የኦሮሞ ማህበረሰብና ቄሮዎች መንቃት አለባቸው /ግርማ ካስ/

የኦሮሞ ማህበረሰብና ቄሮዎች መንቃት አለባቸው /ግርማ ካስ/

አንደኛ የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥያቄዎችን ከሌሎች ማሀብረሰብ ጥያቄዎች ጋር በማቀናጀት ትግሉን አገር አቀፍ ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን መረዳት አለበት።

በኦሮሚያ ለ5 ቀናት ታዉጆ የነበረው አድማ በ 3 ቀናት ውስጥ ውጤት አስመዝግቧል በሚል አድማው መጠናቀቁን የቄሮ አስተባባሪ በመግለጫው እንዳስታወቀ እያነበብን ነው። አድማው ባነሳቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምን ውጤት እንደተመዘገበ ግልጽ አልሆነልኝም። እነ ዶር መራራ አሁንም በወህኒ ናቸው። በግብሩ ጉዳይ ከሶስት ቀናት በፊት ከነበረው ብዙ የተለየ ነገር የለም። በሶማሌ ልዩ ሃይል በኩል እየተደረገ ባለው ጥቃትም ዙሪያ አድማው ያስቀየረው ነገር አለ ብሎ ማሰብ አይቻልም። ምን አልባት የኦህዴድን መግለጫ ከሆነ አስተባባሪዎቹ እንደ ድል የገለጹት፣ “ጉዳዩን አሁን ለኦህዴድ ጥለነዋል” በሚል፣ እርሱ አንድ ነገር ነው።

አድማዉ ቀደም ሲል በስፋት ተግባራዊ ይሆናል ብዬ በተነበይኳቸው ቦታዎች ተግባራዊ ሆኗል። ተግባራዊ አይሆንም ባልኳቸው ቦታዎች እምብዛም ተግባራዊ አልሆነም። ቄሮዎች (የኦሮሞ ጎሮምሶች) ከምእራብ አርሲ፣ ከወለጋ፣ ከምእራብ ሸዋ፣ ከሃረርጌና ከባሌ ሮቢና ከተወሰኑ የደቡብ ምእራብ ሸዋ አካባቢዎች ዉጭ በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች (ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ሱሉልታን ሳይጨምር ድፍን የሰሜን ሸዋ ዞን፣ እንደ አሰላ ያሉበት የአርሲ ዞን፣ የጉጂ ዞን፣ የቦርረና ዞን ፣ ከሮቢ ውጭ እንዳለ የባሌ ዞን፣ የኢሊባቡር ዞን፣ ከአንድ ትንሽ መንደር በቀር የጂማ ዞን፣ ያዳማ ልዩ ዞን፣ የጂማ ልዩ ዞን ..) እንቅስቃሴ ታይቷል ማለት አይቻልም። ነገሮችን ለመደባበስና ድክመት ለመሸፈን ከመሞከር ረጋ ብሎ ማሰብና መጠየቅ አስፈላጊ ነው። የሰሞኑ አድማ ያለፈው አመት ከነበረው በጣም ሲበዛ የቀዘቀዘ ነበር። የሁለተኛው ቀን አድማ ክመጀመሪያው ቀን፣ የሶስተኛው ደግሞ ከሁለተኛው ቀን ግለቱ ቀንሷል።

ቄሮዎች የትግል ሜዳዉን አድማስ በተቻለ መጠን ወደ ኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞችና ብዙ ሌሎች ማህበረሰቦች በሚኖሩባቸው ዞኖች ማስፋት ያለባቸው ይመስለኛል። ከኦሮሚያ ዉጭ ያሉትን እና ከሁለት ሶስተኛ በላይ ሕዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎችን፣ በኦሮሚያ ውስጥ እነ አዳማ፣ እነ ቢሾፍቱ፣ እነ ጂማ፣ እነ ፍቼ፣ እነ አሰላ፣ እነ መቱ. እነ ኡሩርታ፣ እነ አጋሮ፣ እነ ጎሬ፣ እነ በደሌ፣ እነ ቦቆጅ፣ እነ ሽኖ፣ እነ ጫንጮ፣ እነ ዱከም፣ እነ ዝዋይ፣ እነ መቂ፣ እነ ሞጆ፣ እነ አዲስ አበባ/ሸገር ያሉ እነ አወዳይን፣ እነ አምቦን፣ እነ ደምቢዶሎን ፣እነ ዶዶላን ….ቢቀላቀሉ ይሄን ጊዜ ትልቅ ድሎች ተመዝግበዉ ነበር። ያ ነው መሆን ያለበት።

ታዲያ ይሄ እንዲሆን ምንድን ነው መፍትሄው ?

አንደኛ የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥያቄዎችን ከሌሎች ማሀብረሰብ ጥያቄዎች ጋር በማቀናጀት ትግሉን አገር አቀፍ ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን መረዳት አለበት። ቄሮዎች ለምሳሌ ካነሷቸው ሶስት አጀንዳዎች ሁለቱ (የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱና ያለመጠን በህዝብ ላይ የተጫነው ግብር እንዲቆም) በርግጠኝነት የሁሉም ጥያቄ ነበር። በዚህ አጅነዳ ዙሪያ ሌሎችን ማሳተፍ ይቻል ነበር።

ሁለተኛ የኦሮሞ ማህበረሰብ በኦሮሚያ ጥያቄ እንዳለው ሁሉ በኦሮሚያ ያለ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕብረ ብሄራዊ የሆኑ ማህበረሰብ አለ። የዚህ ማህበረሰብ ጥያቄ ፣ ለምሳሌ በኦሮሚያ አማርኛም የሥራ ቋንቋ እንዲሆን፣ በአማራው ክልል እነ ከሚሴ የራሳቸው የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንደተሰጣቸው በኦሮሚያም እንደ አዳማ፣ ጂማ ፣ አሰላ ….ያሉም የራሳቸው ዞን ተሰጥቷቸው አብዛኛው ህዝብ በሚናገረው ቋንቋ ራሳቸዉን እንዲያስተዳደሩ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ይሄን የሌላውንም ማህበረሰብ መብት ቄሮዎች መገንዘብና መቀበል መቻል አለባቸው።

ሶስተኛ “በጉራጌዎች ላይ ዘላለማዊ እርምጃ እንወስዳለን” የሚሉ በዉጭ ያሉ ጸረ-ኢትዮጵያና ዘረኛ አካራሪዎች ትግሉን ሃይ ጃክ እንዳያደርጉትና የነዚህ ሃይሎችን ጉዳት ተረድቶ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሰዎች አጋር የሆኑበት ወይንም እንደ መሪ/ቃል አቀባይ የሚቆጠሩበት ማናቸዉን አይነት እንቅስቃሴዎች፣ ብዙም ሳይሄዱ፣ ሌላው ማህበረሰብ በጥርጣሬ የሚያያቸው ብቻ ሳይሆን የሚቃወማቸዉም ነው። እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን ትበታተን ከፈለገች የሚሉ ናቸው። ሌላው ኢትዮጵያዊ በአገሩ በኦሮሚያ ዉስጥ” መጤ ነው, ፣ እንደ ዉጭ አገር ዜጋ” የሚሉ ናቸው። ብዙዎች ከሕወሃቶች የበለጠ የነዚህን ሰዎች አስተሳሰብና ፖለቲካ በጣም ያስፈራቸዋል። እኔን ብትጠይቁኝ ከኦነግና እንደ ኦሮሚያ ፈርስት ካሉት፣ አስር እጥፍ ህወሃት ይሻለኛል።

የኦሮሞ ወጣቶች በዚህ አገዛዝ ብዙ ግፍና ጭካኔ የደረሰባቸው ናቸው። ትልቅ የኢኮኖሚ በደል የተፈጸመባቸው ናቸው። ተምረው ስራ ማግኘት አይችሉም። በአገራቸው አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። የግፍ ቀንበር በላያቸው ላይ ተጭኗል። የነርሱን ሕመም ሌላውም ይረዳዋል። ራሳቸውን ለይተው ማቆም የለባቸውም ባይ ነኝ።

አዎን የኦሮሞ ወጣቶች በኦነግና በኦሮሞ ፈርስት ፖለቲካ አይምሯቸው እንዲቆሽሽ፣ ከሌላው ወገናቸው ጋር በቋንቋ እንዳይግባቡና ሌላውን ማህበረሰብ በጥርጣሬ እንዲያዩ፣ እንዲጠሉ የተደረጉ ናቸው። የተጣመመ የጥላቻ ታሪክ እየተነገራቸው ያደጉ ናቸው። አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ግን በሶሻል ሜዲያና በኦሮሞ ሜዶያ ኔትዎርክ የጥላቻ አርበኞችን ከሚያዳምጡ፣ በሚኖሩበት ቦታ ያሉ አባቶቻቸውን፣ እናቶቻቸዉን፣ አረጋዉያንን፣ ቄሶችን፣ ሼኮችን ቢያነጋግሩ ፣ ከነርሱ ቢማሩ ጥሩ ነው የሚሆነው። የኦሮሞ ባህል ዘረኝነት አይደለም። አንድነት ነው። የኦሮሞ ባህል ሰው አይለይም፤ ሌላውን የራሱ የሚያደርግ ነው። ኦሮሞ እንዲህ ደረሰብኝ ብሎ ብሶት የሚያወራ አይደለም። መሰናክልን አልፎ መፍትሄ የሚያመጣ ነው። ኦሮሞ ራሱን አግሎ ለብቻው የሚቀመጥ አይደለም። ኦሮሞ ትልቅ ነው። ኦሮሞ ግንድ ነው።

የኦሮሞ ቄሮዎችና ማህበረሰብ መንቃት ያለባቸው መሰለኝ።

LEAVE A REPLY