ሙስናን ወቅት ጠብቆ በሚደረግ ዘመቻ ማስወገድ ይቻላል? /ሀ. ህሩይ – ከቶሮንቶ/

ሙስናን ወቅት ጠብቆ በሚደረግ ዘመቻ ማስወገድ ይቻላል? /ሀ. ህሩይ – ከቶሮንቶ/

ነሐሴ, 2017

መንግሥት ሙስናን ለመከላከል እና ለማጥፋት የፌዴራል የሥነምግባር እና ፀረ ሙስና ዓዋጅን ካወጣ እና ኮሚሽኑን ካቋቋም በርካታ ዓመታት ሆኗል።

ይሁን እንጂ ይህ ዓዋጅ በየግዜው ማሻሻያ ከሚደረግበት በቀር የታቀደለትን ዓላማ አሳክቷል ወይም ሙስናን ከሀገሪቱ በመቀነስ ወይም በማጥፋት ረገድ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም ትልቁና ዋንኛው ችግር ተቋሙ ከፖለቲካ እና ከገዥው ፓርቲ ተፅእኖ ነፃ ያልሆነና እራሱም ቢሆን ከሙስና ያልፅዳ በመሆኑ ነው።

መንግሥት ሙስናን እዋጋለሁ እከላከላለሁ ብሎ ለኮሚሽኑ ሥራ ማስኬጃ በምሚልየኖች የሚቆጠር የየሀገር ሀብት ያፍስስ እንጂ ሙስናን በመታግል የሚታወቀው ትራንስፓረንሲ ኢንተር ናሽናል የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በየአመቱ ከሚየወጣው ሪፖርት ቀረብ ያሉትን ዓመታት በናሙናነት ብንመለከት በጥናቱ ከተካተቱት 177 ሀገሮች ውስጥ ሀገራችን እ.ኤ. በ2013, 111ኛ፣ 2014, 110ኛ፣ በ2015, 103ኛ በ2016 108ኛ ላይ እንደምትገኝ ጥናቱ ያሳያል።

ይህ የሚያሳየው በሚልየኖች የሚቆጠር የሀገር ሀብት የፈሰሰበት ተቋም ውጤት አልባ መሆኑን ነው። በሀገሪቱ ግዜ እየጠበቀ የሚከናወነው የፀረ ሙስና ዘመቻ ዓላማ፦

ገዥው ፓርቲ የውስጥ ሹኩቻና መከፋፈል ሲመጣበት አንዱ ቡድን ሌላውን ለማዳከም፣ ለማጥፋት እና እራሴን እያፀዳሁ ነው ለማለት፣ የህዝብ ብሶትና ጥያቄ አፍጥጦ ሲመጣበት የህዝብን ጥያቄ የመለሰ ለማስመሰል ነው።

ይህ የሙስናውን ሥር ሳይነካ ቅርንጫፉን በመከርከም ፍሬውን የማለምለም ዘዴ ነው። ምክንያቱም ቀደም ሲል የተወሰዱት እርምጃዎች የሚያሳዩት ያልተፈለገውን የሙስና ጀሌ በግምገማ አንስቶ ሌላ ባለድርሻ ሙሰኛን መተካት ወይም መክሰስ እንጂ የፀረ ሙስናው ዘመቻ ዋንኞቹ ሙሰኞች ላይ ሲያነፃፅር ብሎም የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት እውነተኛ እርምጃ መወሰዱን አይደለም።

ዓመታዊ ሪፓርት የሚቀርብለት ፓርላማም ሪፓርቱን ከማዳመጥ እና የይስሙላ አስተያየት ከመስጠት በዘለለ የሚሰጠው ፋይዳ የለም። በምሳሌነት ወሬ ሆኖ የቀረውን የባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባ መጥቀስ ይቻላል።

መንግሥት ሰሞኑን እየወሰደ ያለው እርምጃ የሙስና ጀሌዎቹን በማሰር እና በመክሰስ የህዝቡን ቀልብ ስቦ ቀጣይ የሙስና ተግባሩን በአዲስ ጀሌዎች የሚተካበት ሂደት እንጂ የህዝብ ጥያቄን መመለስ ወይም ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን ለማድረግ አይደለም።

እህአዴግ መራሹ መንግሥት የሀገሪቷን ሀብት ሲሻው በባለሥልጣናቱ፣ ሲሻው የተለያየ ስም ለጥፎ በዘርና በጎሣ በአቋቋማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ ሲሻው ደግሞ በየቦታው በሰገሰጋቸው የፓርቲ አባሎቹ የህዝብና የሀገር ሀብትን እየተቀራመተ ያለ ዋንኛው ተዋናይ ስለሆነ የሰሞኑ የፀረ ሙስና ዘመቻ ግርግር የህዝቡን የመብት ጥያቄ ለማዘናጋት የተወጠነ የኢህአዴግ ሴራ ነው።

መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ተደርጎ ሀገሪቷን እና ህዝቧን በእኩልነትና በነፃነት የሚያስተዳድር፣ ከግል ጥቅም ይልቅ የሀገር እና የህዝብ ጥቅምን የሚያስቀድም መንግሥት እስከሌለ ድረስ ሙስና ከኢትዮጵያ ውስጥ ይወገዳል ማለት ዘብት ነው። የኢህአዴግ መንግሥት በአንድ ወቅት የተከሰተን የወረርሽኝ በሽታን የሚከላከል ይመስል ወቅት እና ግዜ እየጠበቀ የሚያካሂደው የፀረ ሙስና ዘመቻ ለሀገሪቷም ሆነ ፍትህና ነፃነት ለጠማው ህዝብ የሚያመጣው ለውጥ የለም።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሥራውን በአግባቡ መሥራት የተሳነው የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አሁንም በትእዛዝ ክሰስ የተባለውን ከመክሰስ በቀር በህግና በነፃነት ተንቀሳቅሶ ሙስናን እና ሙሰኞችን ይዋጋል ማለት ዘበት ነው።

ዘመቻው ኢህአዴግ እድሜውን ለማራዘምና የሙስና ስልቱን ለመቀየር የሚያካሂደው ነው። እስኪ ውጤቱን አብረን እንጠብቅ።

ቸር ይግጠመን።

ነሐሴ, 2017

1 COMMENT

LEAVE A REPLY