በወልድያ ከተማ ዳግም የስራ ማቆም አድማ ተደረገ

በወልድያ ከተማ ዳግም የስራ ማቆም አድማ ተደረገ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦  በወልድያ ከተማ አላግባብ የተጣለውን ግብር ምክንያት በማድረግ ባለፈው ሳምንት ለ5 ቀናት የስራ ማቆም አድማ መደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ተቃውሞው ዳግም ማገርሸቱ ተሰምቷል። የወልድያ ህዝብ “አላግባብ የተጫነብንን ግብር አንከፍልም” በማለት በትናንትናው እለትም አድማ መቶ መዋሉን ምንጮች ገልጸዋል። ዛሬም ከተመዋ በከፊል ጭር ብላ መዋሏ ተረጋግጧል።

የከተማዋ ህዝብ ግብር አንከፍልም ማለቱን ተከትሎ ወልድያ በአጋዚ ወታደሮች መወረሯን ምንጮቻችን ገልጸዋል። ጥያቄያቸው እስካልተመለሰ ድረስ ተቃውሞው ሊቀጥል እንደሚችልም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከግብር ጫና ጋር በተያያዘ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ጊዜ መንግስት የግብር ቅነሳ ይደረጋል የሚል ማስተባበያ የሰጠ ቢሆንም “ማስተካከያ” አለመደረጉ ታውቋል።በዚህም ምክንያት “ክልል አቀፍ የስራ ማቆም አድማ” ሊጠራ እንደሚችል እየተነገረ ነው።

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ውጥረት የነገሰ ሲሆን በባህር ዳር የታሸጉ ሱቆች አሁንም አልተከፈቱም፤የታሰሩት ሰዎችም ሁለት መቶ የሚሆኑት ክስ ሲመሰረትባቸው ቀሪዎቹ ድግሞ ያለ ምንም ምክንያት በየፖሊስ ጣቢያው ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል።

በጎንደር እስራቱ ቀጥሏል።ከነሐሴ 10 እስከ 15/2009ዓ.ም የተጠራውን የስራ ማቆም አድማ ምክንያት በማድረግ ከተማው በአጋዚ ወታደሮች ተወሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ ነጋዴዎች አላግባብ የተጣለባቸውን ግብር በግዳጅ እየከፈሉ መሆኑንም ምንጮች ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY