በኬንያ አጠቃላይ ምርጫ እየተካሄደ ነው

በኬንያ አጠቃላይ ምርጫ እየተካሄደ ነው

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ኬንያውያን ፕሬዚዳንታቸውንና የፓርላማ አባላትን ለመምረጥ ዛሬ ድምፃቸውን እየሰጡ ነው። ለሁለተኛ ዙር የሚወዳደሩት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ትናንት በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክታቸው ምርጫው በሰከነ መንፈስ እንዲካሄድ አጥብቀው ጠይቀዋል።

በዚህ ምርጫ 19 ሚሊየን ህዝብ ለመምረጥ እንደተመዘገበ የተገለጸ ሲሆን ኬንያዊያን በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ሰጥተው በሰላም ወደየ ቤታቸው እንዲያመሩ እንዲሁም ሀይማኖትን፣ ጎሳንና ቀለምን መሰረት ያደረገ ልዩነት ከመፍጠር ይልቅ አንድነታቸውን እንዲያጠነክሩ የ55 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ኬንያታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል የተቃዋሚዎች ጥምረት የሆነው የናሽናል ሱፐር አሊያንስ (NASA) መሪና የፕሬዚዳንት ኬንያታ ዋነኛ ተፈካካሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ በበኩላቸው፥ የምርጫው ውጤት ሊጭበረበር እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ገልፀው፥ 150 ሺህ ገደማ የፀጥታ ሀይሎች የተሰማሩትም በመራጮች ላይ ጫና ለመፍጠር ነው ብለዋል።

ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለ4ኛ ጊዜ እየተወዳደሩ ያሉት ራይላ ኦዲንጋ ምርጫውን “ጠንካራ እጩ” ሆኖ የቀረበው ያሸንፋል ብለዋል። ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት “ምርጫን የማላሸንፍ ከሆነ ውጤቱ ተጭበርብሯል ማለትነው።” ማለታቸው የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ግጭት እንዳይነሳም ስጋት አለ። የ72 ዓመቱ ኦዲንጋ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ይህ ምርጫ የመጨረሻቸው ይሆናል።

የፕሬዚዳንት ኬንያታ አባት ጀሞ ኬንያታና የራይላ አባት ጃራሞጊ ኦጊንጋ ኦዲንጋ፤ የጸረ-ቅኝ ግዛቱን ትግል አብረው በጋራ ታግለው ነፃ ወጡ። በሗላም የሀገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጀሞ ኬንያታ እንዲሁም ጃራሞጊ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኑ።ነገር ግን ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመታት በሗላ ጀሞ ኬንያታ ምክትላቸው አሰሩ።የሁለቱ የነጻነት ታጋዮች እስከ መጨረሻው የፖለቲካ ባላንጣ ሆነው አለፉ። በዛሬው ምርጫ ደግሞ የሁለቱ ልጆች በሰላማዊ ምርጫ እየተፋለሙ ነው።በ2013 በተካሄደው ምርጫ ኬንያታ ኦዲንጋን ማሸነፋቸው አይዘነጋም።

በአጠቃላይ ምርጫው ኬንያውያን ፕሬዚዳንታቸውን፣ የፓርላማ አባላትን፣ ሴት የፓርላማ አባላትን፣ የአካባቢ ገዢዎችንና ሴናተሮችን እየመረጡ ነው።

በ2007 በተደረገ ምርጫ በወቅቱ ይወዳደሩ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዳንኤን አራፕ ሞይ “ድምፅ አጭበርብረዋል” በሚል በተነሳ ግጭት ከአንድ ሽህ አንድ መቶ በላይ ኬንያውያን ሕይወታቸውን ሲገብሩ፤ ከስድስት መቶ ሽህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።በወቅቱ የተነሳውን ግጭት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጣልቃ በመግባት፤ተቃዋሚውና በስልጣን ላይ የነበረውን ፓርቲ ስልጣን በማጋራት አራፕ ሞይን ፕሬዚዳንት፣ ራይላን ደግሞ ጠቅላይ ሚንስቴር በማድረግ አምስቱን ዓመት ሐገሪቷን እንዲያስተዳድሩ በማስማማት ችግሩ መፈታቱ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY