተው ሲነግዱ የታየበትም ሀቅ ነበር። በአጠቃላይ ዝግጅቱ ወያኔ ከሀገር ቤት መጥቶ የንግድ ስራውን ያቀረበበት እንጂ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ዝግጅት አልነበረም ማለት ይቻላል።

ወያኔ በሀገር ውስጥ ሁሉን ተቆጣጥሮ ነጻ ተቋም እንዳይኖር ብቻ ሳይሆን በነጻ ተቋማት ስም ካድሬዎቹን አሰማርቶ ህዝባችንን መፈናፈኛ ያሳጣው ሳያንስ በስደት ዓለም ያሉ ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚሄድበትን ርቀት ለመረዳት የሮማው ዝግጅት ጥሩ ማሳያ ነበር። እኛን ከሁሉም በላይ የሚከብደንና አእምሯችን ሊቀበለው የማይፈቅደው ነገር በተለይ ዘረኝነትን ሲሆን ሮም ላይ የታየው የወያኔ ወገን የሆኑ ተለይተው ብዙሀኑ ደግሞ ተገልለው የሚደረግን ጸያፍ ተግባር ማውገዝ ብቻ ሳይሆን አምርረን የምንታገለውም ነው። ለዚህም ነው ገና ከጅምሩ ዝግጅቱ በወያኔ መጠለፉን በቂ መረጃ እንዳገኘን ነጻ የሆነና ኢትዮጵያዊያንን በጥቅምና በፖለቲካ ሳይደለል የሚያገለግል ፌዴሬሽን ያስፈልገናል ብለን የተነሳነው። በዝግጅቱ ላይ የሚነግደው ወያኔ መሆኑን በመረዳታችንም የህዝባቸው በወያኔ መጨቆን የሚያሳስባቸው ወገኖች ወደ ሮማ እንዳይሄዱ ከሄዱም ገንዘባቸውን ለስርዓቱ ከማውጣት እንዲታቀቡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጥሪ ስናደርግ ቆይተናል።

በእርግጥ ቀደም ሲል ዝግጅቱ በወያኔ ስለመጠለፉ ይነሱ የነበሩ ሀሳቦችን መነሻ አድርገን አስተማማኝ መረጃ እስክናገኝ ጥሪያችን የዘገየ ቢሆንም በነበረው አጭር ጊዜ ስለሁኔታው ህብረተሰባችን በቂ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ እንደቻልን እናምናለን። ከዚያም አልፎ ዝግጅቱን ባለፉት ዓመታት የተከታተለ ሁሉ የሚያውቀው እንደመሆኑ ከሁሉም አመታት ዝግጅቶች ጋር ሲነጻጸር ደካማውና አነስተኛ ታዳሚ የተገኘበት እንደነበር ሁሉም ያስተዋለውና እኛም በመረጃ ያረጋገጠነው ነው። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እስካሁን ከተደረጉት ዝግጅቶች ሁሉ ብዙ ህዝብ የተገኘበት በሚል በፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር አማካይነት የተሰጠው መግለጫ ድሮም ከወያኔ ጋር የዋለ እውነት ሊናገር እንደማይችል ያሳየ ነበር።

እኛ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን ኢትዮጵያዊያንን አንድ ላይ በማሰባሰብ ረገድ ትልቅ ስራ ሊሰራ የሚችል ተቋም እንደሆነ እንረዳለን። ይሁንና ወያኔ በሰሜን አሜሪካ የተደረገው በአላሙዲን የታገዘ ጥረት አልሳካ ሲለው ፊቱን ወደ አውሮፓ አዙሮ ይህን ተቋም ሲቆጣጠር ከቶም በዝምታ አናይም። ፌዴሬሽኑ ሙሉ ለሙሉ ከወያኔ እስኪጸዳና ነጻ የኢትዮጵያዊያን ተቋም እስኪሆንም የጀመርነውን ትግል አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እናረጋግጣለን።

በመጨረሻም የዘንድርውን የሮም ዝግጅት አስመልክቶ በእኛ በኩል ያደረግነውን ጥሪ ተቀብላችሁ ብዙዎች ጉዟችሁን መሰረዛችሁን፣ ብዙዎች ሮም ከሄዳችሁ በኋላም ገንዘባችሁን ለወያኔ ላለመስጠት የራሳችሁን ተአቅቦ ማደረጋችሁን ከተገኘው ውጤት በሚገባ እንረዳለን። በአጭር ጊዜ ውስጥ ላደረግነው ጥሪ ወገናዊ ምላሽ ለሰጣችሁን፣ ሀሳብና መረጃ ላካፈላችሁን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ላቅ ያለ አክብሮታችንንና ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን። ወደፊትም በጋራ ተናብበን በምንሰራው ጠንካራ ስራ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንንም ከወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ነጻ እናወጣለን።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን በወያኔ መጠለፉ አሳስቦን የተሰባሰብን ኢትዮጵያዊያን በጋራ።

LEAVE A REPLY